1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉባኤ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2006

«የጀርመንና ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉባኤ » የተሰኘ ውይይት እዚህ ጀርመን ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ባሳለፍነው ሣምንት ተሰናድቶ ነበር። በውይይቱ የኢትዮጵያ እና የጀርመን መንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ ባለሀብቶች እና እንግዶች ተሳትፈዋል።

https://p.dw.com/p/1A4hM
GEECON German Ethiopian Economic Conference 2013. Die deutsch-äthiopische Wirtschaftskonferenz "German Ethiopian Economic Conference" (GEECON) 2013, veranstaltet vom deutsch-äthiopischen Forum e.V. in Zusammenarbeit mit der Kölner Industrie- und Handelskammer. Die zweite Konferenz in diesem Jahr fand am 16. Oktober im Maritim Hotel, Köln statt. Autor/Copyright: DW/Mantegaftot Sileshi Siyoum 2013
ምስል DW/Mantegaftot Sileshi Siyoum

ውይይቱ የተካሄደው ከቦን ብዙም በማትርቀው የኮሎኝ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ማሪቲም ሆቴል፣ መለስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ነበር። በውይይቱ የቦንና የኮሎኝ ከተሞች የሚገኙበት የኖርድ ራይን ቬስትፋሊያ ግዛት ባለስልጣናት፣ በበርሊን የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ከኢትዮጵያ የመንግሥት ተወካዮች፣ እንዲሁም ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። የዛሬው የኢኮኖሚው ዓለም ጥንቅራችን «የጀርመንና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉባኤ» በሚል ርዕስ ባሳለፍነው ሣምንት በኮሎኝ ከተማ የተካሄደውን ውይይት የሚቃኝ ይሆናል።

«የጀርመንና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉባኤ» በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ GEECON በሚል ርዕስ ውይይት ሲካሄድ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በውይይቱ ላይ የጀርመን ባለሀብቶች ኢትዮጵያ በመሄድ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ምን አማራጮች አሏቸው የሚለው ነጥብ በዋናነት ተነስቷል። የጀርመን ባለሀብቶች ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛ የመሆናቸው ጉዳይም ተወስቷል። በበርሊን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሐ አስገዶም።

በጀርመን የኖርድ ራይን ቬስትፋሊያ ግዛት መንግሥት ዋነኛ የውጭ ንግድ ምርቶች መዘውሮች ማለትም ማሽኖች፣ ንጥረ ነገሮች እና የብረታ ብረት ውጤቶች እንደሆኑ በውይይቱ ተጠቅሷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከአፍሪቃ ጋር በሚደረገው የንግድ ልውውጥ የተሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ መለዋወጫ አካላት እንዲሁም የግዙፍ መዘውሮች ፍላጎት እየጨመረ ሄዷል ተብሏል። የጀርመን ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የልማት ፖሊሲ የአፍሪቃ ጉዳይ ሃላፊ ሃይኮ ሽቪደሮቭስኪ በውይይት መድረኩ ላይ ማብራሪያ ካቀረቡ ባለስልጣናት መካከል ይገኙበታል። የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተፈለገውን ያህል አለመሰማራታቸው በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፤ ያ ከምን የመጣ ነው በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ባለስልጣኑ ሲመልሱ።

Äthiopien Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa

«በአንድ ጎኑ አሁንም ድረስ በጀርመን ባለሀብቶች በኩል የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰትን ዘርፈ-ብዙ የማድረግ አዝማሚያ አለ። አማራጮቹ እጅግ በርካታ ናቸው። ኩባንያዎች ወረታቸውን ለማፍሰስ የሚችሉበት ብዙ አማራጮች አላቸው። ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት፣ ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ወይንም ሌሎች አህጉሮች ውስጥ ካሉ ሃገራት ጋር ከፍተኛ ፉክክር ላይ ናት። በእዚያ ላይ ደግሞ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ-ንዋይ ለማፍሰስ መወሰናቸውን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥት የንግድ እንቅስቃሴ ማዕቀፉን የማሻሻል ስኬቱ ላይም ይወሰናል»

ባለስልጣኑ አያይዘውም በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ ለማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰዎች የትምህርት ይዘት እና የመሰረተ-ልማት አውታሮች ጉዳይ መሻሻል ይገባቸዋል ብለዋል። እንዲያም ሆኖ ግን የጀርመን ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ፣ በዘመናዊ መልክ የምግብ አቅርቦቶችን ማምረት፣ ማቀናበር እና ማሸግን የሚመለከተው የአግሮ ኢንዲስትሪ ዘርፍ እንዲሁም በአበባ እርሻ ልማት እንደተሰማሩ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲን ወክለው ንግግር ያደረጉት አቶ አክሊሉ ወልደ ማርያም በበኩላቸው የውጭ ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ እንቅስቃሴዎች መንግስታቸው እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

GEECON German Ethiopian Economic Conference 2013. Die deutsch-äthiopische Wirtschaftskonferenz "German Ethiopian Economic Conference" (GEECON) 2013, veranstaltet vom deutsch-äthiopischen Forum e.V. in Zusammenarbeit mit der Kölner Industrie- und Handelskammer. Die zweite Konferenz in diesem Jahr fand am 16. Oktober im Maritim Hotel, Köln statt. Autor/Copyright: DW/Mantegaftot Sileshi Siyoum 2013
ምስል DW/Mantegaftot Sileshi Siyoum

ጀርመናውያን ባለሀብቶች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ለማድረግ እንዲችሉ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ያሏቸውን ነጥቦች የጀርመን ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የልማት ፖሊሲ የአፍሪቃ ጉዳይ ሃላፊው ሃይኮ ሽቪደሮቭስኪ ያብራራሉ።

«በእርግጥም በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ ለማድረግ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰዎች የትምህርት ይዞታን በተመለከተ ቀደም ሲል ጠቅሰናል። ከእዚያ በተጨማሪ መንገዶችን፣ ወደቦችን፣ የባቡር መስመሮችን በተመለከተ የመሰረተ-ልማት አውታሮች ሊሻሻሉ ይችላሉ ብለን እናስባለን። ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ዞሮ ዞሮ የምርት ወጪው ላይ ተፅዕኖ መፍጠራቸው አይቀርም። ያ ማለት፤ ምርቱን ወደ ጀርመን በመላኩ እና በመሸጡ ስኬት ላይ በከፍተኛ ሁናቴ ተፅዕኖ ሊያርፍበት ይችላል ።»

ጀርመናውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ሲያፈሱ ከሚያተኩሩባቸው ነጥቦች መካከል ነዋሪው ምን ያህል የስራ ዕድል አግኝቷል የሚለው ቀዳሚ እንደሆነ ተጠቅሶዋል። ሃይኮ ሽቪደሮቭስኪ።

«የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቱን ተከትሎ ምን ያህል ስራ መፍጠር ተችሏል የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በጀርመን ባለሀብቶች የተፈጠረው የስራ ዕድል እጅግ በጣም አናሳ ነው። እስካሁን በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠሩ የስራ ዕድሎች ሊፈጠሩ ችለዋል። ከጎረቤት ሃገራት፤ ለአብነት ያህል እንደ ኬንያ ባሉ የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ካለው ሁናቴ አንፃር ሲታይ የበለጠ የስራ ዕድል መፍጠር ይቻል ነበር። በእርግጥ አሁንም ድረስ አቅሙ አለ። እናም በስተመጨረሻ የምንመለከተው የገቢና ወጪ ንግዱ ዝርዝሩን ብቻ አይደለም። የጀርመን ኩባንያዎች ውስጥ በመቀጠር ምን ያህል የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፣ ምን ያህሉንስ ማስተማር ተችሏል የሚለውን ማጤን ይገባናል»

Deutschland Äthiopien GEECON deutsch-äthiopische Wirtschaftskonferenz in Köln
ምስል DW/Mantegaftot Sileshi Siyoum

እጎአ በ2007 የኖርድ ራይን ቬስትፋሊያ ግዛት መንግሥት ከሰሐራ በታች ከሚገኙ ሃገራት ጋር የ 3,2 ቢሊዮን ዩሮ የንግድ ግንኙነት ማከናወኑ በውይይቱ ተገልጿል። ዓለምን የመታት የፈፋይናንስ ቀውስ ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ እጎአ በ2012 የንግድ ግንኙነቱ ከ4 ቢሊዮን ከፍ ማlለቱ ተጠቅሷል። ግንኙነቱ በተለይ ከጋና እና ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከሚገኘው ኩማላንጋ ከተሰኘው አውራጃ ጋር ነው ተብሏል። የሙስና ጉዳይም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል። ሙስናን ከማስወገድ አንስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት የተመቻቸ ነገር አለ ሲሉ ይጠቅሳሉ፤ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ባለስልጣኑ አቶ አክሊሉ ወልደማርያም።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ዘንድሮ ባወጣው ዘገባ ሙስና ተስፋፍቶባቸዋል ካላቸው በርካታ የዓለማችን ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች። በውይይቱ ወቅት አቶ አክሊሉ ወልደማርያም ኢትዮጵያ ለመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ቀዳሚ ትኩረት ከሰጠችባቸው ዘርፎች መካከል የእርሻው ዘርፍ በሁለተኛ ደረጃ እንደሚታይ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጭ ባለሀብቶች በሚሰጥበት ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎች የመፈናቀል አደጋ እንደሚደርስባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾች ሲገልፁ ይደመጣል። አምባሳደር ፍስሐ አስገዶም።

ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የመገናኛ አውታር ኢትዮጵያ ድረስ በመሄድ የመሬት መቀራመትን የተመለከተ ዶክመንታሪ ዘገባ በቪዲዮ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopien
ምስል DW

በኮሎኝ ከተማ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው የጀርመንና የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ውይይትን የተመለከተው ጥንቅር እዚህ ላይ ይጠናቀቃል። ወደፊት በኢኮኖሚው ዓለም እንዲዳሰሱ የምትፈልጓቸው ነጥቦች ካሉ ጠቁሙን፤ አስተያየታችሁንም በኢሜል፣ በደብዳቤ፣ በተለመደው የአጭር መልዕክት መቀበያ ስልካችን በፅሁፍ አለያም በድምፅ መቀበያ ስልካችን ልታኖሩልን ትችላላችሁ።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ከታች የሚገኘውን የድምፅ ማጫወቻ ይጫኑ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ