1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የኢትዮጵያ የልማት ትብብር

ረቡዕ፣ ጥር 11 2003

ጀርመንና ኢትዮጵያ የልማት ትብብራቸውን ይበልጥ ለማስፋፋት እንደሚጥሩ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/QtXi
ምስል picture-alliance / dpa

የሁለቱ መንግሥታት የትብብር ውል ለቀጣይ ዓመታት በሚራዘምበት ሁኔታ በፊታችን በጋ ድርድር እንደሚካሄድም ይጠበቃል። የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ዲርክ ኒብል ከወዲሁ ባለፈው ሣምንት ኢትዮጵያን ጎብኝተው ሲመለሱ ለትብብሩ መጠናከር አመቺ ሁኔታ መኖሩን ነበር ያረጋገጡት። እርግጥ ከመንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋር በየደረጃው በተካሄደው ውይይት አከራካሪ ነጥቦችም መነሳታቸው አልቀረም። የዶቼ ቬለ የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ሃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪይ ትናንት በርሊን ላይ ከሚኒስትሩ ጋር ቃለ-ምልልስ አካሂዶ ነበር።

የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ባለፈው ሣምንት የመንንና ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በሁለቱም አገሮች ዓቢይ መልዕክታቸው በበጎ አስተዳደርና በሰብዓዊ መብቶች ከበሬታ ላይ ያተኮረ ነበር። ዲርክ ኒብል በኢትዮጵያ ባካሄዱት ጉብኝት ጥቂትም ቢሆን በመንግሥቱ ከፍተኛ የራስ መተማመን ዝንባሌ ሳይገረሙ አልቀሩም። በዚሁ አድናቆታቸውንም ነው የገለጹት። በሌላ በኩል ሁኔታው የሁለቱን መንግሥታት ትብብር ከባድ ሊያደርገው አይልም ወይ? ሉድገር ሻዶምስኪይ ለሚኒስትሩ በመጀመሪያ የሰነዘረው ጥያቄ ይሄ ነበር።

“የኢትዮጵያ መንግሥት በብዙ ነገር ሊተች ይችል ይሆናል። በልማት ላይ በግልጽ ለማተኮሩ ግን ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው። ለራሱ አገር ግልጽ የሆነ የልማት ውጥን አለው። ይህ ደግሞ ለትብብራችን ዋናው ቅድመ-ግዴታ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮዤዎችን ወደፊት ለማራመድ የራሱን ገንዘብ ለመጠቀምም ዝግጁ ነው። በሌላ በኩል እርግጥ ራሱ ትክክል ነው የሚለውን ነገር ነው የሚከተለው። ይህን ደግሞ ቅኝ-ገዥ ባለመሆናችን እንደግፈዋለን። የምንሻው በኢትዮጵያ መንግሥት የልማት ፕሮግራምና የልማት ፖለቲካ መርህ መሠረት መተባበሩን ነው”

የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ዲርክ ኒብል እርግጥ አገራቸው ለትብብሩ ታላቅ ክብደት የምትሰጣቸውን ማዕከላዊ ቅድመ-ግዴታዎችን ማንሳታቸውም አልቀረም። ከነዚሁ መካከልም ደጋግመው እንደጠቀሱት የሰብዓዊ መብቶች ከበሬታ፣ በጎ አስተዳደርና የፕሬስ ነጻነትን የመሳሰሉት ይገኙበታል። ኒብል በነዚህ አከራካሪ ጥያቄዎች ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ግልጽ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ያስረዱት። የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ተገናኝተው ሲነጋገሩ ያለፈው ግንቦት አገር-አቀፍ ምርጫ ሁኔታም አንዱ የውይይት ርዕስ ነበር። የመንግሥቱን 99,6 በመቶ ድል የተመለከቱትም እንደሚከተለው ነው።

“በዚህ መሰሉ ውጤት የማልረካ ቢሆንም ነገሩን በንጽጽር ለማየት እፈልጋለሁ። ሙሉ በሙሉ ትክክል ,አልነበረም። ጉዳዩ የሚመለከተው የአቶ መለስ ፓርቲ በፓርላማ ውስጥ ያለውን 99,6 በመቶ መቀመጫ እንጂ የምጫውን ውጤት አይደለም። ከዚህ ሌላ ተቃዋሚው ወገን አርባ በመቶ፤ መንግሥት ደግሞ 60 በመቶ ድምጽ ያገኙባቸው የምርጫ አካባቢዎችም ነበሩ። እናም በተራ የብዙሃን ድምጽ ብልጫ በሚሰራበት የምርጫ ሕግ የተቃዋሚው ወገን ድምጽ ከጠረጴዛ ስር ወድቆ እንዲቀር ነው ያደረገው። እና በመሆኑም እንደ ለዘብተኛ ዴሞክራት ብቻ ሣይሆን እንደ ልማት ሚኒስትርም የድምጹን አንጻራዊ ድርሻ የሚያዳብር የምርጫ ህግን ነው በበኩሌ የምሻው”

ዲርክ ኒብል የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢዎችም ምርጫው የምዕራቡን ዓለም መስፈርትና የዴሞክራሲ መርሆ ያንጸባረቀ እንዳልነበር ማረጋገጣቸውንም አስታውሰዋል። ሚኒስትሩ አያይዘው እንዳሉት ጉዳዩ በኢትዮጵያ መንግሥትና በጀርመን መካከል የሚካሄደው ውይይት አንድ አካል ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው። ጀርመንና ኢትዮጵያ የልማት ትብራቸውን ለቀጣይ ሶሥት ዓመታት ለማራዘም በፊታችን በጋ አዲስ ውል ለማስፈን ለመደራደር ያቅዳሉ።

እናም በድርድሩ የጀርመን መንግሥት የሚያስቀምጣቸው አንዳንድ አዳዲስ ቅድመ-ግዴታዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። የልማት ዕርዳታው ከጀርመን በኩል በውጤት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ነው የሚፈለገው። ይሁን እንጂ የልማት ሚኒስትሩ ዲርክ ኒብል በበጋው ስለሚደረገው የሁለቱ የመንግሥታት ድርድር አሁን ቀድሞው ዝርዝር ለመስጠት አልፈቀዱም።

“እርግጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚካሄደውን ንግግር አሁን ቀድሞ ለማንሳት ምንም ምክንያት የለም። ግን የጉብኝታችን ሂደት በንግግሩ ውስጥ ሊጠቃለሉ የሚችሉ አንዳንድ ግንዛቤዎችን ማስገኘቱ አልቀረም። እኔ የማስበው እንዲህ ዓይነት በልማት ላይ ያተኮረና የራስ መተማመን ያደረበት መንግሥት ይበልጥ ሃላፊነትን ሊወስድ ይችላል ብዬ ነው። ለምሳሌ በተወሰኑ ግቦች ለመስማማት ወይም የተወሰኑ ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን በመዘርዘር ወዘተ. ይህ ደግሞ ከኛ በኩል መንግሥቱን እንደ ዕርዳታ ተቀባይ ሣይሆን እንደ ተባባሪ እንድናይ የሚያደርግ ነው”
በዲርክ ኒብል አባባል እንግዲህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ንግግር የተደረገባቸው ነጥቦች ሁሉ በመጪው መንግሥታዊ ድርድር የሚተኮርባቸው እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነገር ነው። መጪው ድርድር ከተነሣ ከጀርመን በኩል ለሲቪል ሕብረተሰብ ተሃንጾ የሚደረገው ጥሪም ዓቢይ ትኩረት እንደሚሰጠው አንድና ሁለት የለውም።
“አዎን፤ ለውጥ መደረጉ የማይቀር ነገር ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት እርግጥ የኤኮኖሚው ትብብር ይበልጥ እንዲጠናከር ይፈልጋል። በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፍም አንዱ የልማት አካል ሆኖ ነው የሚታየው። እና ለምሳሌ የጀርመን ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ሓዊ ዋስትና በተባበሩት መንግሥታት በጸደቀው ስምምነት መሠረት የሚረጋገጥ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ይህንኑም በሚገባ አስገንዝቤያለሁ”

ኢትዮጵያ ውስጥ ከመንግሥት ነጻ በሆኑ ድርጅቶች ላይ የወጣው ሕግ በአገርና በውጭ ብዙ ትችትን አስከትሎ መቆየቱ ይታወቃል። የሲቪሉን ሕብረተሰብ ተግባር የሚጫን መሆኑን ያስተጋቡት ጥቂቶች አልነበሩም። የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትርም በተለይም ከአገራቸው ሰብዓዊ ድርጅቶች ተግባር አንጻር በሣምንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ጉዳዩን አንስተው መነጋገራቸው አልቀረም።

“ይህ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች መመሪያ ሕግ በተለይም በአገሪቱ የሚገኙትን የጀርመን በጎ አድራጎት ድርጅቶች በማስመልከት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር የተነጋገርንበት አንዱ ትልቅ ጉዳይ ነበር። እዚህ ላይ ጥሩ ዕርምጃ አድርገናል። ጉዳዩ በመጪው መንግሥታዊ ድርድር የምናተኩርበትም ነው። ማንኛውም በጀርመን ፌደራል ም/ቤት የሚወከል ፓርቲ ለራሱ የቀረበ በጎ አድራጎት ድርጅት እንዳለውና በስፍራው የሚገኘው ድርጅት የማንም ሆነ የማ ሁሉም ፖለቲከኞች በኔ የሚኒስትር መሥሪያ ቤት በጀት ላይ የሚወስኑ፤ ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉም መሆናቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ግልጽ ነው ያደረግኩት። ሕጉ በተጨባጭ መልክ ሊስተካከል ይገባዋል”

በሁለቱ መንግሥታት የልማት ትብብር ረገድ የጀርመን ቀጥተኛ የበጀት ዕርዳታ የ 2005-ን አከራካሪ ምርጫ ተከትሎ በርካታ ሲቪሎች ከተገደሉ በኋላ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሣል። ዲርክ ኒብል እንደገለጹት ይሄው እንዲቀጥል ለማድረግም አይታሰብም። ይህ የልማት ሚኒስትሩም ጽኑ ዕምነት ነው።

“ከጀርመን በኩል ወደ በጀት ዕርዳታው የመመለስ ሃሣብ የለም። አጠቃላዩ የጀርመን ፖሊሲ የሚያሳየው እንዲያውም ተቃራኒውን ነው። በመሠረቱ አጠቃላይ የበጀት ዕርዳታን የምናፈቅርም አይደለንም። ይህን ባለበት ቦታ ሁሉ እንዲካሄድ የምናደርገው ቀደም ካሉ መንግሥታት ጭምር የገባነውን ግዴታ ለማሟላት ስንል ነው። በበኩሌ የቅድመ-ግዴታው ካታሎግ እንዲለወጥ አድርጌያለሁ። በተለይም የሰብዓዊ መብት ጥበቃን በተመለከተ በደምብ ክትትል እናደርጋለን። በ 15 ወራት የሥልጣን ጊዜዬ የሰብዓዊ መብት ረገጣንና የበጎ አስተዳደር ጉድለትን በማስመልከት ሶሥቴ ዕርዳታ እንዳይሰጥ ወስኛለሁ”

እንግዲህ የጀርመን መንግሥት የዕርዳታ ወይም የልማት ገንዘቡ ምን ተግባር ላይ እንደሚውል በቅርብ ነው ክትትል የሚያደርገው። በውጤት ላይ የተመሠረተ የዕርዳታ ፖሊሲ የወደፊቱ ጽኑ መርህ የሚሆን ይመስላል።

ያም ሆነ ይህ የጀርመኑ የልማት ሚኒስትር ከተቃዋሚዎች ጋርም ሲገናኙ ተቃዋሚ ድርጅቶች የወደፊት ራዕያቸውን ግልጽ ባለማድረጋቸው ጉድለት ማየታቸው አልቀረም። ሥልጣን መያዝ ብቻውን ግብ ሊሆን እንደማይገባ ነው ያስገነዘቡት።

መሥፍን መኮንን / ሉድገር ሻዶምስኪይ