1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን «ግሪን ካርድ» 15ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28 2007

ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ ለተማረ ወይም ሰለጠነ የውጭ የሰው ኃይል ልዩ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ መስጠት ከጀመረች 15 ዓመት ሆናት ። ይህ ልዩ ፈቃድ ግን ሃገሪቱ ትጠብቅ የነበረውን ያህል ብዙ ሙያተኞችን መሳብ እንዳልቻለ ነው የሚነገረው ።

https://p.dw.com/p/1G9YW
Archivbild Bundesarbeitsminister Walter Riester überreicht die erste deutsche Green Card
ምስል picture-alliance/dpa/M. Führer

የጀርመን« ግሪን ካርድ »15 ኛ ዓመት

በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት የተማረ የውጭ የሰው ኃይልን ለመሳብ ለተፈላጊዎቹ ሙያተኞች ልዩ የሥራና የመኖሪያ ፈቃድ ይሰጣሉ ። ይህን ከሚያደርጉት አንዷ ጀርመን ናት ።ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ ለሰለጠኑና በሃገር ውስጥ ምትክ ላልተገኘላቸው የውጭ ዜጎች ይህን ፈቃድ መስጠት የጀመረችው የዛሬ 15 ዓመት ነው ። በጎርጎሮሳ ዊው ነሐሴ 1, 2000 ዓም ሥራ ላይ የዋለው ይህ ደንብ የተደነገገው በጀርመንኛው ምህፃር BITKOM በመባል የሚጠራው የፌደራል ጀርመን የኢንፎርሜሽን ሳይንስ የቴሌኮምኒኬሽንና የአዳዲሶቹ የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪዎች ማህበር ለጀርመን መንግሥት ሚያዚያ 2000 ዓም የሠለጠነ የውጭ የሰው ኃይል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ነው ።በወቅቱ ማህበሩ ፣አሠሪዎች 30 ሺህ የውጭ ባለሞያዎችን እንዲቀጥሩ መንግሥት እንዲፈቅድ ነበር የጠየቀው ። ያኔ ተፈላጊዎቹ ባለሞያዎች የኮምፕዩተር ፕሮግራመሮችና መሠንዲሶች ነበሩ ።በወቅቱ በዘርፉ 75ሺህ የመስኩ ባለሞያዎች እጥረት እንዳለ ይገመት ነበር የጀርመን መራሄ መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር ጥያቄውን በመቀበል በሞያቸው የሚፈለጉ የውጭ ዜጎች ጀርመን ውስጥ እስከ አምስት 5 ዓመት መሥራት የሚያስችላቸው ፈቃድ እንደሚሰጥ በዚያው ዓመት በተካሄደው የሃኖቨሩ የኮምፕዩተር የንግድ ትርዒት ላይ አሳወቁ ። ሽሮደር ይህን ባሉ በ5 ወሩ እጅግ ያስፈልጋሉ ለተባሉት ባለሞያዎች ጀርመን ልዩ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ መስጠት ጀመረች ። ። በዚያን ጊዜ ክፍት የስራ ቦታዎችን የሚሻሙ ሩስያውያን ቡልጋርያውያን ህንዶችና የሌሎችም ሃገራት ዜጎች ወደ ጀርመን ይጎርፋሉ የሚል ግምት ነበር ። መንግሥት ለጊዜው ለ20 ሺህ የውጭ ዜጎች ነበር ፈቃድ ለመስጠት የተዘጋጀው ። ይሁንና 17,9831 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሞያዎች ብቻ ነበሩ እድሉን ተጠቅመው ጀርመን ለመሥራት የመጡት
የዛሬ 15 ዓመት ሽሮደር የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ባየለበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሥራ መስኮች የውጭ ዜጎች እንዲሰማሩ መፍቀዳቸው የጀርመንን ህዝብ ከፍተኛ ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ከቶ ነበር ።በጀርመን ቁጥሩ 4 ሚሊዮን የሚደርስ ሥራ አጥ በነበረበት በዚያን ወቅት የውጭ ዜጎች አስገብቶ ማሠራቱን ብዙዎች በቀላሉ ሊቀበሉት አልቻሉም ።የበርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሠራተኛ ማህበራት እንዲሁም የሽሮደር ፓርቲ አባላት ሶሻል ዲሞክራቶችም ጀርመን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትን ድንበር ሳትሻገር ልትፈታው እንደማትችል ለመረዳት ብዙ ጊዜ ወስዶባቸዋል ።የብዙዎቹ ፍላጎት ክፍት የሥራ ቦታዎች በወጣት ጀርመናውያን እንዲያዙ ነበር ።
የዛሬ 15 ዓመት ሥራ ላይ የዋለው የጀርመን ግሪን ካርድ አሰጣጥ ደንብ የአውሮፓ ህብረት አባል ካልሆነ ሃገር የሚመጡሙ ሙያቸው የሚፈለግ የውጭ ዜጎች በአንድ ሳምንት ውስጥ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ ይረዳል ። ሆኖም ባለሞያዎቹ የመጀመሪያውን ፈቃድ የሚያገኙት ለሠወስት ዓመት ነው ። ሶስቱን ዓመት ከጨረሱ በኋላ ነው የቀሪው ሁለት ዓመት ፈቃድ የሚሰጣቸው ባለሞያዎቹ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የዪኒቨርስቲ ዲግሪ ወይም ዓመታዊ ደሞዛቸው 50 ሺህ ዩሮ ለመሆኑ ማረጋገጫ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። ደንቡ ግሪን ካርድ ላገኙ ሰዎች የግል ሥራ ማቋቋም አይፈቀቅድም ነበር ። ቤተሰቦቻቸውም ጀርመን ውስጥ ወዲያውኑ መሥራት አይችሉም ።እነዚህ ገደቦች እንዲሁም ህብረተሰቡ ለውጭ ዜጎች ያለው አመለካከት በወቅቱ የተጠበቁትን ያህል የውጭ ዜጎች ጀርመን ላለመምጣታቸው ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል ።
የጀርመኑ ግሪን ካርድ ከአምስት ዓመት በኋላ ማለት በጎርጎሮሳዊው 2005 በአዲስ የኢሚግሬሽን ህግ ተተክቷል ። ይህ ህግ ከቀደመው የጀርመን ግሪን ካርድ ህግ አነስተኛ ለውጥ ነው የተደረገበት ። በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይልን ና ሳይንቲስቶችን ወደ ጀርመን የሥራ ገበያ ይበልጥ ለመሳብ ያለመ ው ይኽው የተሻሻለው ህግ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የዩኒቨርስቲም ሆነ የፖሊቴክኒክ ዲግሪ ያላቸው ሙያተኞች ወደ ጀርመን እንዲገቡ ይፈቀዳል ። ለመነሻ 250 ሺህ ዩሮ መወረት ና ቢያንስ ለ5 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችሉ የውጭ ዜጎች በግል ሥራ እንዲሰማሩም ይፈቅዳል ። ከዚህ ሌላ ከጀርመን ዩኒቨርስቲዎች ዲግሪ ያገኙ የውጭ ዜጎች አንድ ዓመት ጀርመን ውስጥ በሙያቸው ሥራ እንዲፈልጉም እድል ይሰጣቸዋል ። ከጎርጎሮሳውያኑ ሚያዚያ 2012 ወዲህ ደግሞ የጋራው የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ብሉ ካርድ በጀርመንም ሥራ ላይ ውሏል ። ፈቃዱን ለማግኘት አመልካቾች እውቅና የተሰጠው ዲግሪና በዓመት ቢያንስ 46 ሺህ ዩሮ የሚያስገኝ የሥራ ውል ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ።አመልካቾቹ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ መሐንዲሶች ሳይንቲስቶች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሙያተኞች እና ሐኪሞች ከሆኑ ደግሞ ዓመታዊ ደሞዛቸው ቢያንስ ወደ 37,752 ዝቅ ሊል ይችላል ።የብሉ ካርድ ገደቡ 4 ዓመት ነው ።
ከጎርጎሮሳውያኑ 2014 ወዲህ ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ህገ ወጥ በሚባል መንገድ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ጨምሯል ። ጀርመን ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ብዙዎች ለስደት የሚመርጧት ሃገር ናት ። በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ውስጥ 24o ሺህ ተገኝ ጠያቂዎች አሉ ። ከነዚህ አመላካቾችም ሁለት ሶስተኛው የተማሩ እንዳልሆኑ ቢገመትም ከመካከላቸው ጀርመን ውስጥ ተፈላጊ በሆኑ ሙያዎች የሰለጠኑና በቂ ልምድም ያላቸውም ይገኙበታል ።ከነዚህም አንዱ በከወራት በፊት ከሶሪያ ወደ ጀርመን የተሰደደው ኒዛር አል ማሃመድ ነው ።አል ማሃመድ በርሊን ውስጥ በሚገን አንድ የቋንቋ ትምሕርት ቤት ጀርመንኛ የሚማር ተገን ጠያቂ ነው ። አል ማሃመድና በትምህርት ቤቱ ቋንቋ የሚማሩ ሌሎች ስደተኞች የተማሩ ናቸው ። ከ7 ወራት በፊት ከሶሪያው የርስ በርስ ጦርነት ሸሽቶ ጀርመን የገባ ናዚር አል አህመድ በሙያው ሐኪም ነው ።ተገን እንዲሰጠው አመልክቶ የሚጠብቀው አል ማሃመድ ጥገኝነት እስኪሰጠው ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ አሁን በሙያው መስራት ነው የሚፈልገው ።
«አዎን አውቃለሁ ። እዚህ ጀርመን የሐኪሞች እጥረት እንዳለ አውቃለሁ ።ሐኪሞች ትፈልጋላችሁ። በሐኪምነት ወይም በረዳት ሐኪምነት ለመሥራት ሳመለክት መጀመሪያ ማረጋገጫ ያስፈልግሃል ይሉኛል ።»
ጀርመን ከሚገኙ 5 ስደተኞች አንዱ ጀርመን ውስጥ በሚፈለጉ ሙያዎች የሰለጠነ ምሁር ነው ። ከዚህ በመነሳትም የፌደራል ጀርመን የሥራ ቀጣሪ መሥሪያ ቤት ለነዚህ ስደተኞች ባልተወሳሰበ ሁኔታ የሥራ ፈቃድ ማለትም BLUE CARD እንዲሰጥ ይፈልጋል ። መስሪያ ቤቱ እነዚህ በሃገራቸው በሚካሄድ ጦርነትና የፖለቲካ ጫና ምክንያት እንደ ሌሎች ሃገራት ዜጎች ከሃገራቸው ለብሉ ካርድ ማመልከት ያልቻሉት ሰዎች እዚህ እድሉ እንዲሰጣቸው ጠይቋል ። ይህም በተቃዋሚው የጀርመኑ አረንጓዴ ፓርቲ የሚደገፍ ሃሳብ ሆኗል ። በጀርመን ፓርላማ የፓርቲው ተወካዮች ሊቀመንበር አንቶን ሆፍ ራይተር ይህ ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርበው እንዲኖሩ የሚያደርግ ጥሩ መፍትሄ ነው ብለዋል ።
« ጥገኝነት ጠያቂ ለብሉ ካርድ ማመልከት የሚችለው ጥሩ ስልጠና ወይም የትምህርት ደረጃ ያለው የተሰደደው በርስ በርስ ጦርነት ና በመሳሰሉ መሆኑን ማረጋገጥ ለሚችል ነው ። ይህ ፈጥኖ ሥራ ለማግኘትና ለመዋሃድ ሉሮ ለመመሥረትም ይረዳል ።»
ይሁንና ጀርመን ውስጥ ለተገን ጠያቂዎች ይህን መሰሉ ፈቃድ እንዲሰጥ የቀረበው ጥያቄ የተገን ጠያቂውን ቁጥር ያበራክታል የሚል ክርክር አስነስቷል ። ይህን መከራከሪያ የሚቃወሙ ወገኖች ደግሞ ከስደተኞቹ የብሉ ካርድን መስፈርት የሚያሟሉት ጥቂቶች በመሆናቸው ይህ ሊያሳስብ አይገባም ይላሉ ። ሃሳቡን የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር ዚግማር ጋብርየልም አልተቀበሉትም ። ሃሳቡ ጥሩ አይደለም ያሉት ጋብርየል ሃገሪቱ ሰዎችን የምታስጠጋበትን መሠረታዊ ምክንያት አስገንዝበዋል ።
«ለሰዎች ጥገኝነት የምንስጠው የሰለጠነ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልገን አይደለም ። ይልቁንም እነርሱ ክትትል ስለሚደረግባቸው በሃገራቸውም በህይወት የመኖር እድል ስለሌላቸው ነው ።»
ስለ ብሉ ካርድ የሚካሄደው ፖለቲካዊ ክርክር እንደቀጠለ ነው ። ኒዛር ለክርክሩም ሆነ ጥገኝነት ስለ ማግኘቱ ደንታ የለውም ። ለምን ቢባል የርሱ ዋነኛ ፍላጎት ጀርመን እንደ ልቡ ተንቀሳቅሶ መሥራት መቻሉ ብቻ ነው ።
«ጀርመን ጥገኝነት ማግኘት አለማግኘቴ ለኔ አስፈላጊ አይደለም ። አንድ ሰው ጀርመን ውስጥ ተንቀሳቅሶ መሥራት መቻሉ ለኔ ጠቃሚው ጉዳይ ነው ። የወደፊት ህይወቴንም እዚህ ነው ማስተካከል የምፈልገው ።
ጀርመን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመሳብ የተከተለችው መንገድ እንደተጠበቀው ውጤታማ አለመሆኑ ነው የሚነገረው ።በመስኩ የተሰማሩ ባለሞያች ሃገሪቱ ተፈላጊ ሙያተኞችን ለመሳብ ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል ይላሉ።ከዚሁ ጎንም መንግሥት ተገን ጠያቂዎች ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ቢፈቅድ እነርሱን ለማቆየት የሚያወጣውን ገንዘብ መቀነስ እንደሚያስችለውም ነው የሚመክሩት ።

Afrikanischer Doktorand
ምስል Fotolia/michaeljung
Deutschland Fachkräfte Fachkräftemangel Deutsch-indisches Joint-Venture in Dresden
ምስል picture-alliance/dpa
Fachkräften aus Indien
ምስል picture-alliance/dpa
Afrikanischer Arzt mit Kollegen
ምስል Fotolia/Minerva Studio

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ