1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ኤኮኖሚና የሙያተኞች እጥረት ተጽዕኖ

ሐሙስ፣ መስከረም 15 2001

የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ ተጠሪዎች በሰለጠነ የሥራ ሃይል እጥረት ሲያማርሩ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል። ለአብነት ያህል በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ኢንጂነሮች እጥረት ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ ለጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገትና ዓለምአቀፍ የፉክክር ብቃት ፈታኝ ነገር መሆኑ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/FOlw
የውጭ ሙያተኞች በጀርመን
የውጭ ሙያተኞች በጀርመንምስል dpa Zentralbild

ጀርመን እንግዲህ የጎደለውን ለመሙላት ከየትኛውም የአውሮፓ አገር ይልቅ የውጭ ሙያተኞች ያስፈልጓታል ማለት ነው። ምክንያቱም ሕብረተሰቡ እያረጀ የሚሄድና የወጣቱ የሥራ ሃይል ድርሻ በመመንመን ላይ መሆኑ ነው። ሆኖም ከመንግሥት በኩል መጤ ሙያተኞችን ወደ አገሪቱ የሥራ ገበያ በማስገባቱ ረገድ ጥርጊያው በሚገባ ተመቻችቶ አይገኝም። በቅርቡ በጉዳዩ የቀረበ ጥናት እንዳመለከተው ቢሮክራሲያዊው የአሠራር ዘይቤ መለወጡና ሳይውል ሳያድር ችግሩን የሚያቃልሉ ጭብጥ ዕርምጃዎችን መውሰዱ ግድ ነው።

ጀርመን የሰለጠኑ የውጭ ባለሙያዎችን በማስገባት ረገድ ከአብዛኞቹ መሰል ምዕራባውያን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ አገሮች ኋላ የቀረች ሆና ነው የምትገኘው። በአሕጽሮት OECD እየተባለ የሚጠራው የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው እንደ ጀርመን የውጭ ሙያተኞች ወደ ሥራ ገበዮቻቸው እንዳይገቡ መሰናክል ፈጥረው የሚገኙት አገሮች ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ ጃፓን፣ ፖርቱጋል፣ ፊንላንድና ፈረንሣይ ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል ግን በዚህ በጀርመን በብዙዎች ኩባንያዎች የሰለጠነው የሥራ ሃይል እጥረት ይበልጥ ግልጽ እየሆነና ችግር እየፈጠረ በመሄድ ላይ ነው። ሥራ አጦችን በማሰልጠን ቀዳዳውን ለመሸፈን በየጊዜው የተደረገውና እየተደረገ ያለው ሙከራ የተፈለገውን ፍሬ አልሰጠም።

በመሆኑም የኤኮኖሚው ዘርፍ መንግሥት ይበልጥ የሰለጠኑ ሙያተኞችን ወደ አገር እንዲያስገባ የሚያደርገውን ውትወታ በወቅቱ ይበልጥ አጠናክሯል። በዘርፉ ላይ ባተኮሩ ጠበብት አማካይነት የመፍትሄ ጽንሰ-ሃሣብ መቅረቡም አልቀረም። ችግሩ ከፖለቲከኞች በኩል የሚፈለገው ቁርጠኝነት አለመታየቱ ላይ ነው። የኤኮኖሚው ዘርፍ የሰለጠነ ሙያተኛ ያለህ ሲል የሚያሰማው እሮሮ መንግሥት መጤዎችን በማዋሃዱ ወይም ሠራተኞችን በማስገባቱ ረገድ የሚከተለው ፖሊሲ ጊዜውን የተከተለ እንዳልሆነ ከማሣየቱም ባሻገር ፖለቲከኞች ሳይዘገይ ተገቢውን ባለማድረጋቸው የሚያጋልጣቸውም ነው የሆነው።

በዓለምአቀፍ ደረጃ ተመራማሪዎችን፣ ኢንጂነሮችና ሌሎች ሙያተኞችን ለመሳብ በሚደረገው ፉክክር ጀርመን ከመሰል መንግሥታት ስትነጻጸር ደካማዋ ናት። ይህንኑ የመጤዎች ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ሽቴፈን አንገኔንድት በቅርቡ ለጥምሩ መንግሥት አካል ለሶሻል ዴሞክራቱ ፓርቲ ቀረብ ላለው ፍሪድሪሽ ኤበርት በጎ አድራጎት ድርጅት ባቀረቡት የጥናት ውጤት አረጋግጠው ነበር።

“የሰለጠኑ የውጭ ሙያተኞችን ድርሻ በተመለከተ በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የቀረበው አሃዝ እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ነው የሚገኘው። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስፈልጉንን መጤዎች ለማግኘት በምንከተለው አሠራር ተስማሚነት ላይ ትልቅ ጥያቄን የሚያስነሣ ነው”

ለነገሩ የጀርመን መንግሥት ባለፈው ዓመት ሕዳር ወር ለአሥሩ አዳዲስ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት የተሽከርካሪና የምርት መኪና ዘርፍ ባለሙያዎች፤ እንዲሁም ኤሌክትሮ-ኢንጂነሮች ወደ ሥራ ገበያው የሚገቡበትን ሁኔታ የሚያቃልል ዕርምጃ በመውሰድ ችግሩን ለማለዘብ ሞክሮ ነበር። ይሁንና የተፈለገውን ያህል ሙያተኞቹን ለመሳብ አልተቻለም። እስካሁን ከምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ብቅ ያሉት ኢንጂነሮች 19 ብቻ ናቸው። ጀርመን ከተጣራች ሁሉም ተንሰፍስፎ በሰልፍ መግቢያውን ያጣብበዋል የሚለው ዕምነት እንደታሰበው አልሰራም።
ዛሬ የተጠቀሱት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ራሳቸው ዴሞክራሲ የሰፈነባቸውና በጥሩ የዕድገት ሁኔታ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በከፍተኛ ሙያ የሰለጠኑ ሠራተኞችን መሳቡ እንደ ጥንቱ ቀላል ነገር አይደለም። በመሆኑም አሁን የጀርመን መንግሥት እንደገና በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በሰለጠኑ የውጭ ሠራተኞች ላይ ተደቅኖ የሚገኘውን መሰናክል ዝቅ ለማድረግ የተግባር ዕቅድ ያለውን መርህ አስፍኗል። ሆኖም ሽቴፈን አንገኔንድትን የመሳሰሉ የጀርመን የሣይንስና የፖለቲካ ጥናት ድርጅት ባልደረቦች የመንግሥቱን ፖሊሲ አሁንም የሚገባውን ያህል ፍቱን ወይም የፈጠነ አድርገው አይመለከቱትም።

“ይህ የተጓተተ ሂደት ወደፊት የሚያዋጣ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የሕብረተሰቡ የወጣት ሃይል ይዞታና የኤኮኖሚያችን መዋቅራዊ ዕድገት የደከመ ሆኖ ነው የሚገኘው። ገና ከአሁኑ ብርቱ የሰለጠነ ሙያተኛ እጥረት አለብን። በአሥርና በአሥራ አምሥት ዓመት ውስጥ ደግሞ ሁኔታው በፍጥነት እየባሰ ነው የሚሄደው። በቀላሉ ሕብረተሰባችን እያረጀ ያለ ነው። ስለዚህም ያለ መጤዎች ችግሩን ልንገፋው አንችልም”

በአርግጥም የጀርመን ሕብረተሰብ ከመጥን በላይ እያረጀ በመሄድ ላይ የሚገኝ ነው። ዛሬ ሰርቶ ለመንግሥት ግብር የሚከፍለውም ሆነ የማሕበራዊ ዋስትናውን ስርዓት፤ ማለት የጡረታና የጤና ጥበቃውን ሽክም የሚወጣው የሥራ ሃይል ከሲሶ አይበልጥም። ይሄው የሕብረተሰብ ሃቅ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን ማሕበራዊ ስርዓት ሊያዛባ እስከማስጋት ደርሶ ነበር። ስርዓቱን ለማቆየት መንግሥት በወሰዳቸው አንዳንድ የለውጥ ዕርምጃዎች የሠርቶ-አደሩ ወገን ሽክም መጨመሩና ለአኤኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ የሆነ የገንዘብ ሃይሉን መጫኑም አልቀረም። ይህ እርግጥ የውስጡ ጉዳይ ነው።

ወደ ሥራ ገበያው ሁኔታ እንመለስና ሽቴፈን አንገኔንድት ወደፊት መጤ ሠራተኞችን የመቀበሉ ፖሊሲ እንዴት ሊሆን እንደሚገባው ሃሣብ አቅርበዋል። የሚያስጨብጡት ቁልፍ ሃሣብም ጀርመን የሥራ ገበያዋን በመለስተኛና በከፍተኛ ደረጃ ለሰለጠኑ መጤዎች በሰፊው መክፈቷ ግድ ነው የሚል ነው። የአቀባበሉን ሁኔታም በሁለት ይከፍሉታል።

“የመጀመሪያው የመጤውን ብቃት መመዘኛ የነጥብ ዘዴ ነው። ዕድሜ፣ የቁዋንቁዋ ችሎታና የሙያ ደረጃን ያካትታል። በዚህ መስፈርት ሙያተኛውን ማስገባት ይቻላል ማለት ነው። ሁለተኛው መንገድ በሥራ ገበያው ሁኔታ ላይ የተወሰነ ይሆናል። ማለት በሥራ ገበያው ላይ የሰለጠነ ሙያተኛ እጥረት እያደገ በሚሄድባቸው ዘርፎች ላይ የሚያተኩር ነው። እና ለዚህ ዘርፍ መጤዎች በየጊዜው በኮታ፤ በተወሰነ አሃዘ እንዲገቡ መልቀቁ አስፈላጊ ይሆናል”

ሃሣቡ ገቢር ቢሆን ዛሬ ተሸማቆና በቅራኔ ተሞልቶ በሚገኘው የመጤ ሠራተኞች ጉዳይ ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ ሊያስከትል የሚችል በሆነ ነበር። ግን ምንም እንኳ ጀርመን መጤ ሙያተኞች የሚያስፈልጓት ቢሆንም ከ 35 ዓመታት በፊት የሰፈነው ከአውሮፓ ሕብረት ውጭ የሚገኙ የውጭ ሠራተኞችን መጋበዙን የሚያግድ ደምብ አሁንም አለ። እርግጥ ደምቡ ከጊዜ በኋላ በርከት ባሉ የልዩ አስተያየት አንቀጾች እንዲለዝብ መደረጉ አልቀረም። በዚህ ልዩ አስተያየት ውስጥ ለምሳሌ የሣይንስ ጠበብት፣ ጋዜጠኞች፣ የውጭ ባሕል ምግብ አዘጋጆች፣ አንጋፎችን የሚንከባከቡ ሠራተኞችና እግር ኳስ ተጫዋቾች ይጠቃለላሉ።
ከዚሀ በተጨማሪ ከምሥራቅ አውሮፓ በአዝመራ ወራት ለለቀማ የሚመጡ ረዳቶች፤ ለተወሰነ ጊዜ የሚላኩ የፋብሪካ ሠራተኞችና ከግማሽ ሚሊዮን ኤውሮ በላይ ካፒታል በሥራ ላይ ለማዋል የሚችሉ ኩባንያዎችም የዚህ ልዩ አስተያየት ተጠቃሚዎች ናችው። ግን ሁኔታው እፍንፍን ያለ የቢሮክራሲ ችግርም አያጣውም። በተለይ ጊዜ የሚፈጀው የመንግሥት የአሠራር ዘይቤ ኩባንያዎች ብዙ የሚያማርሩበት ነገር ነው። እንበል አንድ የጀርመን ኩባንያ አንድን የውጭ ሙያተኛ ማሰራት ከፈለገ የመንግሥቱ አስቀጣሪ ቢሮ የተባለው የሥራ ቦታ በቅድሚያ በአንድ ጀርመናዊ ወይም የአውሮፓ ሕብረት ዜጋ ሊያዝ መቻል-አለመቻሉን አጣራለሁ ነው የሚለው። ይህ ደግሞ አንዳንዴ የተወሳሰበ ሂደት ይታይበታል። በመሆኑም አንገኔንድት ከሁሉም በላይ የአሠራር ግልጽነት እንደሚያስፈልግ ነው የሚያስገነዝቡት።

“ጉዳዩ በአጠቃላይ መልክ ሊተኮርበት የሚገባ ነው። ይህም አጠቃላይ ጽንሰ-ሃሣብ ግልጽና ቁልጭ ያለ መሆን ይኖርበታል። በጀርመን ለመስፈር ለሚፈልግ ሠራተኛ ወይም ሙያተኛ ለሚፈልግ ኩባንያ ተስማሚ መሆኑ ተገቢ ነው”

እርግጥ በጠበብት አካባቢ የውጭ ሙያተኞችን ለጀርመን በሚስማማ መንገድ በማሰማራቱ ጉዳይ በሚፈለገው ዕርምጃ መልሱ ከቀረበ ቆይቷል። ሆኖም ግን የሕብረተሰቡ ውይይት ባለበት መዞሩን እንደቀጠለ ነው። የረባ ዕርምጃ አይታይበትም። የወቅቱ የፍሪድሪሽ ኤበርት ድርጅት የጥናት ውጤት ከፖለቲከኞቹ ጠረጴዛ ላይ ከደረሰ ሰንበት ብሏል። ሆኖም ለምሳሌ ካናዳን በመሳሰሉት መጤ ሠራተኞችን በሚቀበሉ ሃገራት ፍቱን የሆነው የነጥብ ስርዓት፤ ማለት የሥራ ቦታ ማግኘትን ቅድመ-ግዴታ የማያደርገው ዘዴ በወቅቱ የወግ አጥባቂው ሕብረት ተቃውሞ ተደቅኖበት ነው የሚገኘው።
የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻሉ ሕብረት ተጠሪዎች ለግትርነታቸው የሚሰጡት ምክንያት የአገር ውስጡን የሥራ አጥ ሁኔታ ያባብሳል፤ ለማሕበራዊው ዋስትና ስርዓትም ከባድ ሽክም ነው የሚሆነው የሚል ነው። ከዚህ አንጻር የውጭ ሠራተኛ የማስገባቱ ሂደት በሙከራ ደረጃ እንኳ ዕውን ሊሆን የመቻሉ ዕድል ዝቅተኛ ነው። በተለይ ደግሞ የጀርመን ፌደራላዊ ም/ቤት ምርጫ እየተቃረበ በመሄዱ የአገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ትኩረት በወቅቱ ሌላ ላይ ነውና ይህም ሁኔታውን አመቺ አያደርገውም። በአጠቃላይ ለጀርመን በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ችግሩን ለመወጣት የሚቀረው ምርጫ አንድ ነው። የሰለጠኑ ሙያተኞችን በማስገባቱ ረገድ በተቻለ ፍጥነት ከቢሮክራሲ የተላቀቀ ጭብጥ ደምብን ዕውን ማድረጉ ግድ ይሆናል።