1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶይቸ ባንክ የአመራር ተሃድሶ

ረቡዕ፣ ግንቦት 29 2004

ታላቁ የጀርመን የገንዘብ ተቋም ዶይቸ ባንክ ባለፈው ሣምንት የአመራር ለውጥ በማድረግ ወደፊትም ዓለምአቀፍ ክብደቱን እንደጠበቀ ለመቀጠል በአዲስ መንፈስ ተነሳስቷል።

https://p.dw.com/p/158QA
ምስል picture-alliance/dpa

ታላቁ የጀርመን የገንዘብ ተቋም ዶይቸ ባንክ ባለፈው ሣምንት የአመራር ለውጥ በማድረግ ወደፊትም ዓለምአቀፍ ክብደቱን እንደጠበቀ ለመቀጠል በአዲስ መንፈስ ተነሳስቷል። ባለፈው አሠርተ-ዓመት የባንኩ ዕርምጃ ላይ አሻራቸውን አስፍረው የተሰናበቱት የተቋሙ የቀድሞ መሪ የዮዜፍ አከርማን ሥልጣን መልቀቅ እርግጥ ድንገት የመጣ ነገር አይደለም። ውጣ-ውረድ ሲባልበት የቆየ ጉዳይ ነው።

የስዊትዘርላንዱ ተወላጅ አመራሩን በፈቃዳቸው እንደሚያስረክቡ ያስታወቁት ቀደም ሲል ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ነበር። ባንኩ ባለፈው ሐሙስ ሕንዳዊ ምንጭ ያላቸውን አንሹ ጄይንንና ዩርገን ፊትሸንን ለጥንድ አመራር ሲመርጥ በነዚሁ መንኮራኩርነት በተሃድሶ አቅጣጫ እንደሚራመድ ነው የሚጠበቀው። ሁለቱ አዳዲስ መሪዎች ስለ ባንኩ የወደፊት ስልታዊ ዕርምጃ በፊታችን መስከረም ወር ዕቅዳቸውን እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል።

ዶይቸ ባንክ በዚህ በጀርመንና በዓለምአቀፍ ደረጃም በሚያካሂደው የፊናንስ ተግባሩ የታወቀና ከቀደምቱ የገንዘብ ቤቶች አንዱ ሲሆን ከዋና መቀመጫው ከፍራንክፈርት አንስቶ እስከ ኒውዮርክ፣ ለንደን፤ ሢንጋፑርና ሢድኒይ ወዘተ አንድ መቶ ሺህ ገደማ የሚጠጉ ሠራተኞች አሉት። የጀርመን የተረጋጋ የኤኮኖሚና የፊናንስ ዕርምጃ መለያ ሆኖ የኖረው ባንክ በጎርጎሮሣውያኑ 1870፤ ማለትም ከ 142 ዓመታት በፊት ሲቋቋም ትልቅ ሊሆን የበቃው በተለይም በሃያኛው ምዕተ-ዓመት ሌሎች ተቋማትን በመጠቅለል ነበር።

ከዚያን ወዲህ እየተስፋፋ ሲመጣ በፍራንክፈርትና በኒውዮርክ የምንዛሪ ገበዮች ለይም ህያው ሆኖ ይገኛል። ዶይቸ ባንክ «ፋይናንሺያል ስታቢሊቲይ ቦርድ» በተሰኘው የፊናንስ ዕርጋታ ተመልካች አካል እንደተጠቀሰው በይዞታው ጠቃሚ የገንዘብ ተቋም ተብለው ከተደለደሉት 29 ታላላቅ የዓለም ባንኮች አንዱ ነው። ይህም የራሱን የካፒታል ብቃትና አስተማማንነት ያመለክታል። ባንኩ ያላንዳች መንግሥታዊ ድጎማ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ ሲያሳልፍ ለአያሌ ዓመታት በጀርመን መንግሥት የፊናንስ ፖሊሲ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ኖሮት ነው የቆየው።

ይህ ከጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ባንክ ወደፊትም ተሰሚ ሆኖ በመቀጠሉ ብዙ የሚጠራጠር የለም። ግን ለመሆኑ ይህን የጀርመንን መለያ መንኮራኩር የሚዘውሩት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ከተለያየ ባሕልና አስተዳደግ፣ ቋንቋ፤ እንዲሁም ከተለያየ ሙያ የመነጩ ሲሆኑ የዚያኑ ያህል ደግሞ አንዱ ለአዲስ ሙከራ የሚደፍር ሌላው ጠንቀቅ ብሎ በሁለት እግሩ መሬት ላይ የቆመን ያህል ናቸው። መጥፎ ድብልቅ አይደለም።

Bildkombo Anshu Jain Jürgen Fitschen Deutsche Bank
ምስል picture-alliance/dpa

አንሹ ጄይን በምንዛሪ ገበያ ላይ ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ ከ 17 ዓመታት በፊት በ 1995 ዶይቸ ባንክን ሲቀላቀሉ የገቡበትን የመዋይለ-ነዋይ ዘርፍ በዓለም ላይ ቀደምት ለማድረግ በቅተዋል። በባንኩ የለንደን ቅርንጫፍ ከአከርማን ይልቅ ብዙ ገቢ ማስገኘታቸው ነው የሚነገርላቸው። ጠበብት በፊናንስ ትንታኔ በቃትና የፊናንስ ንግድ ተሰጧቸው እጅጉን ያደንቋቸዋል። በሕንድ የተወለዱት ባለሙያ በአጭሩ ለንግዱ ዓለም የተፈጠሩ ናቸው። ይህም ነው በመሠረቱ ለአከርማን ተተኪነት ያበቃቸው። አንጋፋው ጀርመናዊ የሥልጣን ተጋሪያቸው ዩርገን ፊትሽን ደግሞ ቀድሞ በነጋዴነትና በውጭ ንግድ ልምድ ያካበቱ ሲሆኑ በ 1975 ነበር ዶይቸ ባንክን የተቀላቀሉት።

አንሹ ወደፊት ተጠናክሮ በሚቀጥለው ፉክክር ሳቢያ በዓለም ላይ አምሥት ወይም ስድሥት ትልልቅ ባንኮች ብቻ እንደሚቀሩ ነው የሚያምኑት። ዶይቸ ባንክ ደግሞ ከነዚህ መካከል አንዱ እንደሚሆን ጨርሶ ጥርጥር የላቸውም። እንደርሳቸው አስተሳሰብ ምናልባትም በመጨረሻ ከነዚሁ መካከል ብቸኛው አሕጉራዊ የአውሮፓ ባንክ ሊሆን ይችላል። አዲሱ አመራር በዓለምአቀፋዊ የባንክ ተግባሩ የሚቀጥል ሲሆን መቀመጫው ግን ኤኮኖሚዋ ጠንካራ ከሆነው ከጀርመን፤ ከፍራንክፍርት አይነቀልም።

ወደ ባንኩ ታሪክ መለስ እንበልና ዶይቸ ባንክ በቀድሞው የአገሪቱ ምንዛሪ በዴ-ማርክ ጥንካሬና ዕርጋታ ብቻ ሣይሆን በአውቃቀርና በአደረጃጀቱም ዛሬ ፍራንክፈርትን ማዕከሉ ላደረገው ለኤውሮው ምንዛሪ አካል ለአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ምሥረታም በጊዜው በሞዴልነት መወስዱ ይታወሣል። ባለፉት 12 ዓመታት ባንኩን የመሩት የዮዜፍ አከርማን ዘመን አሁን ሲያከትም እርግጥ የፊናንሱ ባለሙያ ጀርመናዊ አለመሆናቸው በበርሊን መንግሥት ዘንድ ክብደት እንዳያገኙ አላደረጋቸውም። በሌላ አነጋገር ክብደት የሚሰጠው የጀርመን መንግሥት ተባባሪ ለመሆን የዶይቼ ባንክ መሪ የግድ ጀርመናዊ መሆን የለበትም።

ይህ ሚና ቀደም ባሉት መሪዎች በሄርማን-አብስ ኢነ፣ በአልፍሬድ ሄርሃውዘንና በኋላም በስዊሱ ተወላጅ በዮዜፍ አከርማን ዘመን በጉልህ ታይቷል። የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል ለምሳሌ የአከርማንን 60ኛ ዓመት ልደት ለማክበር የምግብ ግብዣ እስከማድረግ ደርሰው ነበር። ይህ በብዙ ሚሊዮን ኤውሮ ባለጸጋ ለሆኑት የባንክ አስተዳዳሪ መደረጉ ደግሞ እርግጥ በጊዜው ግብር ከፋዩን ሕዝብ ማስቆጣቱ አልቀረም። ያም ሆነ ይህ አከርማን አሻሚ ባህርይ ቢኖራቸውም በሌላ በኩል የፍራንክፈርት የፊናንስና የአስተዳደር ትምሕርት ተቋም ባልደረባ ክሪስቶፍ ሻላስት እንደሚሉት ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራቸው። አዳዲሶቹ መሪዎች ለዚህ መብቃታቸው ገና ወደፊት የሚታይ ነው።

«ከዚያ ለመድረስ በትጋት መሥራት ያስፈልጋል። ለታማኝነት መብቃት፣ ምስጢርን በስርዓት መያዝ፣ ለራስ ጥቅም ከመጣር መቆጠብና ሃቀኛ አማካሪ ሆኖ መቅረብ ግድ ነው። ተተኪዎቹ እንግዲህ ይህን መቻላቸውን በመጀመሪያ ማሣየት ይኖርባቸዋል»

Deutschland Wirtschaft Banken Hauptversammlung Deutsche Bank Josef Ackermann
ምስል dapd

የአከርማን ተተኪዎች ከሁሉም በላይ የሚጠበቅባቸው እርግጥ የባንኩን የአክሢዮን ባለቤቶች መልሶ ለአትራፊነት ማብቃት ነው። በአከርማን ዘመን በዚህ ረገድ ትልቅ ውዥቀት ታይቷል። አከርማን ከ 12 ዓመታት ገደማ በፊት በባንኩ ተጠሪ አካል አፈ-ቀላጤነት ሲጀምሩ የዶይቸ ባንክ አክሢዮን በፊናንሱ ገበያ 76 ኤውሮ ያወጣ ነበር። ከዚያም በ 2007 ወደ 118 ኤውሮ ሲያሻቅብ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ወቅት በ 2009 ወደ 15 ኤውሮ ያቀለቁላል።

በጥቅሉ የዶይቸ ባንክ አክሲዮን ባለፉት አሥር ዓመታት 60 በመቶ ዋጋውን አጥቷል። እንግዲህ በጊዜው ትርፍ በመሻት የተቋሙን አክሢዮን በመግዛት ፈንታ ገንዘቡን በቁጠባ ደብተሩ ውስጥ ያቆየ ደምበኛ ከክስረት ድኗል ወይም አምልጧል ማለት ነው። ይህን የማቆልቆል ሂደት ባንኮችና የምንዛሪው ገበዮች በጎ ሁኔታ ላይ በሚገኙባቸው ዓመታት በመዋዕለ-ነዋይ ለመግታትና ለማሻሻል ይቻላል።

ለነገሩ ዶይቸ ባንክም በፊናንሱ ቀውስ መነካቱና ወይም በሌላ አነጋገር አደገኛ የገንዘብ ሰነዶችን ገበያ ላይ በማውጣት ለዚሁ አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም። እናም ለውዥቀት በተጋለጠው የመዋዕለ-ነዋይ የባንክ አሠራርና በግል ወይም የኩባንያ ንግድ ረገድ ሚዛንን መጠበቁ ለአዲሱ አመራር ምናልባትም ፈታኝና ከባድ ሸክም የሚሆን ነው። ነገር ግን የፍራንክፈርቱ የባንክ ሙያ ፕሮፌሰር ራይንሃርድ ሽሚት እንደሚሉት አማካይ ስልታዊ መንገድ ሊገኝም ይችላል።

«ለምሳሌ እንደሆኔታው ከአንድ ብድር ጋር የተሳሰሩ ብዙ የክስረት አደጎች መኖራቸውን ማሰብ ይቻላል። እንበል የምንዛሪ ውዝቀት አደጋ! እናም አንድን መዋዕለ-ነዋይ የምንዛሪ አደጋን ከማስወገዱ ጋር አጣምሮ ማቅርብ እንደሚቻል ማስረዳት ያስፈልጋል። ይህን ዓይነቱ ድብልቅ ዘዴ በተለይ ጠቃሚ ነገር ነው»

ዶይቸ ባንክ በዮዜፍ አከርማን የአመራር ዘመን መዋይለ-ነዋይንና ነባሩን የባንክ ንግድ ተግባር ግማሽ በግማሽ ለማጣጣም ዕቅድ ነበረው። ሆኖም እስከዛሬ ግንኙነቱ 60 ለ 40 ነው። ታዲያ አሁን የመዋይለ-ነዋይ ባንኩ ባለሙያ አንሹ ጄይን በአመራሩ አካል ቁንጮ ላይ በተቀመጡበት ሰዓት 50 ለ 50 የሚለው ራዕይ ጽናት ኖሮት ይቀጥል ገና በውል አይታወቅም። ጄይን በ 49 ዓመት ዕድሜ 63 ለደረሱት የሥልጣን ተጋሪያቸው ለዩርገን ፊትሽን ወጣት ሲሆኑ ምናልባትም በቅርቡ አመራሩን ለብቻቸው ሊይዙ ይችሉ ይሆናል። ይህም የባንኩ ባለሙያ ቪስላቭ ዩርቼንኮ እንደሚሉት ተጽዕኗቸውን የጎላ ነው የሚያደርገው።

«የመዋዕለ-ነዋዩ ባንክ በዚህ መሰሉ የገንዘብ ተቋም ውስጥ ታላቅ የገቢ ድርሻ በሚኖረው ጊዜ በስልታዊ አካሄድ ረገድ በአመራሩ ላይም ከዚሁ የተጣጣመ የተጽዕኖ አቅም ይፈጠራል ማለት ነው»

እስካሁን በባንኩ ውስጥ በሙያም ሆነ በአስተዳደር በየዘርፉ የተሰየሙት ሹማምንት የጄይን ታማኞች ናቸው። ሆኖም ስልታቸውን በእርጋታ እንዲያረቁ የአውሮፓው መንግሥታዊ የዕዳ ቀውስ ፋታ ይስጣቸው አይስጣቸው በዶይቸ ባንክ ውስጥ በውል ያልለየለት ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ