1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ማኅበራዊ ዋስትና ስጪው ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ 60ኛ ዓመት፣

ዓርብ፣ ሰኔ 13 2000

የጀርመን ማኅበራዊ ዋስትና ስጪው ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ 60ኛ ዓመት፣

https://p.dw.com/p/ENds
ሉድቪኽ ኤርሃርድ፣ምስል AP

ጀርመን ፣ ባለፉት 60 ዓመታት ካስመገበቻቸው ዐበይት ክንውኖች አንዱ ዋስትና ሰጪው ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ የሠመረበት ሁኔታ ነው። «ብልጽግና ለሁሉ» የተሰኘው መፈክርም ሆነ ጽንሰ-ሀሳብ፣ ማኅበራዊ ዋስትናን ከነጻ ገበያ ጋር በማጣመር ሀ ተብሎ የተጀመረው እ ጎ አ ሰኔ 20 ቀን 1948 ዓ ም ሲሆን፣ ዛሬ ልክ 60ኛ ዓመቱን ደፍኖአል። መርኀ-ግብሩ የተጀመረው በምዕራብ ጀርመን ሲሆን፣ በአሁኑ ዘመን የሚገኙ ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት አንዳች ሳንክ ሳያጋጥመው የተከናወነ አልነበረም። የዶቸ ቨለ ባልደረባ Michael Marek ስለጀርመን ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ አጀማመር ያሰናዳውን ሐተታ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ያቀርበዋል።

እ ጎ አ ሰኔ 20 ቀን 1948 ዓ ም፣ የጀርመን የገንዘብ ሸርፍ በአዲስ መዋቅር ሥራ ላይ ዋለ። በተሃድሶ ለውጥ፣ የዚህ አዲስ የገንዘብ ሸርፍ ቀያሽ፣ ያኔ የኤኮኖሚ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት በኋላም መራኄ-መንግሥት ለመሆን የበቁት Ludwig Erhard ነበሩ።

«ባለፉት ጥቂት ቀናት፣ ነፍሳችንም ሥጋችንም ሲጨነቅ ከሰነበተ በኋላ መደበኛውን ዕለታዊ ኑሮ ተያይዘነዋል። የጀርመን ህዝብ፣ ዛሬ፣ በእርጋታና ስሜቱንም ሰብሰብ በማድረግ ወደየሥራ ገበታው አምርቶአል። እንደሚመስለኝ፣ ከውድቀት ተነሰተን እንዴት እዚህ እንደደረስን፣ የነጻነት ስሜት ያልሠረጸባቸው ጥቂቶች ሊኖሩ ይችላሉ።»

ሉድቪኽ ኤርሃርድ «ውድቀት» ያሉትን አስከፊ ወቅት የጀርመን ህዝብ ጦርነቱ ካከተመ በኋላ ቀምሶታል። ብዙ ገንዘብ ቢቆለልም፣ የሚገኘው ሸቀጣ-ሸቀጥ እጅግ ጥቂት ነበር። ጦርነቱ እንዳለቀ፣ ሸቀጣ-ሸቀጥንም ሆነ መባልእትን በገፍ እየሰበሰቡ መደበቅ፣ የድንጋይ ከሰል ጫኝ ባቡሮችን እያስቆሙ መዝረፍ፣ በስውር የገበያ ቦታዎች መገበያየት የተለመደ ነበር። የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት፣ የድንጋይ ከሰል ማዕድናት በግል እንዲያዙ ቢጠይቁና የሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ ሊቀመንበር ኩርት ሹማኸር የከበርቴ ሥርዓት አክትሞለታል ብለው ቢናገሩና ትልቁ ባለኢንዱስትሪ፣ የ ክሩፕ ብረታ-ብረት ኢንዱስትሪ ባለቤት አልፍረድ ክሩፕ የናዚዎችን ፓርቲ ይደግፉ ስለነበር ታሥረው እንደነበረ ቢታወቅም፣ ማኅበራዊ ዋስትና ሰጪው ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ ፈር የያዘው፣ የሸርፍ ተኀድሶ ለውጥ ከተደረገ በኋላ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ሉድቪኽ ኤርሃርድ፣ የሸርፍ ለውጥ በማድረግ ለማኅበራዊ ዋስትና አዘል የኤኮኖሚ ሥርዓት የሚበጅ አንድ እመርታ ነው ያሳዩት። በተጠቀሰው ሥርዓት፣ የፈለጉትን የመግዛት መብት የማስታወቂያ፣ ሙያና የሥራ ቦታ የመምረጥ መብት፣ እንዲሁም የግል ሀብት የማፍራት ነጻነት ተረጋገጠ-----

(4) « በመጀመሪያ፣ እነዚህ ነጻነቶች፣ በነጻ የሙያና የሥራ ቦታ መምረጥ በሚቻልበት መብት ሲገለጡ፣ በተለይም የፈለጉትን የመግዛት ነጻነት ሲኖር፣ የጀርመን ህዝብ የፖለቲካውን አደረጃጀት ለመቀየስና መጻዔ-ዕድሉን ለመወሰን፣ በትጋት ይሳተፋል ብለን እንጠብቃለን»።

በዚህ ለዘብተኛ የኤኮኖሚ ሥርዓት፣ የቀረጥ ግዴታ፣ የማኅበራዊ አገልግሎትና የግል ባለንብረትነት መብት፣ ሁሉም በተዘረጋው ሥርዓት አቅድ እንዲኖራቸው ነበረ የተደረገው። እ ጎ አ ሰኔ 20 ቀን 1948 ዓ ም፣ ገንዘቡ በተሃድሶ እርምጃ ሲለወጥ፣ የናዚ ጀርመን ብድር በሙሉ እንደተሠረዘ ነው የተቆጠረው። የግል ተጠያቂነት፣ የባንክ ና ተቀማጭ ገንዘብ ሁሉም 10-1 ነው ግምት የተሰጠው። በምዕራብ ጀርመን ይኖር የነበረ ዜጋ ሁሉ እያንዳንዱ 40 ማርክ ተሰጠው።

በአንድ ጊዜ እርምጃ፣ ጀርመናውያን ሁሉ በአንድ ጊዜ የጠነጠኑ ሀብታሞች ወይም ያጡ-የነጡ ድሆች የሚሆኑ መሰለ። አዲሱ የገንዘብ ሸርፍ፣ ባለ አክሲዮኖችን የቤት አከራዮችንና ባለኢንዱስትሪዎችን፤ ሲያቅፍ፣ ብዙኀኑ ባዶ እጃቸውን ነበረ የቀሩት። በተለይም በባንክ ገንዘብ ያስቀመጡ ነበሩ የተጎነጡት። መቶው ገንዘባቸው በ 6,5 ነበረ የተቀየረው። የሙያ ማኅበራት እንደጠየቁት ንብረትን የማስተካከል እርምጃ አልተወሰደም። በዚህ ረገድ የኤኮኖሚ ጠበብት እንደሚሉት፣ የአድልዎ ተግባር መፈጸሙ አልቀረም። ያኔ ቢ-ዞን፣ ይባል የነበረው የአስተዳደር ምክር ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ Herrman Pünder-------

«በዕድሜ የገፉ ወገኖቻችንን፣ የማኅበራዊ ዋስትና የሚያገኙ ጡረተኞችን፣ወይም ደግሞ፣ ፍትሽ በጎደለው አሠራር ሳቢያ ከትውልድ ቦታቸው የተፈናቀሉትንና በተመሳሳይ ሁኔታ የኖሩትን፣ በህይወት ዘመናቸው ያጠራቀሟት ገንዘብ አሁን በሰፊው የሚቀረጥባቸውን አስባቸዋለሁ። ስለሆነም፣ የያኔው የሸርፍ ተሃድሶ ለውጥ፣ የደመሰሰው፣ ያቃወሰው የማይጨበጥ ህልምን እንጂ፣ የትክክለኛውን ንብረት ዋጋ አልነበረም»

የሸርፍ ተሃድሶ ለውጥ ከተደረገ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሱቆች ሁሉ ባዶአቸውን ነበረ የቀሩት። የሸቀጣ-ሸቀጡ ዋጋ እጅግ ናረ። ፕረሱና ፖለቲከኞች የነጻ ገበያው ልምምድ ይብቃ!እያሉ እስከመናገር ደርሰው ነበር። 9 ሚልዮን ያህል ሠራተኞች እ ጎ አ በኅዳር ወር 1948 ዓ ም፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ፣ በጀርመን ታሪክ የመጀመሪያውን ዐቢይ የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር። ይሁንና፣ የያኔው የሸርፍ ለውጥ፣ ሳይውል ሳያድር፣ ለጀርመን የኤኮኖሚ ተዓምር የተሰኘውን አስደናቂ ዕድገት ነበረ ያስገኘላት።