1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ኖኪያ ኮባንያ የመዘጋት ጉዳይና ውዝግቡ

ረቡዕ፣ የካቲት 5 2000

የዓለም ኤኮኖሚ ከመቼውም በላይ በተሳሰረበት በዛሬው ዘመነ-ግሎባላይዜሺን ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በርካሽ ማምረት ወደሚችሉባቸው አካባቢዎች መኮብለላቸው የቀጠለ ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/E0cO
ምስል AP

ከአውቶሞቢል እስከ ኤሌክትሮኒክ ኩባንያዎች ባለፉት ዓመታት ነባር ማምረቻ ይዞታቸውን በከፊል ወይም በሙሉ እየዘጉ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ወይም ወደ ኢሢያ የተሻገሩት የበለጸገው ዓለም ፋብሪካዎች ብዙዎች ናቸው። በዚህ በጀርመንም በዓለም ላይ ታላቁ የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያ ኖኪያ ቦሁም ከተማ ውስጥ የሚገኝ ፋብሪካውን በመዝጋት ወደ ሩሜኒያ ለመሻገር ያደረገው ውሣኔ ባለፉት ሣምንታት በሰፊው ሲያነጋግር ነው የቆየው። ኖኪያ ከትናንት በስቲያ ሩሜኒያ ውስጥ ያሰራውን አዲስ ፋብሪካ መርቆ ከፍቷል። ሆኖም የቦሁም ሠራተኞች ፋብሪካቸው እንዳይዘጋ የሚያደርጉት የሕልውና ትግልም አላበቃም። ተሥፋቸው እስከምን ይሆን?

የፊንላንዱ የሞባይል ስልክ ኩባንያ ክሉጅ በተሰኘው የሰሜን-ምዕራብ ሩሜኒያ አካባቢ ከትናንት በስቲያ አዲስ ፋብሪካውን መርቆ ከፍቷል። የኩባንያው በሩሜኒያ መከፈት ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ መስክ መስፋፋት ተሥፋ ሲሆን በዚህ በጀርመን በቦሁም ከተማ ግን የነባሩ ፋብሪካ የመዘጋት ሂደት ለብዙዎች ሰቀቀን ነው የሆነው። ኖኪያ እንደ ዕቅዱ የቦሁም ማምረቻውን ከዘጋ ከ 2.300 የሚበልጡ ተቀጣሪዎቹ ያለሥራ መቅረታቸው ነው። በአካባቢው ለፋብሪካው ዕቃዎችን የሚያቀርቡ ወገኖችም ተጎጂ መሆናቸው አይቀርም።

በነጻው የኤኮኖሚና የገበያ ስርዓት ውስጥ ኩባንያዎች በርካሽ የሚያመርቱበትንና የተሻለ ትርፍ የሚያገኙበትን አካባቢ ከመምረጥ የሚያግዳቸው ነገር በመሠረቱ የለም። የፖለቲካው ዘርፍ ተጽዕኖም በተጨባጭ ከሞራል ጥሪ አልፎ ኩባያዎቹን ከዚህ መሰሉ ዕርምጃ የመግታት ሥልጣን አለው ለማለት አይቻልም። ይህ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው። ከዚህ ከጀርመን ራሱ የአውቶሞቢሉን ዘርፍ ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች ይዞታችውን በከፊል እየዘጉ የምርት ተግባራችውን ወደ ምሥራቅ አውሮፓና ወደ እሢያ አሸጋሽገዋል። ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡትም በዚህ የሠራተኛው የኑሮ ደረጃ ከፍተኛ በሆነበት የምርቱ ወጪ ከፍተኛ እየሆነ መሄዱን ነው።

የፊንላንዱ ኩባንያ ምርቱን ዘግቶ ለመሄድ መወሰኑ የሕልውና አደጋ ላይ የወደቁትን ተቀጣሪዎቹን ብቻ ሣይሆን ሕዝቡንና ፖለቲከኞችን ጭምር ነው ያስቆጣው። ኖኪያ ሞባይላቸውን ብዙዎች ዜጎችና ፖለቲከኞች አውጥተው ሲጥሉ ሌሎችም የኩባንያውን ምርቶች እንዳይገዙ ወይም እንዳይገለገሉ እስከመጣራት ደርሰዋል። ችግሩ ይህን መሰሉ ዕርምጃ ምናልባት ውሎ አድሮ ቁጣው ሲበርድ የሚረሣ መሆኑ ነው። ለማንኛውም የጀርመን መንግሥት ኩባንያው በዚሁ እንዲቆይ የተቻለውን ሁሉ ግፊት ለማድረግ መሞከሩ አልቀረም። ቦሁምን የሚጠቀልለው የዚህ የኖርድራይን ቬስትፋሊያ ክፍለ-ሐገር አስተዳደር እንዲያውም ኩባንያው አዲስ የሥራ መስኮችን እንዲከፍት ከመንግሥት የተሰጠውን ከአርባ ሚሊዮን ኤውሮ የሚበልጥ ድጎማ መልሶ እንዲከፍል በመጠየቅ ተጽዕኖውን እያጠናከረ ነው። ይሁንና ተጽዕኖ ፍሬ መስጠቱ ቢቀር በውቅቱ ያጠራጥራል።

ኖኪያ በበኩሉ የሥራ መስኮችን ከፍቻለሁ፤ ድጎማውን በአግባብ ነው የተጠቀምኩት ሲል ጥያቄውን ዋጋ አልሰጠውም። ለመዝጋት ዕቅዱ የሚሰጠው ምክንያት የቦሁሙ ኩባንያ በሥራ ወጪ ከፍተኛነት ለፉክክር ብቁ አይደለም የሚል ነው። በአንጻሩ ሩሜኒያ ውስጥ በርካሽ ዋጋ ለማምረት ይችላል። ኩባንያው በግልጽ ባያስቀምጠውም የሩሜኒያ ሠራተኞች ደሞዝ ከጀርመኑ ሲነጻጸር በሰባትኛ በስምንት ዕጅ ያነሰ እንደሚሆን ነው የሚገመተው። ኖኪያ የሩሜኒያ ምርቱን በሁለት መቶ ሠራተኞች በመጀመር በሚቀጥለው 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ተቀጣሪዎቹን ወደ 3.500 ከፍ ለማድረግ ያቅዳል። በግማሽ ዓመት ውስጥ በዚህ በጀርመን የሚገኝ ፋብሪካውን ለመዝጋትም ነው የወጠነው።

የኩባንያው ወደ ሩሜኒያ ማሽግሸግ ሌላም ዒላማ አለው። ይህም ኖኪያ በረጅም ጊዜ ገበያውን ወደ መካከለኛ ምሥራቅና ወደ አፍሪቃ ለማስፋት ያለው ፍላጎት ነው።
ከቡካሬስት እንደተነገረው ኖኪያ በሚቀጥሉት ሰላሣ ዓመታት ውስጥ ግብር መክፈል አይኖርበትም። እርግጥ ኩባንያው ከሰላሣ ዓመት በፊት ቀደም ብሎ ለቆ መሄድ ከፈለገ የመሬትና የፋብሪካ ግብሩን ለኖረበት ጊዜ ሁሉ መክፈል ይጠበቅበታል። ይህን መሰሉ አሣሪ ውል ከሩሜኒያ መንግሥት ጋር በሚቀጥሉት ሁለት ወራት እንደሚፈረም ነው የሚጠበቀው። ከቦሁሙ ሁኔታ ተገቢው ትምሕርት የተገኘ ይመስላል። ኖኪያ 159 ሄክታር ስፋት ባለው የኢንዱስትሪ ማዕከል ዘጠና ሄክታር መሬት ሲኖረው አራት ምርት አቅራቢዎቹም በዚያው እንደሚሰፍሩ ነው የሚጠበቀው።

ታዲያ በዚህ በጀርመን የተያዘው ጥረትና ግፊት ሁሉ ኩባንያውን በቦሁም ለማቆየት መቻሉ ጨርሶ እርግጠኛ አይደለም። ለነገሩ የሠራተኛው ተወካዮች 14 ሚሊዮን ኤውሮ በተግባር ላይ በማዋል ከፍተኛውን የሥራ ወጪ ለመቀነስ ይቻላል በሚል የኩባንያውን አመራር ለማግባባት ዛሬ አዲስ ሃሣብ ይዘው ቀርበዋል። ይሁን እንጂ ሃሣቡ ተቀባይነት ያግኝ-አያግኝ ገና በውል አልታወቀም። የታወቀ ነገር ቢኖር የሠራተኛው ተወካዮች ወደፊንላንድ ተጉዘው ኩባንያው ወደፊት ሞባይሎቹን ሩሜኒያ ውስጥ ከማምረት እንዲገታ በዛሬው ዕለት ሙከራ ማድረጋቸው ነው። እንደተነገረው ኩባንያው በሩሜኒያ ካለው ዕቅዱ ፈቀቅ አላለም። ይህ ደግሞ የሠራተኛው ቁጣና ምሬት ባለበት እንዲቀጥል ነው ያደረገው።

የሠራተኛው ተወካዮች የገለጹት ሻል ያለ የሚመስል ወሬ ካለ የኖኪያ አመራር የፋብሪካው መዘጋት በሚያስከትለው ሁኔታ ላይ በፊታችን በጋ ወራት ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑ ነው። የጀርመን ብረታ-ብረት ሠራተኞች የሙያ ማሕበር ተወካይ ኡልሪከ ክላይነ-ብራህም እንዳሉት “ኩባንያው ግፊቱና የደረሰበት የዝና ጉድፈት ተሰምቶታል። በመሆኑም አሁን ከጠቅላላው የሠራተኛ ውክልናና ከሙያ ማሕበሩ ጋር በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ ዝግጁነት አሳይቷል። ይህም በቦሁም በቂ የሥራ ቦታዎች ባሉበት ይቆያሉ ማለት ነው”

የሆነው ይሁን በሚቀጥለው ሣምንት አጋማሽ ላይ ምናልባት ለሚሰናበቱ ተቀጣሪዎች አማራጭ የሥራ ቦታ በሚገኝበት ወይም የሙያ ሥልጠና ዕርምጃ በሚወሰድበት ሁኔታ ድርድር ሊጀመር እንደሚችል ነው የሚነገረው። እንግዲህ በአጠቃላይ ሁኔታው በተጨባጭ እንዴት እንደሚቀጥል ሰንበት ብሎ መታዘቡ ግድ ይሆናል።