1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ንግድ በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ መስከረም 23 2005

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደገ ነው ተብሎ ከሚነገርላቸው ሀገራት አንዷ ናት። ሆኖም ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ መናር የሀገሬው ህዝብ በኢትኆጵያ መንግስት ከሚወደሰው የሁለት አሐዝ እድገት ያገኘውን ጥቅም አጠራጣሪ አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/16JRT
ምስል Getty Images

ምስስራቅ አፍሪቃን የተሻለ በማረጋጋት በተለይም በምዕራብ መንግስታት የምትወደሰው ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በመሳብ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ውስጥ መዋለ ነዋያቸውን ከሚሰሩ የውጭ ባለሐብቶች ጀርመኖች ይገኙበታል።

ኢትዮጵያና ጀርመን ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የዳበረ ግንኙነት ቢኖራቸውም የጀርመን ባለህብቶች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያላቸው ድርሻ የወዳኝነታቸውን እድሜ አይመጥንም። የጀርመን መዋለ ነዋይ አፍሳሾች በልበ ሙሉነት በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የተጠበቀውን ያክል አልተሳተፉም። በኢትዮጵያ ያሉ አብዛኞቹ የጀርመን ኩባኒያዎች የተሰማሩት በንግዱ ዘርፍ ነው። እንደ GIZ ያሉ የጀርመን የእርዳታ ድርጅቶች ብዙ የፕሮጀክት ሥራዎችንና የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፈዋል። አሁን በኢትዮጵያ ያለው የገበያ ሁኔታ ለጀርመን ባለሀብቶች በየትኛው የንግድ ዘርፍ ሰፊ እድል ሊሰጥ እንደሚችል በጀርመን አፍሪካ ንግድ ማሕበር የምስራቅ አፍሪቃ ተጠሪ ወዘሮ አስማሁ ናታርዲ ይናገራሉ፣

«ኢትዮጵያ ያሉትን ጥሬ እቃዎች በመጠቀም እዚያዊ በፋብሪካ የሚመረቱ ምርት ማምረት ለሚፈልጉ የጀርመን ኩባኒያዎች የኢትዮጵያ ገብያ ምቹ ነው ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጥሬ እቃዎች አሉና። እንዲህ በማድረግ ምርቶቹ ያላቸውን ዋጋ ከፍ አድርገው ለሀገር ገበያና ለውጭ ንግድ ማምረት ይችላሉ።»

አካዚስ የጀርመን ኩባኒያ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጥሬ እቃ በመጠቀም ለሀገሪቷ ገበያ ውስጥ እየተሳተፈ ነው። ከሐረር ብዙም በማይርቅ ቦታ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ በማቋቋም ለሀገር ውስጥ ገበያ የምግብ ምርት ለማቅረብ እየሰራ እንያለ ከጥቂት ወራት በፊት ካፒታል ጋዜጣ ዘግቦ ነበር። ከሰማኒያ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሚኖርባት ኢትዮጵያ እንደ ዜይት በሀገር ውስጥ ላለ ገበያ ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ምርቶች የጀርመን ባለሐብቶችን ፍላጎት ልስብ ይችላል።

የጀርመን ባለሐብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ በርካታ እንቅፋቶች ምክንያት ሆነዋል። የውጭ ምንዛሬ ችግር፣ የገበያ ክፍት አለመሆንና የአደረጃጀት ችግር ዋናዎች ናቸው። የውጭ ምንዛሬ ችግር የጀርመን ባለሐብቶች ዋስትና እንዳይኖራቸው ምክንያት ሆኗል ይላሉ ወይዘሮ አስማሁ ናታርዲ፣

« አብዛኞቹ ስለውጭ ምንዛሬ ዋጋ መዋዠቅ ያጉረመርማሉ። ያም ማለት ንግድ መጀመር ቢፈልጉም ምርቶቻቸው እንደ ዶላርና ዩሮ ባሉ የውጭ ገንዘቦች መሸጥ ስለመቻለቸው እርገጠኞች አይደሉም። ገቢያ ውስጥ ካሉና ገቢያውን መቀላቀል ከሚፈልጉ ነገር ግን እርግጠኞች ካልሆኑ የጀርመን ኩባኒያዎች የሚሰማ ዋናው ችግር ይህ ነው።»

የውጭ ምንዛሬ መዋዠቅ የኢትዮጵያን ገበያ ሙሉ በሙሉየተቀላቀሉና መቀላቀል የሚፈልጉ ለጀርመን ኩባኒያዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ ከሆነ መፍትሔው ምን መሆን ይችላል። ወይዘሮ አስማሁ እንዲህ ይላሉ

«ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ እያለኩ ያሉ ኩባኒያዎች ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ነው። ትርፍም ቢሆን እያገኙ ነው። እኛም ሌሎች የጀርመን ኩባኒያዎችን የምንመክረው ኢትዮጲያ ውስጥ መጥተው ስራ እንዲጀመሩና ምርቶቸውን ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ነው።»

ከውጭ ምንዛሬ መዋዠቅም ባሻገር የኢትዮጵያ ገበያ ነጻ አለመሆን ሌላ ችግር ነው። አንዳንድ የንግድ ዘርፎች በመንግስት ብቻ የሚካሄዱ ሲሆኑ በአንዳንዶቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብቻ እንዲሰሩ ይፈቀዳል። የውጭ ባለሐብቶች በሁሉም ዘርፍ ውስጥ ገብተው የመስራት እድላቸው ሰፋ ያለ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ኩባኒያዎች ችግር አጋጥሟቸው ወደሚመለከተው አካል ሲሄዱ ተገቢውን ምላሽ ፈጥነው አያገኙም። መረጃን ና ውሳኔን የመስጠት ኃላፊነት ያለው ሰው ወይ አካል በግልጽ አለመታወቅም ሌላው ችግር ነው።

በውጭ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ያላት ገጽታዋ የጀርመን ባለሐብቶች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ መሳተፍ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካ በመላ በረሃብና በድህነትና በጦርነት ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል። የአፍሪካ ጀርመን ማህበር ይህንን በዓለም ሚዲያ የተፈጠረውን የዓለም ገጽታ ለመቀየር እየሰራ ነው፣

«ይህ መጥፎ ገጽታ የንግድ እንቅስቃሴዎቹ ላይ ተጽዕኖ እያደረገ ነው። ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ አያውቁም። ኢትዮጵያ ውስጥ ረዣዥም ህንጻዎች እንዳሉ የማያውቅ አሉ። ሀብታም ሰዎች በኢትዮጵያ እንዳሉና በንግድ ተሰማርተው እንዳሉ አያውቁም። ያ ትልቅ ችግር ነው። የጀርመን አፍሪካ የንግድ ማህበር ሀገሪቷ ከምር ምን እንደምትመስል፣ ንግድ ይካሄድ እንደሆንና ከማን ጋር መነጋገር እንደሚገባቸው እና ዬት መዋለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንደሚችሉ እንነግራቸዋለን። ለኛም ቢሆን ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም።»

የጀርመን ባለሐብቶች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪቃ ገበያ ውስጥ ባጠቃላይ ያላቸው እንቅስቃሴ ብዙም አይደለም። በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋና የገበያ ሁኔታ ከኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኬኒያ ውስጥ የጀርመን ባለሐብቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ብዙም ለመግባት ፍላጎት አላሳዩም። የቻይና በምስራቅ አፍሪቃ ገበያ ውስጥ በሰፊ መገኘት የጀርመን ኩባኒያዎችን ከእንቅልፋቸው የቀሰቀሳቸው ይመስላል።
ሰላሳ የጀርመን ድርጅቶችን ያቀፈ GERMAN TECHNOLOGY SOLUTION የተባለ ድርጅት ተወካይ የሆኑ ድራጎ ቡዙክ ወደ ፊት የጀርመን በምስራቅ አፍሪቃ ገበያ ውስጥ ከቻይና ጋር ያለውን ውድድር መመልከት ይገባል ባይ ናቸው፣

« ችግሩ የጀርመን ኩባኒያዎች ይህንን ክልል ማለትም ምስራቅ አፍሪቃን ትኩረት አልሰጡትም ነበር። በዚህ ክልል ጥቂት የጀርመን ኩባኒያዎች ብቻ ናቸው ያሉት። አሁን ቻይናዎች እይሰሩበት ነው። የገንዘብ ፍላጎት በሚያስፈልግበት ቦታም ቢሆን አሁን ቻይናውያን ፈጣኖች ሆነዋል።»

የጀርመን ኢኮኖሚ ተወካዩ ኢንጎ ባዶሬክ ከቻይናና ከሌሎች የእሲያ ሀገራት የሚመጣ ውድድር ያለውን እንድምታ ተገንዝበዋል። እንደሳቸው ከሆነ ለምሳሌ በኬኒያ ውስጥ ከአሲያ ገበያዎች ለሚደቀን ውድድር መፍትሔው «እውቀትን ማስተላለፍ» ነው።

«እኛ ከኤሺያ አቻዎቻችን የምንለየው በዚህ ላይ ነው። እዚህ ምርቶቻችንን መሸጥና እቃዎቻችንን እዚህ የኬኒያ ገቢያ ውስጥ መከመር አይደለም። ይልቅ ችሎታና እውቀትን ከዚሁ ካከባቢው ማፍለቅ ነው እንጂ።»

ኢትዮጵያ በምዕራባዊያን ዓይን ብዙ ጊዜ መረጋጋት የሰፈነባት ሀገር ተደርጋ ትቆጠራለች። በሌላ በኩል ባገር ውስጥ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በመንግስት መካከል ያለው ውዝግብ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የሄደው የኑሮ ውድነት፤ ነዋሪዎችን በኢንቨስትመንት ምክንያት ማፋናቀል፤ የነጻ መገናኛ ዘዴዎች መታፈንና ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የጀርመን ባለሐብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን የመስራት ፍላጎት ምን ያክል ሊጎዳ ይችላል? ወዘሮ አስማሁ ሲመልሱ፣

«አንዳንዴ ፖሊቲካውን ባንድ ጎን ኢኮኖሚውን በሌላው ጎን ማየት ትችላለህ። አንዳንዴ ጥሩ የንግድ ጓድ ካለህ የፖሊቲካው ነገር ብዙም አያሳስብም። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚመስለኝ ፖሊቲካውና ኢኮኖሚው ብዙም የተቀላቀሉ አይደለም። እንደዛ ቢሆን ኖሮ አንዳንድ ሰዎች ገቢያው እንዳይቀላቀሉ ይገድባቸው ይችል ነበር።

Coffee Circle
ምስል Coffee Circle
Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopien
ምስል DW
Blick aus meinem Fenster Addis Abeba Äthiopien
ምስል Solomon Mengist
Addis Abeba
ምስል derejeb/Fotolia

ገመቹ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ