1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የዩናይትድ እስቴትስ ትኩረት በታዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ፣

ሐሙስ፣ መስከረም 7 2002

የጀርመን ፌደራል መንግሥት የሚንስትሮች ም/ቤት የግንባታ ጉዳይ ሚንስትሩ ቮልፍጋንግ ቲፈንዜ፣ በዛ ያሉ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ አውታሮች ይተከሉ ዘንድ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ መክሮ ውሳኔ አስተላልፏል።

https://p.dw.com/p/JizP
ባህር ላይ የተተከሉ በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ አውታሮች፣ምስል AP

ም/ቤቱ፣ ከጠረፍ ፈንጠር ብሎ በ 12 እና 200 ኪሎሜትሮች መካከል ባህር ላይ በሰሜንና ምሥራቅ ባህር ማለት ነው በነፋስ ኃይል የሚሠሩ ኤሌክትሪክ አመንጪ አውታሮች እንዲተከሉ ነው የወሰነው። ይህን ያደረገበት ምክንያት፣ ዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦችን መተላለፊያ መስመርና የባህር ውስጥ እንስሳትን ኅልውና ጥበቃ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

ሚንስትር ቲፈንዜ እንዳስገነዘቡት ወደፊት አስተማማኝና በቂ የኅይል ምንጭ ለማግኘት እንዲሁም አማራጭ የኅይል ምንጭን ሰፋ ለማድረግ፣ ቅድሚያ መስጠት የሚቻለው በነፋስ ኀይል ለሚሠሩ አውታሮች ነው። በመሆኑም ሚንስሩ ከሰሞኑ ባወጡት አቅድ ላይ እንዳስታወቁት ፣ አገራቸው በሰሜን ባህር ዳርቻ ግዛቷ 1,800 ገደማ ያህል በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አውታሮችን ለመትከል ትሻለች። ለጊዜው 30 በሰሜን ባህር ዳርቻ ፣ 10 ሩ ደግሞ በምሥራቅ ባህር ዳርቻ በሚገኘው ጠረፍ አቅራቢያ እንደሚከተሉ ስምምነት ላይ መደረሱ ኀታወቀ ሆኗል። በዚህ የኃይል ምንጭ ፕሮጀክት አማካኝነት በአጠቃላይ 12 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች የዚሁ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ በነፋስ ኃይል የሚንቀሳቀሱት የኤሌክትሪክ ኃልይ አመንጪ አውታሮች በሚተከሉበት ጊዜ ለ 30,000 ሰዎች አዳዲስ ክፍት የሥራ ቦታ እንደሚገኝም ነው የሚነገረው። በሰሜን ባህርና በምሥራቅ ባህር ከፊሉ ፣ የአውታሮች ተከላ ፣ ሚንስትሩ እንዳሉት እ ጎ አ እስከ 2020 ዓ ም ይከናወናል። ይህም ሲሟላ 12,000 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አያዳግትም። ለጊዜው በዚህ በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የማመንጨት ተግባር የሚሠማሩት Alpha Ventus, EON, EWE እና Vattenfall የተባሉት ኩባንያዎች ናቸው። የፌደራላዊው የኅይል ምንጭ ጉዳይ ድርጅት ፕሬዚዳንት ሄርምን አልበርስ ከተናንስ በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት እ ጎ አ እስከ 2020 ገሚሱን ማለት 50% ን ማሟላት ይቻላል። እርሳቸው እንደሚሉት ፌደራል ክፍላተ-ሀገር ፣በነፋስ ኀይል የሚሠሩ አውታሮችን ለመትከያ የሚሆን ቢያንስ 1% መሬት መመደብ ይጠበቅባቸዋል።

« ደቡቡ፣ በግልጽ ትንሽ ተበልጧል። በከፍተኛ ደረጃ ፣ ለምሳሌም ያህል ለተጠቀሰው እርምጃ 1% መሬት ለማዘጋጀት ከታሰበው በጣም ነው ወደ ኋላ የቀረነው። የክፍላተ ሀገር አስተዳደሮች ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሲባል በዚህ ረገድ ማለትም ከነፋስ የኅይል ምንጭ ማግኘት የሚቻልበትን ተግባር የሙጥኝ ብለው ሊያያዙት ይገባል።»

በዓለም ዙሪያ የአየር ንብረት ለውጥ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ፣ በዛ ያሉ መንግሥታት ፣ ለተፈጥሮ አካባቢ ጠንቅ ባልሆኑ በታዳሽ የኅይል ምንጮች ላይ ማትኮሩን ሳይመርጡ አልቀሩም ። በዚህ ረገድ እስከቅርብ ጊዜ ከየፋብሪካው እየተትጎለጎለ ከከባቢ አየር ጋር የሚቀላቀለው የተቃጠለ አየር መጠን እንዲቀነስ በኪዮቶ ስምምነት የተደገበትን ውል ችላ ብላው የቆየችው ዩናይትድ እስቴትስ ፣ በኦባማ አስተዳደር ዐቢይ ግምት ሳትሰጠው እንዳልቀረች ነው የሚነገረው። አሜሪካ፣ ከጊዜ ወደጊዜ ለታዳሽ የኃይል ምንጭ ትልቅ ግምት በመስጠት የተፈጥሮ አካባቢ ተቋም World Watch እንዳለው፣ አምና ብቻ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ቀደም ሲል ከነበረው፣ በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ አውታሮች መጠን 50% ነው ከፍ እንዲል ያደረች። እናም በአሁኑ ጊዜ፣ 30,000 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በነፋስ ከሚንቀሳቀሱ አውታሮች በማመንጨት 17 ሚሊዮን ያህል ቤቶች፣ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አብቃታለች።

ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር መራኂተ-መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል ወደ ዋሽንግተን ብቅ ብለው ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት የአሜሪካው መሪ ፣ ጀርመን ለተፈጥሮ አካባቢ በሚበጅ የኅይል ምንጭ ላይ ማትኮሯን በመጥቀስ አድናቆታቸውን መግለጠቸው አይዘነጋም። ይሁንን በመሃሉ ዩንይትድ እስቴትስ፣ ከጀርመንም ሆነ ከማንኛውም ሌላ ሀገር በላቀ ሁኔታ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አውታሮችን በመትከልና በመጠቀም በዓለም ውስጥ የአንደኛነቱን ሥፍራ ለመያዝ በቅታለች። አሜሪካ ፣ በረሃ፣ ለጥ ያለ ሜዳ፣ ተራራና እጅግ ሰፊ የባህር ጠረፍ ያላት ሀገር በመሆኗ ፣ የነፋስ ኃይል በሽበሽ ነው። «የነፋስ ቀበቶ» የሚባለው የሆነው ሆኖ፣ በአገሪቱ ማእከል፣ በሰሜን፣ ከሰሜን ዳኮታ አንስቶ እስከ ሜክሲኮ ወሰን ያለው ሲሆን በቴክሳስ ፌደራል ክፍለ-ሀገር ብቻ፣ በነፋስ የሚንቀሳቀሱ፣ የአውታሮች ፉሪቶች 7100 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጩ ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ፣ በአሜሪካ በነፋስ ኃይል የሚገኘው የኤልክትሪክ ጉልበት መጠን የሆነው ሆኖ ከ 2% በታች ነው።

ከነፋስና ከፀሐይ፣ ታዳሽ ኃይል፣ በገፍ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም የነዳጅ ዘይት፣ ጋዝ፣ ድንጋይ ከሰልና የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች ወደ ጎን ይግፋሉ ተብሎ እንደማይታሰብ፣ የአሜሪካ የደንጋይ ከሰል ዋና ሥራ አስኪያጅ ባለሥልጣን አስታውቀዋል። ይህ የኃይል በገፍ የሚገኝ በመሆኑም አሜሪካ በሚመጡት 200 ዓመታትና ከዚያም በላይ በድንጋይ ከሰል መገልገል እንደምትችል ነው የሚነገረው ። ይሁንና የታዳሽ ኃይል ምንጭ ዐቢይ ግምት ማግኘቱ አልቀረም። የታወቁ አሜሪካውያን የኃይል ምንጭ ጉዳይ ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች፤ለነፋስ ኃይል ላቅ ያለ ግምት የሰጡት ይመስላል። የአቶም ኃይል ምንጭ የሚያቀርበው ኩባንያ Duke Energy እስከ መጪው ታኅሳስ ወር ማለቂያ ገደማ በዓለም ውስጥ ከታወቁት 10 በነፋስ የሚሠሩ አውታሮች አምራች ኩባንያዎች መካከል አንደኛው ለመሆን በመጣር ላይ ነው። በነዳጅ ዘይት የከበሩት፣ የቴክሳሱ ቢሊዬኔር T.Boone Pickens ራሳቸው ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት አንስቶ፣ ዩናይትድ እስቴትስ የነዳጅ ዘይት ጥገኛ መሆን የለባትም የሚል ቅሥቀሣ ሲያሰሙ ከርመዋል። እርሳቸው በበኩላቸው፣ በነፋስ ኃይል ኤልክትሪክ በማመንጨት ረገድና በምድር የተፈጥሮ ጋዝ ፣ በሁለቱ ዘርፎች ነው ያተኮሩት።

የባራክ ኦባማ እስተዳደር፣ ለአማራጭ የኃይል ምንጮች ላቅ ያለ ትኩረት የሰጠ ሲሆን ተግባራዊ ይሆን ዘንድም፣ የቀረጥ ቅናሽ በማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ ድጎማ ማቅረቡ አልቀረም። ዩናይትድ እስቴትስ፣ ዘገየ ቢባል እ ጎ አ እስከ 2020 ዓ ም ፣ 20% ታዳሽ የኃይል ምንጭ ከነፋስና ፀሐይ እንዲገኝ ነው እቅዷ። በጀርመን ፣ በአሁኑ ጊዜ መጠኑ 14% መሆኑ ይነገራል። በነፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት በሚቻልበት የአውታሮች ገበያ ጀርመን ካገር ውጪም በሰፊው ገቢ አላት። በሃምበርህግ የሚገኘው «ኖርዴክስ» የተባለው ኩባንያ፣ አሜሪካ ውስጥ ምርቱ እጅግ ተፈላጊ ሆኗል። ኩባንያው ባለፈው ሃምሌ ወር ማለቂያ ገደማ፣ አርካንሶ በተባለው የአሜሪካ ፌደራል ክ/ሀገር፣ በነፋስ ኀይል የሚሠሩ አውታሮች መገጣጠሚያ መገንባት ጀምሯል። EON ቴክሳስ ውስጥ በርከት ያሉ በነፋስ የሚሠሩ አውታሮችን በመተከል ላይ ነው። ከፊሉ ሥራ ጀምሯል። በዚህ ወር ወደ 630 የሚጨጉ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አውታሮች ተተክለው፣ ከ 230,000 በላይ ለሚሆኑ ቤቶች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሰጣሉ። Siemens በበኩሉ፣ ባለፈው ነሐሴ፣ ካንሳስ ግዛት ውስጥ የግንባታ ተግባሩን ጀምሯል። የዩናይትድ እስቴትስ የነፋስ ኅይል ጠቀሜታ ጉዳይ ድርጅት ባልደረባ ኤሊዛቤትዝ ሳሌርኖ እንደሚሉት በዚህ ረገድ ጀርመንውያኑ ጠት አሜሪካ ውስጥ ተፈላጊዎች ናቸው። ጀርመን በታዳሽ የኃይል ምንጭ በተለይም በነፋስ ኃይል ለመጠቀም ምርምር የጀመረችው ከአሜሪካ 10 ዓመት ቀደም ብላ ነው።

በሚመጡት ዓመታትም ለዚህ የኅይል ምንጭ ዘርፍ 40 ቢልዮን ዩውሮ ያህል ገንዘብ ሥራ ላይ ማዋሏ እንደማይቀር ነው የተገለጠው።

ታዳሽ የኀይል ምንጭ የሥነ-ቴክኒኩ ችሎታም ሆነ አቅም ባላቸው አገሮች ብቻ ሳይሆን በሌላቸውም ለተፈጥሮ አካባቢ ካለው አዎንታዊ አኳያ ተቀባይነት ያገኘ ነው።

የጀርመን ጎረቤት፣ ኔደርላንድም ፣ ከጠረፍ 75 ኪሎሜትር ገባ ብሎ ሰሜን ባህር ላይ ከ 30-35 ሜትር ጥልቀት ባለው ሥፍራ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ (በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ አውታሮችን) ለመትከል ማቀዷን ከሁለት ሳምንት በፊት ማስታወቋ የሚታወስ ነው። ከ 20-60 የሚሆኑት አውታሮች ራቅ ብለው ስለሚተከሉ ከጠረፍ ሰው ሊያያቸው አይችልም። ከ 100-300 ሜጋዋት የሚያመነጩት አውታሮች ከ 100,000-300,000 ለሚሆኑ ቤቶች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያቀርባሉ። በ2020(እ ጎ አ)ግን የኔደርላንድ መንግሥት ከተጠቀሰው ሥፍራ 6,000 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ እንዲመነጭ ነው የሚሻው ።

ተክሌ የኋላ፣