1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የኢትዮጵያ ጉብኝትና አስተያየት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 25 2009

ለአጭር ቀናት ጉብኝት ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ ተጉዘዉ የነበሩት የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዚግማር ጋብሬል ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ፤ ከአፍሪቃ ሕብረት እና ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ከሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተነጋግረዋል።

https://p.dw.com/p/2cJCL
Bundesaussenminister Sigmar Gabriel l SPD trifft Hailemariam Desalegn
ምስል Imago

German FM Sigmar Gabriel met Ethiopian opposition representatives - MP3-Stereo

ለአጭር ቀናት ጉብኝት ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ ተጉዘዉ የነበሩት የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዚግማር ጋብሬል ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ፤ ከአፍሪቃ ሕብረት እና ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ከሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተነጋግረዋል።ሚኒሥትሩ ከባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ዉይይት የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ለውጥ ገቢራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ጥያቄያቸዉ እውን ለመሆኑ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሚ ፖለቲከኞች ጥርጣሬ አላቸው። እሸቴ በቀለ
በእለተ-ማክሰኞ አዲስ አበባ የነበሩት የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዚግማር ጋብሬል ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮችን አነጋግረዋል። የመድረክ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ውይይቱን ጠቅለል ባሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የተለየ አጀንዳም ያልነበረው ሆኖ አግኝተውታል። 

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ያደመጡት ብሶት ዚግማር ጋብሬል ከጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋርም መክረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትሩ ከአቶ ኃይለማርያም ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ብቻቸውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተቃዋሚዎች ከወትሮው የበለጠ አፍኖናል ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ጋብሬል ኢትዮጵያ ለምትሻው የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰትም ቢሆን ቅድሚያ መረጋጋት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

«(የኢትዮጵያ መንግሥት) የአስቸኳይ ጊዜዉን አዋጅ እንዲያነሳና ከሁሉም በላይ ፖለቲካዊ ለዉጥ ለማድረግ የገባዉን ቃል ገቢር እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚንስትሩን በድጋሚ አጥብቀን ጠይቀናል። በተለይ ተገፍተናል የሚል ስሜት ያላቸዉ ወገኖች በፖለቲካዉ የመሳተፍ እንድል እንዲኖራቸዉ የተሐድሶ ለዉጥ ማድረግ አስፈላጊ ነዉ። እርግጥ ነዉ ከዚሕ ቀደም የምጣኔ ሐብት ርዳታ ለማድረግ አስታዉቀናል። ይሁንና መዋዕለ ንዋይ ከዉጪ ወደ ሐገሪቱ የሚፈሰዉ በሐገሪቱ ፍትሐዊ ሥርዓት መኖሩ፤የተረጋጉ ሁኔታዎች መኖራቸዉን ባለሐብቶች ሲያረጋግጡ ነዉ። እዚሕ የመጣነዉም ለዚሕ ነዉ።»
በኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ በኋላ ከፍተኛ የጀርመን ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ጥቅምት መባቻ ወደ ኢትዮጵያ የሄዱት መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልም አገሪቱ በፖለቲካ ምኅዳሯ ለውጥ ያሻታል ሲሉ ወትውተው ነበር። የመንግሥት ባለሥልጣናቱ እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ እንዲህ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ እርዳታ ከሚሰጡ እንግዶቻቸው ጋር ሲገናኙ የሚያወሩት ግን የሚመሳሰል አይመስልም። 

የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ልደቱ አያሌው የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ዚግማር ጋብሬልን መሰል የምዕራቡ ዓለም ሹማምንት ብቅ ሲሉ «የሚጠበቅ» ነገር እንዳለ ይስማማሉ። እንደ አቶ ልደቱ አባባል ሹማምንቱ የሰነዘሯቸው ትችቶች ይኑሩ እንጂ፤ የሚጠበቀውን ያክል ለውጥ አልመጣም። 


እሸቴ በቀለ 
ሸዋዬ ለገሠ