1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የኤቦላ ርዳታ ዘግይቶ ይሆን?

ማክሰኞ፣ ኅዳር 23 2007

በሶስት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የተዛመተዉ ኢቦላ 6000 ገደማ ሰው ገልዋል። ወደ 16 ሺህ ህዝብ ደሞ በተውሓሲው ተለክፎአል። የኢቦላ ወረርሺኝ ያደረሰዉ ቀዉስ ከቁጥጥር ዉጭ የሚወጣበት ደረጃ መድረሱ እየተነገረ ነዉ። የኤቦላ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገዉ ጥረትና ትብብር ጀርመን የምታደርገዉ ርዳታ ሳይዘገይ እየተነገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1DyIJ
Evakuierungsflugzeug Robert Koch Airbus A340-300 27.11.2014 Tegel
ምስል Reuters/M. Gambarini

የኤቦላ በሽታ መዛመት ይፋ ከተደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ ዛሬም የተሐዋሲዉን ስርጭት መግታት አልተቻለም። የህክምና ባለሞያዎች በጊኒ፤ በላይቤሪያና በሴራሊዮን የተዛመተዉን የኢቦላ ተሐዋሲ መግታት እንዳልተቻላ ዛሬም ይናገራሉ። እነዚህ የምዕራብ አፍሪቃዉያን ሃገራት ከጀርመን እና ከሌሎች ዓለም ሃገራት አስቸኳይ ርዳታን ይሻሉ። የኤቦላ ተሐዋሲን ቁጥጥርን በተመለከተ የጀርመን ተጠሪ፤ ቫልተር ሊንደር ይህን ስራቸዉን ከጀመሩ ስድስት ሳምንት ሆናቸዉ። ብዙ ትችት አቅራቢዎች እንደሚናገሩት ጀርመን በምዕራብ አፍሪቃ የኤቦላ ወረርሽኝን አስከፊነትን ዘግይታ ነዉ የተረዳችዉ ፤ ለርዳታዉም እጅግ ዘግይታለች ሲሊ መንግሥትን ይተቻሉ። ይህን አስመልክቶ «ፍራንክፉርተር አልገማይነ ሳይቱንግ» የተሰኘዉ የጀርመን ጋዜጣ «በጀርመን የዉጭና የልማት ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ አደጋ» ሲል ዘግቦአል። ሌሎች የተለያዩ የጀርመን የመገናኛ ብዙሃንም የኤቦላ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት የጀርመን ርዳታ እጅግ መዘግየቱን እንዲሁም በላይቤሪያ ይገነባል የተባለዉ የኤቦላ ህሙማን ማዕከል በቀጣይ የግንባታዉ ስራ ለሌላ ቀጠሮ መተላለፉን ተዘግበዋል። የጀርመኑ የኤቦላ ተሐዋሲ ቁጥጥር ኃላፊ ዲፕሎማት ቫልተር ሊንደር ፤ በርግጥ ርዳታዉ መዘግየቱን በመግለፅ ይህ በዚህ ሁኔታ እንደማይቀጥል ተናግረዋል።
« ርዳታዉ ዘግይቶአል፤ ዘገየ ስንል ደግሞ በሁሉ ረገድ ነዉ። ያ ማለት ችግሩ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን በቅድምያ ያወቀዉ ድንበር አያግዴዉ የሐኪሞች ማህበርና ምናልባትም አንድ ሁለት የህክምና ተቋም በስተቀር በይፋ አልታወቀም ነበር። የዓለሙ የጤና ድርጅት እና የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሃገራት ጀርመንም ቢያዩ ጥሩ ነበር ፤ በዚህም አለ በዝያ እጅግ ዘግይተናል። አሁን በቀጣይ ለርዳታዉ እጅግ መዘግየታችንን የምናየዉ ይሆናል፤ እንድያም ሆኖ ለብዙዎች ርዳታችን በጣም ዘግይቶአል፤ ምክንያቱም በርካቶች በወረርሽኙ ህይወታቸዉን አጥተዋልና ነዉ።»
የጀርመን መንግሥት ተሐዋሲዉ በተሰራጨባቸዉ ሶስት የተለያዩ የገጠር ቦታዎች አነስተኛ የኤቦላ ህክምና መከታተያ ማዕከል መገንባቱ ተመልክቶአል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች ሶስት ግዜ የተገኙት የኤቦላ ቁጥጥር ቢሮ የጀርመኑ ተጠሪ ቫልተር ሊንደር በሚቀጥለዉ ሳምንት ዳግም ወደ ምዕራብ አፍሪቃ እንደሚሄዱ እና በተቻለ ፍጥነት የጀርመን ርዳታ ለማድረስ እየጣሩ መሆናቸዉን መግለፃቸዉ ተመልክቶአል።
በሌላ በኩል ስለ ኤቦላ ተሐዋሲ ምንነት በርሊን ላይ በተደረገ ዉይይት፤ ኤቦላ ተሐዋሲ በተዛመተባቸዉ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የተስፋ ጭላንጭል መታየቱን በቩልዝቡርግ የህክምና ምርምር ተቋም ጀርመናዊዉ ክሌመንስ ኦሽል ገልፀዋል። እንደ ክሌመንስ ከአለፈዉ መስከረም ወር ጀምሮ የኤቦላ ወረርሽኝ በተዛመተባቸዉ አካባቢዎች የዓለምአቀፉ ርዳታ የሚታየና የሚዳሰስ መሆኑን ተናግረዉ ነበር። እንድያም ሆኖ በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በሚገኙ የገጠር መኖርያ አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ድጋፍና ምክር እንደሚፈልጋቸዉ፤ በጀርመን ቱቢንገን ከተማ በሚገኘዉ የጀርመን ሐኪሞች ተልኮ ተቋም ዳይሪክተር ጌዚላ ሽናይደር ገልፀዋል። እንደ ሽናይደር በስጋት ዉስጥ የሚገኙት ከበሽታዉ የዳኑ ሰዎችና በኤቦላ ወላጆቻቸዉን ያጡ ህፃናት ሊደገፉ ይገባል፤
« እጅግ ብዙ ገና መሰራት የሚገባቸዉ ጉዳዮች አሉ። ኤቦላ የማኅበረሰቡን ህሊና እጅግ ጎድቶአል። ነዋሪዉ ህልዉና ፍቅር ከሚያገኝበት ከቤተሰቡ መካከል በህሙማን አሉ በሞትም ይነጠቃሉ። በዚህም ፍርሃት ነግሶአል ፍርሃት ደግሞ ወደ መገለል ያመራል፤ ፍርሃት መከለልን ጭንቀትን ያመጣል።»
የበለፀጉት መንግሥታት ማኅበረሰብ እስከዛሬ የኤቦላ ተሐዋሲን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ለምን እንዳልሰሩ ራሳቸዉን ሊጠይቁ ይገባል ሲሉም ጌዚላ ሽናይደር ተናግረዋል። ከጎርጎረሳዊዉ 1976 ዓ,ም ጀምሮ የኤቦላ ተሐዋሲ በተደጋጋሚ መከሰቱ ተዘግቦአል። ለአንድ በሽታ መፈወሻ መድሃኒት ለማግኘት ህሙማን ማስፈለጋቸዉን የገለፁት ጌዚላ ሽናይደር ፤ በምዕራብ አፍሪቃ ባለፉት 40 ዓመታት 16 ሺ የኢቦላ ምልክቶች መመዝገባቸዉንና በአሁኑ ሰዓት ዳግም ለተቀሰቀሰዉ የኤቦላ ወረርሽኝ መከላከያ መድሃኒት መስራት አለመቻሉን ተችተዋል።
በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ተሐዋሲዉን ለመከላከል ያስችል ይሆናል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የክትባት መድሃኒት፤ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ተስፋ ሰጭ ዉጤትን ማስገኘቱ መገለፁ ይታወቃል። በጀርመን ሃንቡርግ በሚገኝ የህክምና ምርምር ተቋም ዉስጥ የተሰራዉ የኤቦላ መከላከያ ክትባት በሚቀጥለዉ ወር ሰዎች ላይ እንደሚሚከር ዘገባዉ ያሳያል።

Dr. Gisela Schneider, Direktorin des Deutschen Instituts für Ärztliche Mission e.V.
የጀርመን ሐኪሞች ተልኮ ተቋም ዳይሪክተር ጌዚላ ሽናይደርምስል DW/B. Marx
Ebola Guinea 21.11.2014
ምስል AFP/Getty Images/K. Tribouillard
Walter Lindner, Diplomat, Ebola-Beauftragter der Bundesregierung
የኤቦላ ተሐዋሲን ቁጥጥርን በተመለከተ የጀርመን ዲፕሎማት ቫልተር ሊንደርምስል DW/B. Marx

ቤቲና ማክስ / አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ