1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

36 ኛዉ የጀርመን የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ክብረ በዓል

ሰኞ፣ ግንቦት 28 2009

«ጀርመናዉያን የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀንን የሚከበሩት በየሁለት ዓመቱ ነዉ። ለዚህ በዓል መከበር መነሻ የሆነዉ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ነዉ። በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ጊዜ በአዉሮጳም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍላትም ጦርነት ተነስቶ፤ ብዙ ሕዝብ እንዳለቀ በተለይም ደግሞ አይሁዶች እንደተጨፈጨፉ የሚታወቅ ነገር ነዉ።

https://p.dw.com/p/2e0IQ
Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Tewahedo St. Immanuel-Kirche in Berlin
ምስል Äthiopisch-orthodoxe Tewahedo St. Immanuel-Kirche

የጀርመን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ክብረ በዓል

በርሊን ትጸልያለች ፤ታከብራለች፤ ትደንሳለች፤ ተብሎላታል። ባለፈዉ ሳምንት ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች የታደሙበትና ለአምስት ቀናት የዘለቀዉን የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀን ያስተናገደችዉ የጀርመን  መናገሻ ከተማ በርሊን። ጀርመናዊዉ ሊዮናድ ባህ አልያም ደግሞ የበርሊኑ ቅዱስ  አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን ዲያቆን ወልደ እየሱስ በርሊን ላይ ተዘጋጅቶ በነበረዉ የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን በዓል ላይ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያንን ወክሎ ስለ ቤተ-ክርስትያኒቱ ስለታሪክዋ ስለ ባህሉ ለታዳሚዉ ሲገልጽ ከነበሩት ኢትዮጵያዉያን መካከል አንዱ ነበር።  እንደተናገረዉ በልቡ አበሻ ይሁን እንጂ ትዉልዱ እድገቱ እዚሁ ጀርመን ነዉ።

Deutschland 36. Evangelischer Kirchentag in Berlin
ከ 200 ሺህ በላይ ሕዝብ በበዓሉ ላይ ተካፍሎአል።ምስል picture-alliance/dpa/M. Gambarini

በዚህ ዝግጅታችን ዝግጅታችን የቀድሞዉን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ፖለቲከኞች የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና ፤ የግብረሰናይ ድርጅቶች የታደሙበትን የጀርመኑን የወንጌላዊት ቤተ- ክርስትያን ቀን እንቃኛለን።

ዘንድሮ በበርሊን ለአምስት ቀናት በድምቀት የተከበረዉ የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን በዓል ለየት የሚያደርገዉ የዛሬ 500 ዓመት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሕግጋቶችን በመቃወም 95 ጭብጥ የዝርዝር ሃሳቦችን ያቀረበዉ ጀርመናዊ ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ላይ ተኃድሶን አድርጎ ፕሮቴስታንት የተሰኘዉን ኃይማኖት የመሰረተበት ዓመት መታሰብያ በመሆኑም  ነዉ። ማርቲን ሉተር የዛሬ 500ዓመት በምስራቃዊ ጀርመን ዛክሰን አንሃልት ፊደራላዊ ግዛት ቪተምበርግ በምትባል ትንሽ ከተማ በሚገኝ የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን አምድ ወይም በር ላይ የያዛቸዉን የለዉጥ ሕግጋቶች ለጥፎ ተቃዉሞዉን ያሰማበት ከተማ በመሆኑም ዝግጅቱ እንደ በርሊን ሁሉ በትንሽዋ በቪተምበርግ ከተማም ነበር።  የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ መላከ ገነት አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ እንደነገሩን የዘንድሮዉ በዓል ለየት ያለ ነበር።

« የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን በየሁለት ዓመቱ አንድ ጊዜ የምታከብረዉ የቤተ-ክርስትያን ቀን ተብሎ የሚከበር ነዉ። በዘንድሮዉ ዓመትም ከሌላዉ ጊዜ ለየት የሚያደርገዉ ማርቲን ሉተር፤ በቪተንበርግ ወይም ደግሞ ማርቲን ሽታት ቪተንበርግ በሚባለዉ ቦታ ላይ በካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ላይ የነበረዉን የተለየ ሃሳብ ያቀረበበት 500 ኛ ዓመት ስለሆነ ነዉ።  በዚህም ምክንያት ከሌሎቹ ጊዜያት ከሚከበርበት ዓይነት ሁኔታ በተለየ ነዉ የተከበረዉ። ምክንያቱም የህዝቡም ብዛት ሲታይ፤ የነበሩት ዝግጅቶች ሲታዩ ሰፋ ያሉ ነበሩ። »  በዝግጅቱ መግቢያ ላይ የቀረበዉ ጀርመናዊዉ ሊዮናርድ ባህ በዚህ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ወክሎ ከተሳተፉት በርካታ ኢትዮጵያዉያን መካከል አንዱ ነበር። ሊዮናርድ በርሊን የተከበረዉ የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀን እጅግ ደማቅ ነበር ሲል እንዲህ ይተርካል።  
«በበርሊን የተከበረዉ የቤተ-ክርስትያን ቀን እጅግ ደማቅና ጥሩ ነበር። በዚህ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ- ክርስትያን ራሱን የሚያስተዋዉቅበት ሁለት ቦታዎች ነበሩት። አንዱ ከኮለኝ የመጣዉ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን የቆመበት ቦታ ሲሆን ሁለተኛዉ እዚሁ በርሊን የሚገኘዉ የቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን የያዘዉ ቦታ ነበር።  የኢትዮጵያን ቤተ-ክርስትያንን ባህልን ለመተዋወቅ ወደዚህ ቦታ ብዙ ሰዎች መጥተዉ ነበር። የአብያተ ክርስትያናቱ ልዑካን የኢትዮጵያ ባህላዊ ቡናን ምግብን ሁሉ አቅርበዉ ነበር።  ስለኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን ታሪክ፤ እምነትና ባህልን የሚገልጽ ህትመትንም ለእድምተኛዉ አድለናል። ብዙ ሰዎች ስለቤተ-ክርስትያኒቱ በርካታ ጥያቄዎችንም ጠይቀዉ በዝርዝር ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ ሰጥተናል። »
ዘንድሮ ጀርመናዉያን በአከብሩት የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀን ዝግጅት ለላይ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ እድምተኞች ተገኝተዋል።  በዝግጅቱ ላይ ደግሞ ከ 2000 በላይ ተቋማት በላይ ተካፍለዋል። ጀርመናዉያን ኢቫንጌሊሸር  ኬርሽንታግ ሲሉ የሚጠሩት የወንጌላዊ ቤተ-ክርስትያን ክብረ በዓል አጀማመርን የሚነግሩን በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ኃላፊ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ናቸዉ።  

Deutschland 36. Evangelischer Kirchentag in Berlin - Barack Obama und Angela Merkel
የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የበዓሉ ተጋባዥ ነበሩ። ምስል picture-alliance/AP Photo/G. Breloer


«ጀርመናዉያን ኢቫንጌሊሸር ኬርሽንታግ የሚሉት የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀን የሚከበረዉ በየሁለት ዓመቱ ነዉ። ለዚህ በዓል መከበር መነሻ የሆነዉ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ነዉ። በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ጊዜ በአዉሮጳም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍላትም ጦርነት ተነስቶ፤ ብዙ ሕዝብ እንዳለቀ በተለይም ደግሞ አይሁዶች እንደተጨፈጨፉ የሚታወቅ ነገር ነዉ። ሆኖም ከዚህ ወዲህ ጦርነት ይብቃ በማለት የሰላም መልክትን ለማስተላለፍ በተለይ የጀርመን ወንጉጌላዊት ቤተ-ክርስትያን፤ አባቶች ፖለቲከኞች ታዋቂ ሰዎችን በማሰባሰብ ጦርነትን ለማብቃት ሰላም ለማምጣት ምንያስፈልጋል በሚል ሲነጋገሩ የጀመሩት ነዉ። ይህንም ቀን እስቲ ለማንኛዉም የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀን በማለት የሰላም ቀን እንሞክር ብለዉ ጀመሩት። ከዓመት ዓመት እየሰፋ እየታወቀ መጣ፤ እናም ዛሬ ይኸዉ ለ 36 ኛ ጊዜ ለማክበር በቅተናል። የዘንድሮዉ በዓል ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ላይ ተሃድሶ ያደረገበት 500ኛ ዓመት በመዋሉ አንድ ላይ ተከብሮአል። የበዓሉ መሪ ቃልም ደግሞ “አንተ እኔን አየኸኝ „ የሚል ነዉ።» የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ መላከ ገነት አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ እንደገለፁት በዓሉ የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን በዓል ይባል እንጂ በዚህ መድረክ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ሁሉ የሚነሱበት ነዉ። 

Berlin Kirchentag 2017 Dr. Thomas de Maiziere und Sheikh Ahmad Masaa al-Tayyeb
የጀርመን ሀገር አስተዳደር ሚኒስትር ቶማስ ዴ ሚዜር እና ሼክ አህመድ ማሳ በበዓሉ ላይ ምስል picture-alliance/Citypress24


«በዓሉ በባለቤትነት የወንጌላዊት ቤተክርስትያን በዓል ተብሎ ይዘጋጅ እንጂ በበዓሉ ላይ የሚቀርቡ ርዕሶችን ስናይ ሃይማኖታዊ ርዕሶች ብቻ አይደለም የሚነሱት። ማኅበራዊ ጉዳዮች፤ ፖለቲካ፤ ሃይማኖቱም ሰዎች የሚሳበት በዓል ነዉ። በዚህ በዓል ላይ የሚገኙትን የሚካፈሉትን ራሱ ስናይ የጀርመን ሃገርን ጨምሮ የሌሎች ሃገር መሪዎች ይገኛሉ። የሃይማኖት መሪዎችም እንደዚሁ ተገኝተዉ ከሕዝቡ ጋር በቀጥታ ዉይይት የሚያደርጉበት ልዩ ዝግጅት ነዉ። እና በዚህም በዓል በጀርመን የምትገኘዉ የኛ የኢትዮጵያዉያን ቤተ-ክርስትያንም ተጋብዛለች። በዝግጅቱ ላይ ቦታ ተሰጥቶን የኛን የሃገራችንን ሥነ- ጽሑፍ፤ ሥነ-ሕንጻ፤ ታሪክ ሃይማኖት ባህል ለማስተዋወቅ እድሉን አግኝተናል። የተጋበዝነዉ እና ብቻ ሳንሆን ሌሎችም፤ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችም ሥራዎቻቸዉን የሚያስተዋዉቁበት ልዩ አጋጣሚ ነበር። የተለያዩ የእምነት ድርጅቶችም እየተገኙ ይህንኑ ሁኔታ ለሕዝቡ የሚያስተዋዉቁበት ከሕዝብ ለሚቀርብ ጥያቄ መልስ የሚሰጡበት አጋጣሚ ነዉ ይህ በዓል። »   በተለይ በርሊን ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስትያን በዝግጅቱ ላይ ለየት ያለ ቦታ ተሰጥቶት ነበር የሰማነዉ ዝግጅቱ እንዴት ነበር? 

Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Tewahedo St. Immanuel-Kirche in Berlin
የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን መዘምራንምስል Leonard Bahr


« ከበዓሉ መክፈቻ ጀምሮ ከዝያም በኋላ መንገድ ላይ በተደረገዉ በዓል ላይ የባህል ምግብን በማቅረብ ቡና በማፍላት እንዲሁም ስለቤተ-ክርስትያናችን፤ እንዲሁም ስለሃገራችን የተለያዩ መረጃዎችን ለሰዎች በመስጠት ስለ ቤተ-ክርስትያናችን እየጠየቀ ተረድቶ አዉቆ የሄደበት ሁኔታ ነበር። በእዉነት ብዙ ሕዝብ ስለ እምነቱ ስለኢትዮጵያ የማወቅ ጉጉት እንዳለዉ ተረድተናል። ይህን ታሪክ ባህል የሰሙት ሰዎች ደግሞ ከዚህ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድና ለማየት ጉጉት እና ፍላጎት ያላቸዉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ተረድተናል። በተለይ ደግሞ እዚህ በርሊን አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ቅዳሜና እሁድ የሚከበር በዓል ስላለ የሰሙትን ለማየት በዝያ ፀሎቱን ለመከታተል ፍላጎቱ እንዳላቸዉ አይተናል። ሌላዉ የተሳተፍነት መዝሙር በማቅረብ ነዉ። ዜማችን የተለየ ነዉ። እዚህ አካባቢ ከሚደመጠዉ ዜማ የኛ ዜማ የተለየ ስለሆነ ፤ ሰፊ መድረክ ተሰቶን ስለነበረ፤ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን መዝሙር አቅርበዋል።»    

 
የዝግጅቱ ዋና ተጠሪ  ጀርመናዊትዋ ኤሌን ኡበርሼር ባደረጉት ንግግር እምነትና ፖለቲካ የሚራራቁ አይደሉም ብለዋል። 

«እምነትና ፖለቲካ የማይራራቁ ናቸዉ። በዚህ የቤተ-ክርስትያን በዓል እለት የተለያዩ  ፖለቲከኞች ለዉይይት ለንግግር በዚህ መድረክ ላይ መቅረባቸዉ አንድ ማረጋገጫ ነዉ። ዓለም በአንድ ላይ በማይራመድበት በአሁኑ ጊዜ  የቤተ- ክርስትያን ቀን በዓል ታዳሚዎች እንደ እንደ የራሳቸዉ አስተሳሰብና ግንዛቤ በአንድ ላይ መሆን መቻላቸዉን አስመስክረዋል። » 


ረዘም ላሉ ዓመታት በበርሊን ነዋሪ የሆነችዉ ቅድስት ወልደማርያም በዝግጅቱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ቡና እና ባህላዊ ምግብን ካቀረቡት ኢትዮጵያዉያት መካከል አንዷናት። 
« አቀራረባችንን ከሚጠብቁት በላይ ሆኖ ነዉ ያገኙት በጣም ብዙ ጥያቄዎችን ያቀርቡልን ነበር። የማስተዋወቁን ስራ ምግቡን ባህሉንም ሃይማኖቱንም፤ አንድ ላይ አድርገን ነበር ማስተዋወቅ የፈለግነዉ። መጀመርያም ለዚህ በዓል መድረክ ስንዘጋጅ ከሌላዉ ለየት ብለን መቅረብ አለብን ፤ በምናቀርበዉ ምግብ ብቻ ሳይሆን በአለባበሳችንም ከሌሎች ለየት ብለን መታየት አለብን ብለን ነበር የተነሳነዉ። የባህል ልብስ ለብሰን ነበር። የበዓሉ ታዳሚዎች ጥያቄ ይጠይቁ ነበር። ስለምግቡ፤ ስለወጡ፤ በምን እንደተሰራ፤ እንዴት መብላት እንዳለብን፤ ሁሉ ይጠይቁ ነበር። ቡና እየቆላን አፍልተን ነበር ስናጠጣ የነበረዉ። 
በቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጂኔሪግ ትምህርት ተመርቆ እዚሁ ትዳር ይዞ ከ 25 ዓመት በላይ የሚኖረዉ በላይ ደመረ የበርሊኑ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን ሌላዉ አገልጋይ ነዉ። 
« የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀን ነዉ። በዚህ ትእይንት ላይ በሺህ የሚቆጠሩ የሃይማኖት ተቋማቶች የተለያዩ ኤግዚቢሽኖችን ያሳዩ ነበር ። እኛም ከነሱ በጣም ብዙ የተማርነዉ ነገር አለ። በቤተ-ክርስትያን እምነት የተነሳ በተለይ ወጣቶችንና ልጆችን በትምህርት በጥልቅ አንጾ ማሳደግ የሚለዉ ላይ አልተሰራም። ይህም እንቅስቃሴ የጀመረዉ አሁን በቅርቡ ነዉ። ከዚህ መድረክ የተማርነዉ ነገር፤ ይበልጥ በዚህ ስራ እንድንቀጥል እና በተለይም እኛ ዉጭ የምንነኖር ሰዎች ያለብን ፈተና ብዙ ስለሆነ ፤ ከአገር ባህል ከቤተ-ክርስትያን እምነት አንጻር ያለዉ እንቅፋት ብዙ ስለሆነ እዝያ ላይ አጥብቀን መስራት እንዳለብን የተረዳንበት ሁኔታ ነበር።»   

Deutschland  36. Evangelischer Kirchentag - Wittenberg
ምስል picture alliance/dpa/S. Willnow


በዝግጅቱ ላይ ከተለያዩ የክርስትና ሃይማኖቶች ሌላ የሙስሊም ሃይማኖት፤ የቡዲዝም እናም ሌሎች የተለያዩ ተቋማቶች ተካፍለዋል።  የዝግጅቱ ዋና ተጠሪ  ጀርመናዊትዋ ኤሌን ኡበርሼር ባደረጉት ንግግር « ባለንበት በግሎባላይዜሽን ማለት በአፅናፋዊዉ የኤኮኖሚ ትስስር ስር ዓለም የተለያዩ እምነቶች ተነጣጥለዉ መጓዝ አይችሉም፤ ነገር ግን አንዱ ስለሌላዉ ሃይማኖት የሚያዉቀዉ በጣም በጥቂቱ ነዉ። የቤተ-ክርስትያን ቀን የክርስትና እና የሙስሊም ሃይማኖትን በማገናኘት የግንኙነት ድልድይ የሚገነባ ቀን ነዉ። »  


የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ መላከ ገነት አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ  እንደገለፁት ከዚህ ዝግጅት ብዙ ትምህርትን ቀስመናል ሲሉ ተናግረዋል።  
የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን መድረክ ተዘርግቶበት በነበረበት ቦታ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ የነበረዉና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይዩን ባንዲራን አገልድሞ መድረክ ላይ ከመዘምራን ጋር ተሰልፎ ሲያዜም፤ ታሪክና ባህልን ሲያስረዳ የነበረዉ ጀርመናዊዉ ሊዮናርድ ባህ ነዉ። ሊዮናርድ ታሪኩን እንዲህ ነግሮናል፤ 

Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Tewahedo St. Immanuel-Kirche in Berlin
ጀርመናዊዉ ዲያቆን ሊዮናርድ እና ዲያቆን ዳንኤልምስል Leonard Bahr


«እኔ የምንም ዓይነት እምነት ተከታይ አልነበርኩም፤ ወደ ቤተ-ክርስትያንም አልሄድም ነበር። ቤተሰቦቼ የወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን እምነት ተከታዮች ቢሆኑም እኔን ወደ እምነቱ አልወሰዱኝም። በክርስትናም አላስጠመቁኝም። የ15 የ 16 ዓመት ልጅ ሳለሁ ስለኢትዮጵያ ታሪክ፤ ስለ አጼ ኃይለስላሴ የማወቅ ጉጉት አደረብኝ። ስለኢትዮጵያ በጣም ብዙ የታሪክ መጻሕፍትን አንብብያለሁ። ስለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትም አንብያለሁ። ከዝያ ነዉ በእምነቱ ተስቤ ጀርመን ኮለኝ ወደሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን የሄድኩት። ወደ እምነት ተቋም ስሄድ የዝያን ጊዜዉ ለኔ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር።  ከዝያም መኖርያዬን ወደ በርሊን ቀይሪ በርሊን ወደ የሚገኘዉ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ-ክርስትያን በየጊዜዉ መሄድ ጀመርኩ።  ከዝያም  ነዉ ስለ ሃይማኖቱ ትምህርት ወስጄ በዓመቱ ማለት በጎርጎረሳዊዉ 2014 ዓ.ም መጋቢት ወር ክርስትና ለመነሳት የበቃሁት።»

      
«ወደ ኢትዮጵያ የሄድኩት አገሪቱን ሕዝቧን ታሪክዋን አኗኗሩን ቀረብ ብዬ ለማወቅ ስለፈለኩ ነዉ።  በተለይ በተለይ ደግሞ ባህላዊዉን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ትምህርት ቤት ለመጎብኘት ነበር። ማለት ባህላዊዉን የግዕዝ አነባበብ ዘዴ፤ የፀሎት ሥነ-ስርዓቱን  ለማየት ነበር፤ ወደዝያ የሄድኩት። እዝያም ሄጄ የህዕዝ አነባብ በመጠኑ፤ በከፊል ተምሪ ተመልሻለሁ። ይህን የጀመርኩትን ትምህርት ግን ተመልሼ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ መቀጠል እፈልጋለሁ። »

በጀርመን ዘንድሮ ለ 36 ኛ ጊዜ ሥለ ተካሄደዉ ስለ ጀርመን ወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን ቀን በዓል ምንነት ያየንበትን መሰናዶ እስከዚሁ ነበር። ቃለ-ምልልስ የሰጡንን ሁሉ በማመስገን ሙሉዉን ጥንቅር እንዲያደምጡ እንጋብዛለን። 

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ