1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የፈረንሳይ ስምምነት

ሰኞ፣ ሰኔ 20 2008

ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት ለመዉጣት በሕዝበ ዉሳኔ ካሳለፈች በኋላ የኅብረቱ አባል ሃገራት ቀዉሱን በተመለከተ የሚያደርጉትን ዉይይት እንደቀጠሉ ነዉ።መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንድ ለግማሽ ሰዓት የስልክ ዉይይት ካደረጉ በኋላ በከፍተኛ ደረጃ ግልፅና ጥርጣሪ የሌለበት መፍትሄ ለማግኘት እንደሚገኛኑ ተገልጾአል።

https://p.dw.com/p/1JEbv
Merkel und Hollande treffen sich informell in Straßburg
ምስል picture-alliance/dpa/P. Seeger

ከወደ ፈረንሳይ በተሰማዉ ዘገባ መሠረት ፈረንሳይና ጀርመን ፤ ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት ለመዉጣት ባካሄደችዉ ሕዝበ ዉሳኔ ላይ ያላቸዉ አቋም በጣም የተቀራረበ ነዉ። ብዙዎች የአዉሮጳ ኅብረት ሃገራት ተወካዮች እንጊሊዝ ከኅብረቱ የመዉጫ ማመልከቻዉን በአስቸኳይ እንድታቀርብ ቢጠየቁም የእንጊሊዝ መንግሥት ይህን እንደማያደርግ ነዉ የገለፀዉ።

የጀርመን ፊደራል መንግሥት በበኩሉ እንጊሊዝ የአዉሮጳ ኅብረት መልቀቅያ ማመልከቻን በመጭዉ በልግ ወራት ላይ ታስገባለች ብሎ ይገምታል። የጀርመን መንግስት ቃል አቀባይ ሽቴፈን ዛይበርት ምናልባት በአዲስ የሚመሰረተዉ የለንደን መንግሥት የእንጊሊዝን ከአዉሮጳ የመዉጣት ሂደቶች በይፋ ይጀምራል ሲሉም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ብሪታንያ የገንዘብ ሚኒስትር ጆርጅ ኦስቦርነ ሃገሪቱ ከአዉሮጳ ኅብረት በሕዝበ ዉሳኔ ለመዉጣት ከወሰነች በኋላ የፊናንስ ጉዳይ ፖለቲካዉን ለማረጋጋት መንግሥት ቆርጦ መነሳቱን ገለፁ። እንድያም ሆኖ በገንዘብ ግብይት መድረክ ረዘም ላለ ጊዜ የዋጋ አለመረጋጋት እንደሚከሰት ጆርጅ ኦስቦርነ ለንደን ላይ የግብይት ምንዛሪ ሲጀመር ባደረጉት ንግግር ሳይገልፁ አላለፉም። እንደሚኒስትሩ፤ ሃገራቸዉ የምጣኔ ኃብት ችግሮችን ለመወጣት የሚያስችል ኃይል አላት። ሚኒስትሩ በመቀጠል ፤ ከአዉሮጳ ኅብረት አባልነት የመዉጣቱ ሂደት መጀመርያ፤ ከአዉሮጳ ኅብረት ጋር የሚኖረን የሥራ ግንኙነቶች በምን አይነት መንገድ እንደሆን ግልፅ ሲሆን ነዉ፤ ለአሁኑ ለመጀመርያ የሚቀየር ምንም ነገር የለም ሲሉ መናገራቸዉ ተዘግቦአል። ባለፈዉ አርብ የብሪታንያ ሕዝበ ዉሳኔ መዘርዝር ዉጤት ይፋ እንደሆነ የብሪታንያዉ መገበያያ ገንዘብ ፓዉንድ ዋጋ ከ 31 ዓመት ወዲህ እጅግ ማቆልቆሉ ይታወቃል። ብሪታንያ በኅብረቱ አባልነት እንድትቆይ ፍላጎታችን ነዉ ያለዉ የጃፓን መንግሥት በበኩሉ ፤ በፊናንስ ረገድ ለሚከተለዉ ቀዉስ መዘጋጀቱን ገልጾአል። በጃፓን ካቢኔ ምክትል ፀኃፊ ሂሮሲጌ ሴኮ እንደተናገሩት፤

«አሁን የገበያ አለመረጋጋት አያስፈልገንም፤ መረጋጋት አስፈላጊ ነዉ ብለን እናምናለን። ስለዚህም ግብይይቶችን በትኩረት እያጤንን ነዉ። ስለሚወሰደዉ ሁነኛ ርምጃ ምንም መገለጫን አንሰጥም።»

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ