1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የድንበር ቁጥጥር ውሳኔ

Eshete Bekeleሰኞ፣ መስከረም 3 2008

ጀርመን ከኦስትሪያ በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ ቁጥጥር ፣በቼክ ሪፐብሊክና ፖላንድ ድንበር አቅራቢያም ድንገተኛ ፍተሻ ማድረግ ጀመረች። በዚሁ እርምጃ እስካሁን 30 ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና 90ስደተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጀርመን ፖሊስ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1GWOO
Symbolbild - Grenzkontrollen Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe

[No title]

ጀርመን ከኦስትሪያ በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ የቁጥጥር ኬላዎች በማቆም በወቅታዊው የስደተኞች ቀውስ ላይ የአቋም ለውጥ አምጥታለች። ከሳምንት በፊት የጀርመኗ መራሔተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል የአገሪቱን ድንበር ለተገን ጠያቂዎች ከከፈቱ በኋላ የተከሰተው የስደተኞች ጎርፍ ያሳሰበው መንግስት ፍተሻና ቁጥጥር እንዲደረግ ለፖሊስ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ካለፈው ወር መገባደጃ ጀምሮ ከስልሳ ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ጀርመኗ ሙኒክ ከተማ ደርሰዋል። ተገን ጠያቂዎቹ በሙኒክ የባቡር ጣቢያ እስከ መተኛት መገደዳቸው ሁኔታው ለከተማዋም ሆነ በአጠቃላይ ለጀርመን ከአቅም በላይ ለመሆኑ ጠቋሚ ነው ተብሏል።

የድንበር ቁጥጥሩ ከተጀመረ በኋላ 30 ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና 90 ስደተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጀርመን ፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። የጀርመን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ዴ ሚዚዬር እርምጃው ለአገሪቱ ደህንነት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

« የዚህ እርምጃ ዓላማ አሁን ወደ ጀርመን በመጉረፍ ላይ የሚገኘውን ስደተኛ መገደብ ናየጉዞውም ሂደት የተስተካከለ እና በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ማድረግ ነው። ይህ ከፀጥታ ማስከበር አንፃርም አስፈላጊ ነው። ይህንን ነው የሻንጋይ የግድብ ስምምነትም በግልፅ ያስቀመጠው»

Deutschland Österreich Bahnhof Wien Flüchtlinge
ምስል Reuters/H. P. Bader

ጀርመን ወቅታዊውን የስደተኞች ቀውስ 28ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት በተለይም ምስራቃውያኑ በፍትሃዊነት ለመከፋፈል ያሳዩት ቸልተኝነት አሰላችቷታል። አገሪቱ የርስ በርስ ጦርነት ለሚሸሹት ሶርያውያንና የሌሎች አገራት ተገን ጠያቂዎች ተመራጭ መዳረሻ ነች።

የድንበር ቁጥጥር ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፖሊስ ሰራዊት በጀርመንና ኦስትሪያ ድንበር አቅራቢያ ቁጥጥሩን ጀምሯል። በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው የባቡር ምልልስ ለአስራ ሁለት ሰዓታት ቆሞ ነበር። ከቼክ ሪፐብሊክና ፖላንድ ድንበር አቅራቢያም ድንገተኛ ፍተሻ ይደረጋል ተብሏል።

ባለፉት 9 ወራት ብቻ 450,000ተገን ጠያቂዎች ወደ ጀርመን ገብተዋል። እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ ቁጥሩ ከዚህ በበለጠ ያሻቅባል የሚል ስጋት በመላ አውሮጳ ይደመጣል። የመንግሥት ውሳኔ በስደተኞች ለተጨናነቀችው ለደቡብ ጀርመንዋ የባየርን ፌደራዊ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትርና የጀርመን ክርስትያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ (CSU) የበላይ ሆረስት ዜሆፈር እፎይታ የሰጠ ይመስላል።

« በባየርን አሳሳቢነት ይህ የድንበር ቁጥጥር በመጀመሩ በጣም ደስተኛ ነኝ። ይህ ለመላው አለም እና ለፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክም ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል»

ውሳኔው ለምን ያህል ጊዜ ገቢራዊ እንደሚሆን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያሉት ነገር የለም።ምንም ይሁን ምን በቶማስ ደ ሚዚዬር በኩል የተደመጠው ውሳኔ ጀርመን ለመግባት ለሚያልሙት ተገን ጠያቂዎች የመርዶ ያክል ነው።

የጀርመንን ውሳኔ ተከትሎ ኦስትሪያና ስሎቫኪያ ወደ አውሮጳ የሚተሙትን ስደተኞች ለመቆጣጠር የድንበር ቁጥጥር እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል። ሐንጋሪ ከሰርቢያ የምትዋስንበትን የድንበር አካባቢ በሽቦ አጥር ከመከለሏ በተጨማሪ ወታደሮች ማሰማራቷን ሬውተርስ ዘግቧል። በወቅታዊው የስደተኞች ቀውስ ላይ ለመምከር በብራስልስ የከተሙት የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ መዘየዳቸው ከጅማሮው ጥያቄ ውስጥ ወድቆ ነበር። የጀርመን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ዴ ሚዚዬር ከጉባዔው በፊት «ከአንዳች የመፍትሄ ሃሳብ ስለመድረሳችን እርግጠኛ አይደለሁም።» ሲሉ ተናግረዋል።

Grenze Österreich Deutschland Grenzkontrolle Polizei
ምስል Reuters/Dominic Ebenbichler

የብሪታኒያ አገር ውስጥ ጉዳይ ዋና ፀሃፊ ቴሬሳ ሜይ እና የስሎቫኪያ አቻቸው ሮበርት ካሊናክ ወደ አውሮጳ የሚተሙትን ሰደተኞች በድርሻ የመከፋፈሉን ሃሳብ አጥብቀው እንደሚቃወሙ ከጉባዔው በፊት ተናግረዋል።

የጀርመን መንግስት ከድንበር ቁጥጥሩ በኋላም ተገን ጠያቂዎች ወደ አገሪቱ መግባት እንደማይከለከሉ ነገር ግን እንደ ቀደመው ሳይሆን በጥብቅ ስርዓት እንደሚሆን አስታውቋል። «ጊዜያዊ የድንበር ቁጥጥር ድንበርን መዝጋት አይደለም።» በማለት የተናገሩት የመራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ቃል አቀባይ ሽቴፈን ዛይበርት ነገር ግን የጸጥታ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሰዎችን ማንነት ማጣራት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐንጋሪ ስደተኞችን ያለምንም ምዝገባ በአውቶቡሶች ወደ ኦስትሪያ እየላከች መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ