1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለም ጤና ድርጅት ስብሰባ በዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ላይ ተቃውሞ ተሰንዝሯል

ሰኞ፣ ግንቦት 14 2009

የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት በጄኔቫ ነገ የድርጅቱን ዳይሬክተር ጄኔራል ይመርጣሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በምስጢራዊ ድምፅ አሰጣጥ ለመመረጥ በእጩነት ከቀረቡት ጎራ የሚገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ እና የጤና ጥበቃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ደጋፊዎች እና ነቃፊዎች በየፊናቸው ዘመቻ ላይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/2dOsx
Äthiopische Rückkehrer aus Jemen Theodros Adhanom Interviewpartner
ምስል DW/T. Getachew

mmt Dr.Tedros WHO Election controverssy among Ethiopians - MP3-Stereo


የዓለም ጤና ድርጅት 70ኛ መደበኛ ስብሰባ በዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ላይ በተሰነዘረ ተቃውሞ አንድ ተብሎ ተጀምሯል። ዛሬ በስዊዘርላንዷ የጄኔቫ ከተማ የተጀመረውን ስብሰባ ድንገት በተቃውሞ የናጡት አቶ ዘላለም ተሰማ የተባሉ የፖለቲካ አቀንቃኝ መሆናቸው ተሰምቷል። የፖለቲካ አቀንቃኙ በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው እስኪወጡ ድረስ «አፍሪቃ በድጋሚ አስቢ» የሚል መፈክር ሲያሰሙ የሚያሳይ የቪዲዮ ምሥል በዓለም ጤና ድርጅት ድረ-ገፅ ታይቷል።  

ዶ/ር ቴዎድሮስ ተቃውሞ የገጠማቸው ግን በስብሰባ አዳራሹ ብቻ አይደለም። በስዊትዘርላንዷ የጄኔቫ ከተማ አደባባይ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፅ/ቤት ፊት ለፊት አቶ ካሳሁን አደፍርስን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን የዓለም ጤና ድርጅት እጩነታቸውን ተቃውመዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ለአለም ጤና ድርጅት በኃላፊነት መመረጥ የለባቸውም የሚል አቋም ያላቸው አቶ ካሳሁን ፖለቲካዊ መፈክሮች ከፍ ብለው በተሰሙበት የተቃውሞ ሰልፍ ተሳትፈዋል። አቶ ካሳሁን በተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲወቀስ ፤ በሕግ ያገዳቸው ሰንደቅ አላማዎችም ሲውለበለቡ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጩ ምሥሎች ያሳያሉ። ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የገዢው ፓርቲ አባል መሆናቸውን የሚያስታውሱት አቶ ካሳሁን «ባለፉት አመታት በነበሩ ችግሮች ብዙ ንጹኃን ዜጎች ተገድለዋል። በንጹኃን ዜጎች ግድያ የሚፈለግ ሰው ትልቅ ክብር ወዳለው የጤና ድርጅት ያውም ለመሪነት መመረጥ የለበትም» ሲሉ ይሞግታሉ። 

Logo der Weltgesundheitsorganisation (engl. kurz WHO)

በዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ በተለያዩ የስዊዘርላንድ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል። እንደ ተቃውሞው ሁሉ  ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የዓለም የጤና ድርጅትን በበላይነት ለመምራት ብቁ ናቸው የሚሉ ኢትዮጵያውያንም ነገ በዚያው የጄኔቫ አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ያደርጋሉ። በዚያው በጄኔቫ አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ የተዘጋጁት አቶ ሽመልስ በዛብህ «ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒሥትር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት የእናቶች እና ሕፃናት ሞት ቁጥር እንዲቀንስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የምዕተ-ዓመቱን ግብ (ኢትዮጵያ) ቀድማ እንድታሳካ ያደረጉ መልካም ኢትዮጵያዊ ናቸው» ባይ ናቸው። ዶ/ር ቴድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉባቸው አመታትም «ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም ጋራ ያላት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል ያደረጉ ትሁት እና ጨዋ ሰው መሆናቸውን እንደ አንድ ዜጋ የምረዳ ሰው በመሆኔ ቴድሮስ ያልተመረጠ ማን? የሚል እሳቤ ነው ያለኝ» ሲሉ ያክላሉ። 

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሥመ-ጥር ፖለቲከኞች እና የጤና ባለሙያዎች ይፋዊ ድጋፍ ያገኙት  ዶ/ር ቴድሮስ ከኢትዮጵያውያን ዘንድ የከፋ ትችት እና ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ዶ/ር ቴድሮስ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ሊደገፉ ይገባል ከሚሉት ጋር አይስማሙም። ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ አቶ በቀለ ገርባ፤ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አንዱዓለም አራጌን የመሳሰሉ «በመፃፋቸው ብቻ ወይም የተቃዋሚ አመራር በመሆናቸው ብቻ የታሰሩ ሰዎች አሉ» የሚሉት አቶ ካሳሁን የእሥር እርምጃዎቹ ሲወሰዱ «ከፊት ሆኖ በመሪነት ያለን ሰው ለምን ኢትዮጵያዊ ስለሆነ አትደግፉም? ማለት አግባብነት ያለው ጥያቄ አይመስለኝም።» ሲሉ ይናገራሉ። 

ብሪታንያዊው ዴቪድ ናባሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም
ብሪታንያዊው ዴቪድ ናባሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖምምስል E. Capobianco

ለነገው የድጋፍ ሰልፍ የተዘጋጁት አቶ ሽመልስ በበኩላቸው ከአቶ ካሳሁን ፈፅሞ የተቃረነ አቋም አላቸው። «በተቃዋሚ ጎራ ያለ ሰው እንኳን ለእንደዚህ ያለ ኃላፊነት ቢታጭ በእኔ እምነት ኢትዮጵያዊ መሆኑ ስለሚያኮራኝ ያርግለት ብዬ ነበር የምለው» ይላሉ አቶ ሽመልስ። «በእንደዚህ አይነት ፅንፍ የለቀቀ ጥላቻ አንድ የአገሩ ዜጋ ለዚህ ሲመረጥለት እማይደሰት ትውልድ ያየሁበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው» ሲሉም የዶ/ር ቴድሮ አድኃኖምን የመመረጥ ዕድል ለመቃወም በጄኔቫ አደባባይ የታደሙ የአገራቸው ዜጎችን አምርረው ይወቅሳሉ። 

ለዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊነት እጩነታቸውን ካሳወቁ ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተዘዋወሩ ሲቀሰቅሱ የከረሙት ዶ/ር ቴድሮስ ከብሪታኒያዊው ዴቪድ ናባሮ እና ከፓኪስታናዊቷ ሳኒያ ኒሽታር የበረታ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ