1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ወጣት በጎ ፈቃደኞች በእስራኤል

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2005

ትምህርት ቤቶች ለረዥም ጊዜ የሚዘጉበት የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት በርካታ የጀርመንና የእስራኤል ወጣቶች የልምድ ልውውጥ መርኀ ግብር የሚያካሂዱበት ወቅት ነው ። ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ ጀርመናውያን ወጣት በጎ ፈቃደኞች በእስራኤል ማህበራዊ አግልግሎቶችን በመስጠት ላይ ናቸው

https://p.dw.com/p/19OHV
ምስል Aktion Sühnezeichen/H. Greyer

የዶቼቬለዋ ክላውድያ ፕሬቬዛኖስ እንደዘገበችው ወጣት ጀርመናውያን በናዚ ጀርመን የተጨፈጨፉትን ይሁዲዎች ሃገር ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ።
«በ 2 ተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን አይሁዶች ላይ ከተፈፀመው ጭፍጨፋ ከተረፉ ሰዎች ጋር መነጋገር የቻልኩ ፣ ከመጨረሻዎቹ ትውልዶች መካከል አንዷ መሆኔ ምን ማለት እንደሆነ ለመገንዘብ ችያለሁ ።»
የሰማችኋት የ24 አመቷ ኤላ ኤንትስማን የዛሬ 5 አመት ለ 12 ወራት እስራኤል በሚገኝ አንድ አፀደ ህፃናት በኋላም በአንድ የአዛውንቶች መጦሪያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥታለች ። ኤላ በአዛውንቶቹ መጦሪያ ውስጥ ባለፈው የካቲት 100 ዓመታቸውን ያከበሩትን ግሬትል ሜሮን የተባሉትን ጀርመን የተወለዱትን አዛውንት ትንከባከብ ነበር ። አጋጣሚው ታሪክን ይበልጥ ለመረዳት ጥሩ መንገድ ነበር ።

« ለሰላም የእርቅ አገልግሎት » በእንግሊዘኛው ምህፃር ASF የተባለው ድርጅት እድሜያቸው ከ 18 እስከ 30 የሚደርስ ወጣቶችን ፣ በየጊዜው ከጀርመን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ እስራኤል ከሚልኩ ድርጅቶች አንዱ ነው ። በዚህ ድርጅት አማካይነት በየአመቱ 900 ወጣቶችን ወደ እስራኤል ይሄዳሉ ።

Aktion Sühnezeichen - Seniorenheim Haifa
ምስል Aktion Sühnezeichen/H. Greyer

በጎ ፈቃደኞች ኪቡት በሚባሉት የእስራኤል እርሻዎች ውስጥም ነው የሚያገለግሉት ። እጎአ በ2012 እስራኤል የሄዱት በጎ ፈቃደኖች ቁጥር 1200 እንደነበር ቴላቪቭ የሚገኘው የዚህ መርሃ ግብር ሃላፊ አያ ሳጊ አስረድተዋል ። ብዙዎቹ ለምን ወደ እስራኤል እንደሚመጡ ሲያስረዱ
«ለምን እንደሚመጡ እንደ በጎ ፈቃደኛው የሚለያይ ይመስለኛል ። እኛም አንዳንዴ እውነተኛ ምክንያታቸውን አናውቅም ። ወደ አንድ ሃገር የሚስበን ጉዳይ ምን እንደሆነ እና ምን እንደሚያገናኘን ሁሌም መልሱ የለንም ። ሆኖም አንዳንዶቹ በታሪኩ በመሳባቸው ምክንያት እዚህ የሚገኙ ይመስለኛል ። ይህ የምክንያቱ አካል ይመስለኛል ። »
ናዚ ጀርመናውያን በ2ተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመንና በአውሮፓ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ይሁዲዎች ላይ ያካሄዱት ጭፍጨፋ በጀርመንና በእስራኤል ታሪክ ላይ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ተፅእኖ አንዳሳደረ ነው ። ASF ን የመሳሰሉ ድርጅቶች ወጣቶችን ከጀርመን ወደ እስራኤል መላክ ከጀመሩ ወደ 50 ዓመት ተጠግቷል ። ASF እንደሚለው በነዚህ ዓመታትም ወጣቶች ወደ እስራኤል ለመሄድ ያላቸው ፍላጎት አልቀነሰም ። በእስራኤል እርሻዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡት ከ50 ሃገራት ከመጡ ግለሰቦቹ አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን ናቸው ። ጀርመናውያኑም ለሁለቱ ሀገራት ታሪክ ይበልጥ ትኩረት እንደሚሰጡ ሃላፊዋ አያ ሳጊ ይናገራሉ

Freiwilliger der Aktion Sühnezeichen Friedensdienst in Israel
ምስል Josi Aloni


« እነርሱ ታሪኩን ይበልጥ ያውቃሉ ። ብዙ አውቀት ይዘው ነው የሚመጡት ። ጉዳዩ ይበልጥ ስሜትን የሚነካ መሆኑንም ይገነዘባሉ ። አንዳንዶቹ እንዲያውም ስለዚህ ጉዳይ ጠለቅ ያለ እውቀት ለመገብየት ይጥራሉ »
እያንዳንዱ ጀርመናዊ በጎ ፈቃደኛ ከጊዜው የተወሰነውን ከናዚዎች ጭፈጨፋ ካመለጡ ሰዎች ጋር ያሳልፋል ። ኤላ አንትስማን የዛሬ 5 ዓመት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሰጠች በኋላ በዓመት ሁለቴ እስራኤልን ትጎበኛለች ። መጀመሪያ እስራኤል ስትሄድ የጠበቀችውና የገጠማት የተለያየ ነበር ።

« ጀርመናዊ ስለሆንኩ ብዙ ሰዎች ያነጋገሩኛል ብብዩ አልጠበቅኩም ነበር ። አስቸጋሪም ይሆናል ብዬ ነበር የምጠብቀው ሆኖም በተቃራኒው አብዛኛዎቹ ሁሉም ማለት ይቻላል በበጎ ስሜት አቅርበውኝ በጀርመንኛ ሊያነጋግሩኝ ይፈልጉ ነበር ። »
ሌላው የ20 ዓመቱ ቫይስቤክ እስራኤልን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመረጠው አጋጣሚውን በመጠቀም የቀደመውን የጀርመን ታሪክና በይሁዲዎች ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በቅርበት ለመረዳት ነው ። ። በASF አማካይነት ወደ እስራኤል ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሄዱት ወጣቶች አብዛኛዎቹ ከህፃናት አዛውንት እና አካል ጉዳተኞች ጋር የተገናኙ ማህበራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ ነው የሚሰማሩት ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ