1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ምርጫ

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2009

የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ሊካሄድ ከ8 ወራት ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው ። ዋና ዋናዎቹ የጀርመን ፓርቲዎችም ከወዲሁ በየአቅጣጫው ለምርጫው ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው ። ከመካከላቸው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ለመራሄ መንግሥትነት የሚወዳደር አዲስ እጩ እና ሊቀመንበር ሰይሟል ። አዲሱ ተፎካካሪ በመጪው ምርጫ ምን ዓይነት ተፅእኖ ሊያሳድር ይችላል ?

https://p.dw.com/p/2Wha4
Martin Schulz
ምስል Reuters/H. Hanschke

የጀርመን ምርጫ እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ

 የአዲሱ ተፎካካሪ ብቃትስ እንዴት ይመዘናል ? ዋና ዋናዎቹ ፓርቲዎች የሚጠብቋቸው ተግዳሮቶችስ ምን ይሆናሉ ?በዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን የምናተኩርባቸው ጉዳዮች ናቸው ።እስካለፈው ሳምንት ድረስ፣ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶችን ፓርቲ በመወከል ለመራሄ መንግሥትነት ይወዳደራሉ ተብለው የተጠበቁት የፓርቲው ሊቀመንበር እና የኤኮኖሚ ሚኒስትር ዚግማር ገብርየል ነበሩ ። ሆኖም ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለመራሄ መንግሥትነት እንደማይወዳደሩ፣ከፓርቲያቸው መሪነትም እንደሚነሱ አስታውቀዋል። እነዚህን ሃላፊነቶችም የቀድሞው የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ማርቲን ሹልትስ እንዲረከቡ ባቀረቡት ሀሳብ መሠረት ፣ሹልትስ የፓርቲው መሪ እና እጩ መራሄ መንግሥት ሆነው ከትናንት በስተያ በይፋ ተሰይመዋል ። እነዚህ ሃላፊነቶች የተሰጧቸው ሹልትስ ባሰሙት ንግግር ዋነኛ ትኩረታቸው ሠራተኛው ህዝብ እንደሚሆን ቃል ገብተዋል ።
«ለኔ ትልቁ ነገር እና የፖሊሲያችንም ትኩረት ደንቦችን የሚያከብረው ፣ልጆቹን እና አዘውትሮም ወላጆቹን የሚንከባከበው ፣ ከሁለት ወገን ገቢ ቢያገኝም ኑሮ በአብዛኛው የማይሳከለት የዚህች አገር ጠንካራ ሠራተኛ ህዝብ እና ጭንቀቶቹ ናቸው ። ለዚህም ነው ለዚህች ሀገር መራሄ መንግሥትነት የምወዳደረው።»
በሹልትስ የተተኩት ጋብርየል እጩ መራሄ መንግሥትነቱን የተዉት ከተቀናቃኛቸው ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲዋ እጩ አንጌላ ሜርክል ጋር የመፎከከር አቅም እንደሌላቸው በመግለፅ ነበር ።እኔ ብወዳደር ፓርቲው ሽንፈት ሊገጥመው ይችላል በሚል ስጋት ከውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉት ጋብርየል ወሳኝ ባሉት ምርጫ ተወዳዳሪ ሆነው እንደማይቀርቡ ባሳወቁበት ወቅት በህዝብ አሰተያየት መመዘኛ  መሠረት ፓርቲያቸው የያገኘው  ድጋፍ ተቀናቃኙ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ ከነበረው ድጋፍ በእጅጉ ያነሰ ነበር ። SPD አዲሱን ዓመት የተቀበለው ከተፎካካሪው ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በምህጻሩ CDU 15 በመቶ ያነሰ ድጋፍ ይዞ ነው ። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው የህዝብ ድጋፍ መቀነስ ፓርቲው መሪውን እና ለመራሄ መንግሥትነት የሚያቀርበውን እጩ ለመለወጥ ያስገደደው ዋነኛው ምክንያት ነው ። ይህ እርምጃም በጥቂት ቀናት ውስጥ ውጤት አስገኝቷል እንደ ይልማ ።ቢልድ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ በጎርጎሮሳዊው 2017 መጀመሪያ ላይ «ዛሬ በጀርመን ምርጫ ቢካሄድ ከሜርክል እና ከሹልትስ ማንን ትመርጣላቸው» ብሎ አስቀድሞ ባሰባሰበው የህዝብ አሰተያየት መመዘኛ ሜርክልን 39 በመቶው ሹልትስን ደግሞ 38 በመቶው መደገፋቸው ተዘግቧል ። ሹልትስ ጋብርየልን ከተኩ በኋላ ደግሞ የፓርቲው የህዝብ ድጋፍ ይበልጥ ከፍ ብሏል ። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንዳለው በአስተያየት መመዘኛዎቹ መሠረት አሁን ህዝቡ ለሁለቱ ተፎካካሪዎች የሚሰጠው ድጋፍ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሹልትስ ጋብርየልን ከተኩ በኋላ ፓርቲው ከህዝቡ የሚያገኘው ድጋፍ እየጨመረ የመጣው በተለያዩ ምክንያቶች ነው ። በዋነኛነት ከሚጠቀሱት መካከል ከዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል መውጣታቸው እና ፣ በጀርመን ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን አደርጋለሁ ማለታቸው ነው ። የ61 ዓመቱ ሹልትስ በእጩ መራሄ መንግሥትነት የሚወዳደሩበት የአሁኑ የጀርመን ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ እንደሚሆን በሰፊው ተገምቷል ። በቀድሞው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ኤስ.ፔ.ዴ መሪ በዚግማር ጋብርየል እምነት መጪው ምርጫው ካለፉት ምርጫዎች የተለየ ነው የሚሆነው ። ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲዋ አንጌላ ሜርክል የመስከረሙ ምርጫ ከከዚህ ቀደሞቹ እጅግ ከባድ እንደሚሆን ነው የተናገሩት ።የሜርክል ፓርቲ ባለፉት ጊዜያት በተካሄዱ የአካባቢ እና የክፍላተ ሀገር ምርጫዎች አሸማቃቂ ሽንፈቶች ገጥመውታል ። ከተመሠረተ 4 ዓመት እንኳን ያልሞላው «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ በመጪው ምርጫ ከዚህ ቀደም ለአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ይሰጥ የነበረው ድምጽ እንዲቀንስ ያደርጋል የሚል ግምት አለ ።ፓርቲው በምርጫው ሊያገኝ የሚችለው ድምጽ  ከ10 እስከ 20 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ይነገራል ። ይህ እና ሌሎችም ዓለም ዓቀፍ እና አውሮጳ ነክ ጉዳዮች ከ8 ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚካሄደውን የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ልዩ ያደርገዋል ይላል ይልማ ኃይለ ሚካኤል ።ባለፉት 22 ዓመታት የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት አባል እና በመጨረሻዎቹ 5 ዓመታት ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ሹልትስ ከሁለት ወር በፊት ከአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ሲሰናበቱ ለፓርቲያቸው ለኤስ ፔዴ በእጩ መራሄ መንግሥትነት ተወዳዳሪ ሆነው ሊቀርቡ ነው ሲባል አስተባብለው ነበር ። በዚህ የተነሳም ባለፈው ሳምንት እጩነቱን መቀበላቸው አስገርሟል ። ሹልትስ በመጪው ምርጫ የሚወዳደሩት ፓርቲያቸውን በሀገሪቱ ትልቅ ኃይል ያለው ፓርቲ ለማድረግ እና ሀገራቸውን በመራሄ መንግሥትነትም ለመምራት መሆኑን አስታውቀዋል ። በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን  አስተያየት ሹልትስ ለፓርቲያቸው ማንሰራራት ብቸኛው እድል ናቸው ።  ይሳካላቸው ይሆን ? አብረን የምናየው ይሆናል ።

EU-Gipfel Brüssel Januar 2012 Martin Schulz Angela Merkel
ምስል dapd
Deutschland Martin Schulz bei der SPD Bundestagfraktion
ምስል picture alliance/dpa/K. Nietfeld

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሃመድ