1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የአዲስ አበባ ጉብኝት

ሰኞ፣ መጋቢት 15 2006

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍርንክ ባልተር ሽታይንማየር በአፍሪቃ የሦስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ። ጀርመናዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና

https://p.dw.com/p/1BVAV
ምስል picture alliance

ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ጋ ተገናኝተው ሀሳብ ተለዋውጠዋል። ሽታይንማየር በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በተካሄደው ስብሰባ እንደተናገሩት፣ አፍሪቃውያን በአህጉራቸው ለሚነሱ ውዝግቦች ራሳቸው መፍትሔ ለማፈላለግ የጀመሩት ጥረታቸው ይሳካ ዘንድ ከአውሮጳ፣ ከጀርመን ለዚሁ የሚያስፈልገው ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ያሰሙት ሀሳብ ሰሚ ጆሮ ማግኘቱን ገልጸዋል።

Frank Walter-Steinmeier in Äthiopien
ምስል DW/Getachew Tedla

« በዚህም የተነሳ ከተለመደው የኤኮኖሚ ተራድዖ ትብብር ጎን በሌሎች በርካታ ዘርፎችም ትብብራችንን አጠናክረናል። በዚህም መሰረት፣ በሶማልያ እና አሁን ደግሞ በማሊ የፀጥታ ኃይላትን በማሠልጠኑ ተግባር ላይ ተሠማርተናል። »

የሁለቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ውይይት በሀገሮቻቸው የጋራ ግንኙነት፣ ባካባቢ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንደነበር ዶክተር ቴዎድሮስ አስታውቀዋል።

« ባጠቃላይ ባለን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት፣ ከዚያ ደግሞ ባካባባ እና ባለም አቀፍ ላይ ነው የተወያየነው። በነዚህ ዘርፎች በጣም ተመሳሳይ አቋም ነው ያለን, አፈታቱም ላይ በጋራ ለመስራት ነው የተስማማነው። »

ሽታይንማየርም ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋ ላለው የቆየ የጋራ ግንኙነት ከፍተኛ ቦታ እንደምትሰጠው በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሚነሱ ውዝግቦች እልባት እንዲያገኙ ሁነኛ ድርሻ አበርክታለች ሲሉ አሞግሰዋል።

« ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ዋነኛ አጋራችን መሆንዋን እና በውጭ ፖሊሲያችንም ከፍተኛ ቦታ መያዟን ነው። በአፍሪቃ ለሚታዩት ብዙዎቹ ውዝግቦች መፍትሔ በማፈላለጉ ረገድ ርዳታ ታደርጋለች፣ በተለይ ግን፣ ለጠቅላላው አካባቢ ኃላፊነትን በመውሰድ አርአያ ሆናለች። »

ለኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች በበርሊን ሥልጠና ለመስጠት ዕቅድ መያዙን ሽታይንማየር አክለው ገልጸዋል። ጀርመናዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በአንድ ቀኑ የአዲስ አበባ ጉብኘታቸው የአፍሪቃ ህብረትን እንደጎበኙ እና ከህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ጋ ተገናኝተው ሀሳብ እንደተለዋወጡ ተገልጾዋል። ሽታይንማየር በአፍሪቃ በሚያደርጉት በዚሁ የመጀመሪያው ጉዟቸው ከኢትዮጵያ ቀጥለው ታንዛንያ እና አንጎላንም ይጎበኛሉ።

ስለጀርመናዊው እንግዳ ጉብኝት ጌታቸው ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ ተከታዩን ዘገባ ልኮልናል።

ጌታቸው ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ