1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ቀኝ ፅንፈኞች ዘመቻ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2007

ጀርመን ውስጥ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የውጭ ዜጎች ጥላቻ ዘንድሮ እየጨመረ መሄዱ ማነጋገሩ ቀጥሏል ። ከዚሁ ጋር ለውጭ ዜጎች መብቶች የሚቆሙ ፖለቲከኞችም የግድያ ዛቻ ሰለባ መሆናቸው ማሳሰቡ አልቀረም ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።

https://p.dw.com/p/1F8Tp
Brand in zukünftiger Asylbewerberunterkunft
ምስል picture-alliance/dpa/Hendrik Schmidt

በአንዳንድ የጀርመን ከተሞች የውጭ ዜጎች ጥላቻ በየአጋጣሚው የሚታይ ክስተት ነው ። የውጭ ዜጎች በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከሚደርስባቸው አድልዎ ና መገለል በተጨማሪ የተለያዩ ጥቃቶችም ይፈጸሙባቸዋል ። በዚህ ረገድ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተባብሰው የቀጠሉትን በተገን ጠያቂዎች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መጥቀስ ይቻላል ። አራተኛ ወሩ በተጋመሰው እጎአ በ2015ና ከዚያም በቀደመው በ2014 ዓም ጦርነትና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከተባባሰባቸው የዓለም ክፍሎች የመጡ በርካታ ተገን ጠያቂዎች አውሮፓ ገብተዋል ። ከነዚህ ስደተኞች የተወሰኑትን ካስጠጉት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት አንዷ ጀርመን ናት ። እነዚህ ተገን ጠያቂዎች ግን በአንዳንድ የጀርመን ግዛቶች ህዝቡ እጁን ዘርግቶ አልተቀበላቸውም ። በአንዳንድ አካባቢዎች በተጠለሉባቸውና ለወደፊት መኖሪያቸው እንዲሆን በታሰቡ ቤቶች ላይ አደጋ እየተጣለ ነው ። ትረግሊትስ በተባለችው በምሥራቅ ጀርመንዋ የዛክሰን አንሃልት ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ በምትገኘው አነስተኛ ከተማ ለስደተኞች መጠለያ በተዘጋጀ ህንፃ ላይ የደረሰው የቅርብ ጊዜው የእሳት አደጋ ከጥቃቶቹ አንዱ ነው ። አቃቤ ህግ የርግ ቪልክማን ስለ አደጋው በሰጡት መግለጫ እሳቱ ሆነ ተብሎ መለኮሱን የሚጠቁም መረጃ ነበር የሰጡት ።
«እስካሁን በተደረገው ማጣራት እንደተደረሰበት አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ወደ ቤቱ በመግባት እሳቱን ለኩሰዋል።በአመዛኙ የሚመስለው እሳቱን በፍጥነት የሚያቀጣጥል ቁሳቁስ ተጠቅመዋል።»
በመጪው ግንቦት ስደተኞች እንዲገቡበት ታቅዶ የነበረውን ይህን ህንፃ ያጋዩት ሰዎች ማንነት እስካሁን አልልታወቀም ። የፌደራል ክፍለ ሃገሩ ፖለቲከኞች ይህ አሳፋሪ ጥቃት ያሳደረባቸውን ስሜት ሲገልፁ ነበር ። ትረግሊስ የምትገኝበት የዛክሰን አንሃልት ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ራይነር ሃዝልሆፍ ከጥቃቱ በኋላ የሰጡት መግለጫ በስፍራው የተፈፀመው ጥቃት የግዛቲቱ አስተዳደር ሰብዓዊ ግዴታውን ከመወጣት ወደ ኋላ እንዲል እንደማያደርገው ነበር ያሳወቁት ።« እኛ ጋ ጥገኝነት የጠየቁ ሰዎችን የመርዳት ሰብዓዊ ግዴታ አለብን ። ምንም ዓይነት መዘዝ ይኑረው ከልባችን ያመንበት ጉዳይ ስለሆነ እንደርገዋለን ። ይህ መንገዳችንን ለማደናቀፍ ዛሬ ማታ በሞከሩት ወንጀለኞች ተግባር ከሥራችን አንዘናጋም ።»
ሰሞኑን ዓብይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ የዘለቀው የትረግሊትሱ ጥቃት ይሁን እንጂ ከ4 ወር በፊት « ፎራ » በተባለው ኑርንበርግ አቅራቢያ በሚገኘው የደቡብ ጀርመን ከተማ የሚገኝ የስደተኞች መጠለያ በእሳት ተያይዟል ። ሰሜን ጀርመን ሃምቡርግ አቅራቢያ ባለው Escheburg ኤሸቡርግ ፣በደቡባዊ ጀርመን ሙኒክ አጠገብ በሚገኘው Germering ጌርመሪንግ እንዲሁም በምሥራቅ ጀርመኑ ፌደራዊ ግዛት በሜክለንቡርግ ፎርፖመርኑ Sanitz ሳኒትስ እና በዋና ከተማይቱ በበርሊንም ተመሳሳይ የእሳት ቃጠሎዎች ደርሰዋል ። 2700 ነዋሪዎች ያሏት የትረግሊትስ ከተማ ባለሥልጣናት 40 ያህል ለሚሆኑ ስደተኞች መኖሪያ የመሥራት እቅድ እንዳላቸው ከማሳወቃቸው በፊት ከተማዋ በሰላማዊነትዋ የምትታወቅ ከተማ ነበረች ። በከተማይቱ የውጭ ዜጎች ቁጥር ሲሰላ አንድ ከመቶ ብቻ በሆነባት ትረግሊትስ ስደተኞችን እንድትቀበል የተጠየቀችው ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ። ጥያቄውን በመቀበል የከተማይቱ ባለሥልጣናት ስደተኞቹን ለመቀበል ዝግጅት ሲጀምሩ «ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ» የሚል መርህ የሚከተለው NPD የተባለው ቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማይቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አደራጅቶ የስደተኞች መጠለያ መሰራቱን የሚቃወሙ ሰልፎች በየሳምንቱ ይካሄድ ጀመር ።በኋላም በመጋቢት ወር ውስጥ ተቃዋሚዎች በከንቲባው ቤት አቅራቢያ ያቀዱት ሰልፍ እንዲታገድ ከንቲባው ማርኩስ ኒርት(NIERTH) ቢጠይቁም ሰሚ ባለማግኘታቸውበፈቃዳቸው ሥራቸው ለቀዋል ። ከዚያ በፊት ከንቲባው ከተማዋ ስደተኞች እንድትቀበል በመስማማታቸው በርሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ የግድያ ዛቻ ተሰንዝሮባቸዋል ። ከዚያ በኋላ ነበር በዚህች ከተማ ለስደተኞች የተዘጋጀው ህንፃ በእሳት እንዲጋይ የተደረገው ። ከአደጋው በኋላ የቀድሞው ከንቲባ በሰጡት አስተያየት የችግሩ መፍትሄ በነዋሪው እጅ ውስጥ ያለ መሆኑን ነበር የተናገሩት።
«ሁኔታው አስከፊ ነው ። እዚህ ለሚኖሩት ሰዎች በጣም አዝናለሁ ። በዚህ አካባቢ ከዚህ ቀደም ከነበረው የከፋ እኩይ ሁኔታ እያጋጠመ ነው ።ግን ይህን አስከፊ ሁኔታ ማስወገድ የሚችሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው ። ማክሸፍ የሚችሉትም የዚሁ አካባቢ ሰዎች ናቸው ። ይህን ማስወገድ የሚችሉት ከምንም በላይ ድርጊቱን በመቃወም እርምጃ እንወስዳለን ለስደተኞቹም እንቆማለን ብለው ሲነሱ ነው። »
ሌሎች የጀርመን ፖለቲከኞችም ይህን መሰሉ ዛቻ ከቀኝ አክራሪዎች እየተሰነዘረባቸው ነው ። ዛቻው የሚደርሳቸውም በፖስታ በኢሜልና በፌስቡክ መሆኑ ተነግሯል ።ማዕከላዊ ጀርመን የምትገኘው የቱሪንገን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ቦዶ ራመሎቭ ይህ እጣ ከገጠማቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው ። ራመሎቭ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ 3 ጊዜ የግድያ ዛቻ ደርሶዋቸዋል ።ዛቻው ግን ምንም ዓይነት ተፅእኖ ሊያሳድርባቸው እንደማይችል ነው የተናገሩት ። ከዚሁ ጋር የተረግሊትሱ ከንቲባ ስለ ሚገኙበት ሁኔታም አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር ።
«ትንሽ ራሴን ላረጋጋና ልናገር ይህ ዛቻ በቀጥታ እኔን የሚመለከት አይደለም ። አሁንም ከስደተኞቹ ጎን እቆማለሁ ።እናም የተሰነዘረውን ዛቻ ከቁብም አልቆጥረውም ። የትረግሊትሱ ከንቲባ ከስራቸው በፈቃዳቸው የተሰናበቱት የሚደግፋቸው ስላጡ ነው ። የከተማይቱ ምክር ቤት በአሁኑ ጊዜ በፖሊስ ጥበቃ ስር ነው ።»
ከራመሎቭ ሌላ በዛክሰን አንሃልት ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ የምትገኘዋ የማግድቡርግ ከተማ ከንቲባ ሉትስ ትሩምፐርም ለሳምንታት በፖሊስ ጥበቃ ስር ነው ያሉት ።የጀርመን ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲው ትሩምፐር በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የናዚ አርማ የሰፈረባቸው ሥስት የዛቻ ደብዳቤዎች ደርሰዋቸዋል ።ከንቲባ ትሩምፐር እንደተናገሩት ይህ እስከዛሬ ገጥሟቸው የማያውቅ ነገር ነው ። «እንደዚህ ያለ ነገር ሲያጋጥመኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ። እንደሚመስለኝ ይህ ሁኔታ አሁን በተጀመረው የፔጊዳና ና በስደተኞችና በእስልምና ላይ ከሚካሄደው እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው ።በአሁኑ ጊዜ ይህ ሁኔታ በምስራቅ ጀርመንና በትላልቅ ከተሞች ተዘውትሮ የሚታይ ሆኗል ።በየጎዳናው የሚሰማው የጥላቻ ቅስቀሳ ሁሉ በጥሞና ሲያስቡብት በእያንዳንዱ ስደተኛ ላይ ምን ያህል ጥላቻ እንዳለ የሚያመላክት ነው ። »
የግድያ ዛቻ የተሰነዘረባቸው ትሩምፐር የደረሷቸውን ደብዳቤዎች በሙሉ ለፖሊስ ሰጥተዋል ። የደብዳቤዎቹ ፀሃፊም ተደርሶበት ምርመራ እየተካሄደበት ነው ።ትሩምፐር እንዳሉት ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት በቅጡ ተመዝግቦ ሊቀመጥና ህዝብም እንዲያውቀው ሊደረግ ይገባል ።
«ጉዳዩ እስከመጨረሻው ድረስ በደንብ እንዲመዘገብና ህዝቡም በቅጡ እንዲከታተለው ይደረጋል ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ ። ምክንያቱም እንደ ማህበረሰብ ይህን መታገስ አንችልም ።ማንነታቸው ካልታወቀ ሰዎች በኩል በኢንተርኔት የጥላቻ ቅስቀሳ ማካሄድ መቻሉ በፖለቲከኞች ላይ የሚሰነዘረው የግድያ ዛቻ ከፍ እንዲል አድርጓል ።ከዚያ ጋር ተያይዞ የፍርሃት ድባብ ሰፍኗል ።»
ከአፍቃሪ ናዚዎች በኩል የሚላኩት አሁንም ያልቆሙት የማስፈራሪያ ደብዳቤዎች አዲስ አይደሉም ቀድሞም ያሉ ናቸው ።እነዚህ ዛቻዎች ቢኖሩም የመብት ተሟጋቾች ከ20 ዓመት በፊት አንስቶ ከምሥራቅ ጀርመን ትላልቅ ከተሞች ውጭ ባሉ አካባቢዎች ከስደተኞች ጎን ከመቆም ወደ ኋላ ያሉበት ጊዜ የለም ። አማዱ አንቶንዮ የተባለው ቀኝ ፅንፈኞችን የሚቃወም ተቋም ባልደረባ አኔታ ካነ ሁኔታውን ሲነፃጽሩት በፖለቲከኞች ላይ የሚሰነዘረው ዛቻ ጠባቂ ከሌላቸው ስደተኞች ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በጣም አሳሳቢ ሆኖ አይታያቸውም ።
«ለፖለቲከኞቹ ይዞታ ያን ያህል አያሳስበኝም ። አንድ ሰው ራሱንና ቤተሰቡን መጠበቅ የሚችልበት ሁኔታ እስካለ ድረስ ይህ ፖለቲካ ነው ። »
ካነ ፖለቲከኞቹ የሚደረግላቸውን ጥበቃ በየቀኑ ተቀጣጣይ እሳት ጫሪ ቤንዚን የተሞሉ ጠርሙሶች ይዘው በሚኖሩባቸው ቤቶች መስኮቶች ፊት ለፊት ቆመው ቀኝ አክራሪዎች ከሚጠብቋቸው ስደተኞች ሁኔታ ጋር ነው የሚያነፃፅሩት ።እርሳቸው እንደሚሉት እነዚህ ስደተኞች በየምሽቱ ሊደርስባቸው ከሚችል አደጋ ስጋት ጋር ነው የሚኖሩት ። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በስጋት መኖር ምን ማለት ነው ሲሉም ይጠይቃሉ ። የማግድቡርጉ ከንቲባ በበኩላቸው የሚደረግላቸው የፖሊስ ጥበቃ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አረጋግቷቸዋል ።ይህን መሰሉ ጥበቃ ግን ለሁሉም ማድረግ እንደማይችሉ ነው የተናገሩት።
«ለእያንዳንዱ ከንቲባም ሆነ የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ የፖሊስ ጥበቃ እንዲሰጥ ማድረግ አልችልም ።ይህ ወደፊት የምንታገሰው ሁኔታ አይሆንም ። ፍላጎቴ አጠቃላዩ ማህበረሰብ ይህን የጥላቻ ቅስቀሳና ዛቻ እንደማይቀበል እንዲያሳይ ነው ።»
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጀርመን ተጠናክሮ የቀጠለው ቀኝ አክራሪዎች በፖለቲከኞች ላይ የሚሰነዝሩት የግድያ ዛቻና መፍትሄው አሁንም ማነጋገሩ ቀጥሏል ።

Deutschland Dessau Kundgebung Neonazis
ምስል picture-alliance/dpa/J. Woitas
Markus Nierth
ምስል picture-alliance/L. Schulze
Brand in zukünftiger Asylbewerberunterkunft in Tröglitz
ምስል picture-alliance/dpa/H. Schmidt
Reiner Haseloff CDU Sachsen-Anhalt Tröglitz
ምስል picture alliance/dpa/Hendrik Schmidt

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ