1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀልባ ስደተኞች ሞት ያስከተለው አስተያየት

ሰኞ፣ መስከረም 27 2006

በኢጣልያ የባህር ክልል አካባቢ ሐሙስ፣ መስከረም 23 ቀን፣ 2006 ዓም ወደ አውሮጳ ለመግባት በሞከሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች ላይ እንደገና ዘግናኝ የመሰመጥ አደጋ ከደረሰ በኋላ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የህብረቱ የስደተኞችና እና የውጭ ዜጎች ጉዳይ ፖሊሲ ሰብዓዊነት

https://p.dw.com/p/19tz8
ምስል Reuters

እንዲታከልበት እና ለስደተኞች ደህንነት ከለላ እንዲሰጥ ለማድረግ በጋራ ጥረት እንዲያደርጉ የየሀገራቱ ፖለቲከኞች እየጠየቁ ነው። የአውሮጳ ህብረት የስደተኞችና እና የውጭ ዜጎች ጉዳይ ተመልካች ኮሚሽን ተጠሪ ወይዘሮ ሴሲልያ ማልምሽትሮም አባል ሀገራት ተጨማሪ ስደተኞችን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበል። የሰብዓዊ መብት ረገጣን እየሸሹ የተሻለ የኑሮ እና የስራ ዕድል ፍለጋ ወደ አውሮጳ መግባት በሚፈልጉት ተስፋ የቆረጡ ስደተኞች ሁኔታ በሚበዘብዙ ሕገ ወጥ አሸጋጋሪዎች አንፃር ህብረቱ ትግሉን ማጠናከር እንደሚገባው የሴሲል ማልሽትሮም ቃል አቀባያቸው ሚሼል ቸርኮኔ አሳስበዋል። « ከዚሁ አሳዛኝ አደጋ እና ከሌሎች አሳዛኝ አደጋዎች በስተጀርባ የሰዎች ተስፋ መቁረጥ ሁኔታን የሚበዘብዙ የወንጀለኛ ቡድኖች መረብ ይገኛል። ገሀዱ ሕገ ወጡ የሰው ማሸጋገር ተግባር ግዙፍ ትርፍ የሚያስገኝ ወንጀል መሆኑ ነው። ስለዚህ በእነዚህ ወንጀለኛ መረቦች አንፃር ትግላችንን ማጠናከር ይኖርብናል።»

Italien Flüchtlingsdrama Lampedusa
ምስል REUTERS

የስደተኞች እና የውጭ ዜጎች መብት ሊከበር እና ወደ አውሮጳ የሚመጡ ስደተኞች በዚያ መቆየት የሚችሉበት ተጨማሪ ሕግ እንዲዘጋጅ ነው የጠየቁት።

መንግሥታዊ ያልሆነው «ፕሮ አዙል» ዋና ስራ አስኪያጅ ጉንተር ቡርክሀርት ግን የአውሮጳ ህብረት የስደተኞችና እና የውጭ ዜጎች ጉዳይ ተመልካች ኮሚሽን ተጠሪን እና ቃል አቀባያቸውን አባባል ላይ እና ፣ በተለይ የድንበሮቻቸውን ቁጥጥር ባጠናከሩት ኢጣልያ፣ ግሪክ፣ ሞልታ እና ቆጵሮስ ላይ ብርቱ ወቀሳ በመሰነዘር ይኸው ፖሊሲያቸው ስደተኞች አደገኛውን የባህር ጉዙ እንደ መጨረሻ አማራጭ እንዲጠቀሙበት አድርጓል ሲሉ ነቅፈዋል።

እንደሚታወሰው አንዲት 500 ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ ከትናንት በስቲያ ወደ ኢጣልያ ደሴት ላምፔዱዛ ልትደርስ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀራት በደረሰባት የቃጠሎ አደጋ ሰጥማለች። በሕገ ወጦቹ አሸጋጋሪዎች የሚንቀሳቀሱት ጀልባዎች ለአደጋ ጊዜ ርዳታ መጥሪያ ስልክ እንኳን ስለሌላቸው ተሳፋሪዎች የጀልባዋ ሞተር ከጠፋ በኋላ ርዳታ ለማግኘት ሲሉ በለኮሱት እሳት ነበር ቃጠሎው የተነሳው። የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ሕይወታቸው ያለፈች ቢያንስ የ130 ስደተኞችን አስከሬን ሲያወጡ፣ በሕይወት የተረፉ 155 አድነዋል። አደጋው እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ነው የነፍስ አድን ቡድኖች ሰራተኞች ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የገለጹት። የኢጣልያ ሀገር አስተዳደር ሚንስትር አጀሊኖ አልፋኖም የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ነው ያስታወቁት።

Cecilia Malmström
ምስል picture-alliance/dpa

« 93 አስከሬኖች ከነዚህም የአራት ሕፃናት እና የሁለት ነፍሰ ጡሮች አስከሬኖችን የያዙ ከረጢቶች ተመልክቼአለሁ። እንዲሁም የብዙ ወንዶች እና ሴቶችም አስከሬኖች ጭምር። የሚያሳዝነው ሌሊቱን እና ነገን የሟቾች ቁጥር ከፍ ማለቱ አይቀርም። »

እአአ በ 2013 ዓም የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ወደ 9000 የሚጠጉ ስደተኞች ኢጣልያ እና ሞልታ ገበተዋል። ይኸው የስደተኞች ቁጥር ከ 2012 ዓም ጋ ሲነፃፀር በእጥፍ ነው የጨመረው። በ2012 ሕይወታቸውን ያጡት ስደተኞች ቁጥር 500 ነበር። በዚችው ከሊቢያ በተነሳችው ጀልባ ውስጥ ከተሳፈሩት እና ከሞቱት መካከል ብዙዎቹ ኤርትራውያን፣ ሶማልያውያን እና የጋና ዜጎች ናቸው። የሞቱት እና የተረፉት ስደተኞች በሀገሮቻቸው ያለውን ክትትል ሸሽተው የወጡ መሆናቸው ሲታሰብ አደጋው እጅግ ዘግናኝ መሆኑን የተመ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት ባልደረባ አድሪያን ኤድዋርድስ ገልጸዋል።

« ከዚሁ አደጋ በስተጀርባ ያለውን አሳዛኝ ታሪከ ማሰብ ተገቢ ይሆናል። ብዙዎቹ ስደተኞች ምናልባት በየሀገሮቻቸው የሚካሄዱ ጦርነቶችን፣ ያረፈባቸውን ክትትል ወይም የሰብዓዊ መብት ረገጣን የሸሹ ሊሆኑ ይችላሉ። እና ይህ አደጋውን እጥፍ ድርብ አሳዛኝ ያደርገዋል። »

Flüchtlinge Einwanderung Griechenland Grenzkontrolle 05.11.2010
ምስል picture-alliance/dpa

በአደጋው እጅግ የተደናገጠችው ኢጣልያ የስደተኞቹን ችግር ለብቻዋ ልትወጣው እንደማትችል አስታውቃለች። የካቶሊካዊቱ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስም ለስደተኞቹ ችግር ደንታ ያለተሰጠበትን ድርጊት በማውገዝ አደጋውን እጅግ አሳፋሪ ብለውታል።

ወደላምፔዱዛ እጅግ ብዙ ስደተኞች የገቡት ከሁለት ዓመት በፊት በዐረባውያት ሀገራት የሕዝብ ዓመፅ በተቀሰቀሰበት ጊዜ ነበር። በዚያን ጊዜ 48,000 ነበሩ ላምፔዱዛ የገቡት። ከነዚሁ ግማሾቹ ከቱኒዝያ ሲሆኑ፣ የተቀሩት ከዐረባውያት ሀገራት ዓብዮት በፊት ወደ ሊቢያ የሄዱ ከሰሀራ በሰተደቡብ ካሉ አፍሪቃውያት ሀገራት፣ ከኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማልያ ስደተኞች ነበሩ። ኢጣልያ ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ሀገርዋ በባህሩ መንገድ እንዳይገቡ ለማከላከል ቀደም ባሉ ዓመታት ከሊቢያ እና ከቱኒዝያ ጋ ሁለቱ አፍሪቃውያት ሀገራት ስደተኞቹን በዚያው እንዲያሰተናግዱ ስምምነት ከደረሰች በኋላ የስደተኞቹ ቁጥር መጀመሪያ ላይ ቢቀንስም ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ እየጨመረ ሄዶዋል።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ