1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድርቅ አደጋ ስጋት በጉጅ ዞን

ዓርብ፣ የካቲት 17 2009

በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ ስጋት እየጨመረ ነዉ ተባለ። በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በአንድ ቀበሌ ብቻ እስከ 300 ከብት መሞቱ ተገልጿል። በዞን የሚኖሩ አርብቶ አደሮች አደጋዉ እንስሳት ለይ ብቻ ሳይሆን ሰዉም ላይ እያንዣበበ መሆኑን በመግለፅ አፋጣኝ እርዳታ እንዲደረግላቸዉ ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/2Y9il
Äthiopien Dürre
ምስል CC BY EU/ECHO/Anouk Delafortrie-ND 2.0

Drought in Guji Zone Ethiopia - MP3-Stereo

 የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ  እርዳታዉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በድርቅ ከተጠቁ አራት ክልሎች፤ የኦሮሚያ ክልል አንዱ ነዉ። በክልሉ በተለይ በጉጂ ዞን በድርቅ ምክንያት የመጣዉ አደጋ በአካባቢዉ አርብቶ አደሮች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል ተብሏል። አርብቶ አደሮቹ እንደሚገልጹት በድርቁ ሳቢያ ዉኃና የግጦሽ ሳር በመጥፋቱ እንስሶቻቸዉ እየሞቱ ነዉ።
በጉጂ ዞን የሻኪሶ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ  የፈለጉ  ግለሰብ  ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ ዝናብ ባለመዝነቡ ዉኃና የግጦሽ ሳር ተመናምኗል። በመሆኑም ከሻኪሶ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኙ የአርብቶ አደሩ መንደሮች ከብቶች መሞት ጀምረዋል።

የዝናቡ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ በሰዉም ይሁን በእንስሳት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ስጋት ተደቅኗል ሲሉም አብራርተዋል። አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገም በስፍራዉ ሰብአዊ ቀዉስ ሊከሰት ይችላል ሲሉም ግለሰቡ  ስጋታቸዉን ተናግረዋል።
በጉጂ ዞን የዶዶላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርብቶ አደር ረጋሳ ዱለቻ በበኩላቸዉ እሳቸዉ በሚኖሩበት ቀበሌ በክረምት በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ የተነሳ ለእንስሳትም ይሁን ለሰዉ በቂ ዉኃ የለም ብለዋል። በዚህ የተነሳ የቀየዉ ሰዉ ዉኃ ፍለጋ ሙሉ ቀን እንደሚጓዝም ገልጸዋል። ያም ሆኖ ግን የእንስሳቱን ሕይወት መታደግ እንዳልተቻለ አርብቶ አደሩ ተናግረዋል።

አስራ ሁለት ከብቶቻቸዉ በድርቁ ሳቢያ እንደሞቱባቸዉ የሚናገሩት አርብቶ አደር ረጋሳ ዱለቻ በአካባቢያቸዉ በግምት ከ300 መቶ በላይ ከብቶች መሞታቸዉንም ይናገራሉ።  በዝናብ እጥረት ሳቢያ እንደ ግጦሽ መሬቱ ሁሉ ለሰዉ ምግብነት የሚዉሉ ሌሎች ሰብሎችም ለጉዳት ተዳርገዋል። በመሆኑም  እንስሳቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰዉ ላይም  አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ ገልጸዋል።

Pastoralisten Somalia
ምስል DW/J.Jeffrey

እንደ አርብቶ አደሩ ገለጻ አሁን ባለዉ ሁኔታ በምግብ እጥረት የሞተ ሰዉ ባይኖርም፤ በቂ ምግብ ባለማግኘት ምክንያት የታመሙ እና የደከሙ ሰዎች መኖራቸዉን ግን አልሸሸጉም። በመሆኑም በሰዉም ይሁን በእንስሳት ላይ ድርቁ የከፋ ጉዳት ሳይመጣ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኑነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘዊዴ በበኩላቸዉ በሀገሪቱ ድርቅ በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች ለሰዉም ይሁን ለእንስሳት እርዳታ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ባልተዳረሰባቸዉ አካባቢዎችም ከስፍራዉ በሚመጣ መረጃ መሠረት ሥራዉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ