1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን-ኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ጉባዔ

ረቡዕ፣ ሰኔ 6 2004

የጀርመንን የግል ኤኮኖሚ ዘርፍ መዋዕለ-ነዋይ ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ ላይ ያለመ አንድ የጀርመንና የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ጉባዔ ባለፈው ሣምንት ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ተካሂዶ ነበር።

https://p.dw.com/p/15CsL

የጀርመንን የግል ኤኮኖሚ ዘርፍ መዋዕለ-ነዋይ ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ ላይ ያለመ አንድ የጀርመንና የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ጉባዔ ባለፈው ሣምንት ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ተካሂዶ ነበር። በዚሁ ጉባዔ ላይ የጀርመኗ ቻንስለር የወሮ/አንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠሪ ጉንተር ኑክ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አምባሳደርና የኤኮኖሚ ጉዳይ ልዑካን፣ የኮሎኝ ከተማ የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት የዓለምአቀፍ ንግድ ተጠሪ፤ እንዲሁም የጀርመን መልሶ ግንባታ ባንክ የምሥራቅ አፍሪቃ ዘርፍ ሃላፊና የጀርመን ኩባንያዎች ወኪሎችም ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያን በተመለከተ የጀርመን ኩባንያዎች ትኩረት በተለይም ያረፈው በሁለት ዘርፎች ላይ ነበር። እነዚሁም የኤነርጂው መስክና የዕርሻ ልማት ሲሆኑ ኩባንያዎቹ ኢትዮጵያ በፍጆታ ረገድ በዓለም ላይ ዝቅተኛዋ በሆነችበት በኤነርጂ ረገድ ከአሁኑ በአገሪቱ ተሰማርተው በመስራት ላይ ይገኛሉ። በወቅቱ ዋናው የኤነርጂ ምንጭ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ መሆኑ ሲታወቅ፤ ታዳሽ የጸሃይና የነፋስ ሃይል ማመንጫም በመሰራት ላይ ነው። ከዚሁ ሌላ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰባት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ስፋት ያለው ለም መሬት ለኪራይ ሲያቀርብ ይህም ዘርፍ የጀርመን ኩባንያዎች የዓይን ማረፊያ እየሆነ መሄዱ አልቀረም።

Äthiopien Awasse See
ምስል Meklit Mersha

የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው በጉባዔው ላይ የተገኙት ልዑካን በሙሉ ኢትዮጵያ በጥሩ አየሯ፣ በተፈጥሮ ሃብቷና ከአንድ እስከ ሁለት ዶላር በሚያወጣ ርካሽ የስራ ጉልበት ለባለሃብቶች ተስማሚ መሆኗን በማመልከት የጀርመንን ኩባንያዎች ለመሳብ ሞክረዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሄድ አገሪቱን ለውጭ ባለሃብቶች ጠቃሚ እያደረገ መምጣቱ ሲጠቀስ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተግባር ላይ በሚሰማሩበት ጊዜ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ታክስ መክፈል እንደሌለባቸውም ነው የተነገረው።

ይሁን እንጂ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ በተያዘው የለም መሬት ቅርምት ወይም ነጠቃ የተነሣ በጉባዔው አኳያ ተቃውሞ መሰማቱም አልቀረም። በመሬት ቅርምቱ የሕዝብ መፈናቀል፣ የምግብ ዋስትና እጦትና የአካባቢ ተፈጥሮ ዝቤት እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ነው የተጠቀሰው። የኢትዮጵያውያኑን ተቃውሞ ያቀናበሩት ወሮ/አሳየሽ ሮይሸል የተቃውሞውን ምክንያትና ዓላማ አስረድተዋል፤ ያድምጡ!

ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በመተባበር የጀርመንን ሕዝብ ትኩረት ለመሳብ በጉባዔው ስፍራ የራሱን ተቃውሞ ያሰማው የሕልውና አደጋ ላይ ለወደቁ ሕዝቦች የቆመ ድርጅት የአፍሪቃ ዘርፍ ሃላፊ ኡልሪሽ ዴሊዩስም የጉባዔውን ዓላማ አግባብ የለሽ ብለውታል።

«በጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ወጪ የመዋዕለ ነዋይ ባለቤቶች በኢትዮጵያ የእርሻ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማነሳሳትና ከዚሁ ጋር በማያያዝም በለም መሬት ቅርምት ላይ የገቡ የጀርመን ኩባንያዎችን እንድ ጥሩ ምሳሌ ለማቅረብ የሚደረገውን ሙከራ አግባብ የለሽ ሆኖ ነው ያገኘነው»

Ulrich Delius Gesellschaft für bedrohte Völker
ምስል Gesellschaft für bedrohte Völker

ኡልሪሽ ዴሊዩስ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ለኢትዮጵያ እጅግ ጠቃሚ ነገር እንደሆነ በማመልከት ይህም ያለ አገሪቱ አርሶ አደር ተሳትፎ እንደማይሳካ አስገንዝበዋል። እንደርሳቸውይህ ሣይሆን የእርሻ ልማት ተሃድሶ ማድረግ ጨርሶ አይቻልም።

«አዎን የሚቻል ነገር አይደለም። ከኢትዮጵያ አርሶ አደር ጋር አብሮ መስራት ግድ ይሆናል። እናም የምንለው ልማትን፤ የትንሹን ገበሬ ሁኔታ የሚያሻሽል ዕርምጃን እንደግፋለን ነው። ግን ሰፊ መሬት ለመቆጣጠር የሚሞክሩት ታላላቅ ኩባንያዎች ቅርምት በኛ ዕምነት አስፈላጊ አይደለም። ይህ በመሠረቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉዳዩን ትልቅ ችግር አድርጎ በመመልከት ያወጣውን መርህ የሚጻረር ነው። በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ የመሬት ቅርምትን የሚቃወም አዲስ መርህ ለማሰፈንም ታቅዷል። እና ይህ ጉባዔ ይህንንም የሚጻረር አሳፋሪ ነገር ነው»

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ለም መሬትን በማከራየቱ ረገድ ዜጎች መፈናቀላቸውን ሲያስተባብሉ በዚህ መንገድ ለውጭ ባለሃብቶች የተሰጠው መሬት ጥቅም ላይ ያልዋለ ባዶ ቦታ እንደነበር ነው እንደገና የተናገሩት። በጉባዔው ላይ የተገኙት ሶላር-23 የተሰኘው የኤነርጂ ኩባንያና አካሲስ የተባለ የተክል ነዳጅ ለማምረት በኢትዮጵያ የተሰማራ ኩባንያም ለምሳሌ የሰፈሩበት መሬት ተነጥቆ እንዳልተሰጣቸው ግልጸዋል። ይሁንና ይህ አባባል በብዙ ታዛቢዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም።

በዓለምአቀፉ የመሬት ንግድ ላይ ያተኮረ «ላንድ ማትሪክስ» የተሰኘ በቅርቡ ይፋ የወጣ የዳታ ባንክ ወይም ጥንቅር መረጃ እንዳመለከተው የመሪት ቅርምቱ ተጎጂ አነስተኛው ገበሬ ነው። ጥናቱ የተባበሩት መንግሥታትን፣ የዓለም ባንክን፣ እንዲሁም የታላላቅ የልማት ፖሊሲና የምርምር ድርጅቶችን መረጃዎች በአንድ ይጠቀልላል። እንግዲህ ኩባንያዎቹ በድሃው ገበሬ ትከሻ አትራፊ ሆነዋል ማለት ነው።

Günther Nooke
ምስል DW/Mesfin Mekonnen

ወደ ጉባዔው መለስ እንበልና የጀርመንና የኢትዮጵያ ግንኙነት በተለይ በዲፕሎማሲው ረገድ ረዘም ያለ ታሪክ ያለው ነው። የሁለቱ ሃገራት የኤኮኖሚና የንግድ ግንኙነትም እያደገ በመሄድ ላይ ሲሆን የቻንስለር አንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠሪ ጉንተር ኑክ እንዳስረዱት የጀርመን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርገው ትብብር ከልማት ዕርዳታ አቅርቦት ይልቅ የኤኮኖሚ ሽርክናን ይመርጣል። ጉንተር ኑክ በቅርቡ ዋሺንግተን ላይ ተካሂዶ የነበረውን የቡድን-ስምንት የምግብ ዋስትና ጉባዔ መለስ ብሎ በማስታወስ ዘላቂ ዕድገት እንዲገኝ የሕዝብ ተሳትፎ ወሣን መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

«ቡድን-ስምንት መንግሥታት በግንቦት 18 እና 19 ኢትዮጵያን ጨምሮ ከስድሥት የአፍሪቃ ሸሪክ መሪዎች ጋር በመሆን ዋሺንግተን ላይ ባካሄዱት ጉባዔ በምግብ ዋስትና ረገድ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር ተስማምተዋል። ቡድን-ስምንት እስካሁን በ 26 የአፍሪቃ ሃገራት በእርሻ ልማት ለተገኙት ስኬቶች ዕውቅና ሲሰጥ በዚሁ ዘርፍ ተጨማሪ ዕርምጃ እንዲደረግም ነው የሚፈልገው»

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 85 በመቶ የሚበልጠው ሕዝብ በዕርሻ ልማት ላይ የተሰማራ ሲሆን ይሄው ዘርፍም የአገሪቱን የኤኮኖሚ ዕድገት ግማሽ ድርሻ ይይዛል።

«ስምምነቱ ለኢትዮጵያም ጥሩ ዕድልን የሚፈጥር ሲሆን ስድሥቱ መሪዎችም ለዚሁ አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት ቃል ገብተዋል። እርግጥ ይህ ዘላቂና አረንጓዴ የልማት ጥረት ስኬት ሊያገኝ የሚችለው አብዛኛው ሕዝብ ተሳታፊ ሲሆን ብቻ ነው»

የጀርመን መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ እንደ ቻይና በመንግሥታዊ መዋቅራዊ ግንባታ ፕሮዤዎች ለመሳተፍ አይፈልግም። ነገር ግን፤

«ለጀርመን ኩባንያዎች ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ ዋስትና ለመስጠት ዝግጁ ነው። በጀርመን የልማት ድርጅት በኩል ዘላቂ ለሆነ ዕድገት ካፒታል ያቀርባል። የውጭ ንግድ ዋስትናም ይሰጣል»

ጉንተር ኑክ በሌላ በኩል የጀርመን መንግሥት ዘላቂ የኤኮኖሚ ዕደገትን በማራመዱ ረገድ በኤኮኖሚ ትብብርና የልማት ተቋሙ አማካይነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በአፈጻጸም መሠረታዊ ነጥቦች ሳይስማማ መቅረቱንም በዝምታ ለማለፍ አልፈለጉም። የዴሞክራሲው ሁኔታ ሊሻሻል ይገባዋል ባይ ናቸው።

«የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ወደ ኢትዮጵያም ሆነ በጥቅሉ ወደ አፍሪቃ እንዲሄዱና ለዘላቂ የኤኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ከተፈለገ የፖለቲካ ዕርጋታ መኖሩ ወሣኝ ነገር ነው። የኢትዮጵያ ሁኔታ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በንጽጽር ምናልባት ደህና ተብሎ ሊወደስ ይችላል። ግን ዕርጋታና ልማት ለዘለቄታው ከላይ ወደታች በትዕዛዝ ብቻ የሚቀናበር ሊሆን አይችልም። በኢትዮጵያም ቢሆን ዘላቂ ዕርጋታ ሊኖር የሚችለው መንግሥት በሕብረተሰቡ ብዙሃን ሲታቀፍ፣ ፍትሃዊና ነጻ ምርጫ የወለደው ሲሆን ብቻ ነው። በጎ አስተዳደር እንዲኖር ማድረግ፣ ሰብዓዊ መብቶችንንና የውሁዳንን ደህንነት ማረጋገጥም ያስፈልጋል»

ኮሎኝ ላይ የተካሄደው የጀርመን-ኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ጉባዔ በዓይነቱ የመጀመሪያው መሆኑ ሲነገር ቀጣይ ጉባዔዎች እንደሚከተሉ ተሥፋ በመጣል ነው የተፈጸመው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ