1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩርዲስታን ወታደሮችንም ያሰለጥናል

ዓርብ፣ የካቲት 30 2010

የባግዳድ  እና የኢርብል ጠላቶች የሚያዟቸዉን ተፋላሚ ወታደሮች እኩል ማሰልጠን እንዴት ይቻላል? አንዳዶች ሥልጠናዉ ሁለቱን ጠላቶች ለማቀራረብ ሊረዳ ይችል ይሆናል ይላሉ።ለብዙዎች ግን ከባድ ነዉ

https://p.dw.com/p/2u46t
Irak Bnaslawa nahe Erbil Ausbildung der Peshmerga durch die Bundeswehr
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

Bundeswehr im Irak - MP3-Stereo

በስድት ሐገራት የሠፈረዉ የጀርመን ጦር በያለበት የሚቆይበት ጊዜ እንዲራዘም ተሰናባቹ የሐገሪቱ ካቢኔ ወሰነ።ካቢኔዉ ባለፈዉ ሮብ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት አፍቃኒስታን የሠፈሩት የጀርመን  ወታደሮች ቁጥር ከ980 ወደ 1300 ከፍ ይላል።እራሱን የኢራቅ እና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት  (ISIS) ብሎ የሚጠራዉን አሸባሪ ቡድን ለመዉጋት ኢራቅ የሠፈረዉ ጦር ወደ 800 ዝቅ ይላል።የጦሩ ተልዕኮም የኢራቅ ጦርን በማሰልጠን ላይ ያተኩራል።ጦሩ እስካሁን የሚያሰለጥነዉ ፔሽ ሜርጋ የሚባለዉን የኩርዲስታንን ጦር ብቻ ነዉ።የጀርመን ጦር አዲሱ የኢራቅ ተልዕኮ ፈታኝ፤ ምናልባትም አወዛጋቢ ይሆናል ተብሎ እየተነገረ ነዉ።ኬርሽተን ክኒፕ ያጠናቀረዉ ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አዘጋጅቶታል።
ኢራቅ የሠፈረዉ የጀርመን ጦር ተልዕኮ፤ ARD ተብሎ የሚጠራዉ የጀርመኑ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበዉ፤ የኢራቅ ጦርን የዉጊያ ብቃት ማዳበር፤ ፈንጂ የማምከን ችሎታዉን ማጠናከር፤ የዕዝ መዋቅር ግልፅነትን ማስረፅ፤ የሎጂስቲክስ እና የሕክምና አቅምን ማደርጀት ነዉ።ተልዕኮዉ አሰልጣኞችን በማሰልጠን ላይ ያተኮረ ነዉ ተብሏል።የጀርመን ጦር የኢራቅን ብሔራዊ ሠራዊት እንዲያሰለጥን ጠያቂዉ የኢራቅ መንግሥት ነዉ።
በቅርቡ ኢራቅን የጎበኙት መከላከያ ሚንስትር  ኡርዙላ ፎን ዴር ላይን እንዳሉት ደግሞ ለወታደሮቹ ሥልጠና የጠየቀዉ የባግዳድ መንግሥት ብቻ ዓይደለም በሰሜናዊ ኢራቅ መንግስት አከል አስተዳድር ያቆመዉ የኩርዲስታን ግዛት ጭምር እንጂ።
                                   
«የኩርዲስታን አስተዳደርም፤ የባግዳድ ማዕከላዊ መንግስትም፤ የሚንስትር መስሪያ ቤቱን ዳግም በማዋቀሩ ሒደት እና በሥንቅና ትጥቅ አደረጃጀት እንድንረዳቸዉ ጠይቀዉናል።ኢራቅን ለዘለቄታዉ ለመረጋጋት የሚጠቅሙ ጉዳዮችን ማጠናከር፤ በራሱ የሚተማመን፤ ታማኝ እና ፈጥኖ መንቀሳቀስ የሚችል ጦር ኃይል ማደራጀት አስፈላጊ ነዉ።ይሕን ለማድረግ ጀርመን ኃላፊነቷን ትወጣለች።»
የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያ መሪዎች ኢራቅን ከወረሩ ከ1995 ወዲሕ አረባዊቱ ሐብት ሐገር ወድማለች።በኃይማኖት ሐራጥቃ ሱኒና ሺዓ፤ በጎሳ አረብ እና ኩርድ እየተባለ ተከፋፍላለች።ኩርዶች በብዛት የሚኖሩባት የሰሜናዊ ኢራቅ ግዛት ሕጋዊ እዉቅና አይኑረዉ እንጂ የምትገዛዉ ከመንግሥት ባልተናነሰ አስተዳድር ነዉ።ስሟንም ኩርዲስታን ብለዉታል።
ባለፈዉ መስከረም በተደረገዉ ሕዝበ ዉሳኔ የግዛቲቱ ሕዝብ ዘጠና ከመቶ በሆነ ድምፅ የግዛቲቱን ነፃነት አፀደቀ ተብሎ ነበር።የኢራቅ ጦር፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ኃያሉ ዓለም አከሸፈዉ እንጂ መሽዑድ ባርዛኒና ተባባሪዎቻቸዉ ነፃነት ለማወጅ ወስነዉም ነበር።
GIGA በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርመን ጥናት ተቋም የበላይ ኃላፊ ሔነር ፉርቲግ እንደሚሉት ኩርዶች አሁንም ቢሆን አለቅጥ የተለጠጠዉ የራስ ገዝ አስተዳደራቸዉ እንዲነካ አይፈልጉም።
                         
«(ኩርዶች) የራሳቸዉ ፓርላማ አላቸዉ።ሕጋዊ እዉቅና ባይኖረቸዉም እራሳቸዉን ያስተዳድራሉ።አነሰም በዛ የራሳቸዉ የሕግ ሥርዓት አላቸዉ፤ ነዳጅ ዘይትም ወደ ዉጪ ይልካሉ።የራሳቸዉ ጠረፍ ጠባቂ ጦር አላቸዉ።ፔሽሜርጋ የሚባል  ጦርም አላቸዉ።እነዚሕ ነገሮች እንዳሉ እንቂቀጥሉ፤ ቀስበቀስ እንዲጠናከሩም ይፈልጋሉ።»
የጀርመን ጦር እስካሁን ድረስ የኩርዶቹን ፔሽሜርጋ ጦር እያሰለጠነ ነዉ።ሥልጠናዉ አክራሪዉን ደፈጣ ተዋጊ ISISን ለመዉጋት ጠቅሟል ነዉ የሚባለዉ።የመጨረሻዉ ዙር ሥልጠና የፊታችን ሰኔ ማብቂያ ይጠናቀቃል ነዉ የሚባለዉ።ይሑንና ባዲሱ ሥልጠናም የኩርዶች ጦር ይሳተፋል ነዉ የተባለዉ።ይኽ ነዉ የአስልጣኙ ጦር ታላቅ ፈተና።የባግዳድ  እና የኢርብል ጠላቶች የሚያዟቸዉን ተፋላሚ ወታደሮች እኩል ማሰልጠን እንዴት ይቻላል? አንዳዶች ሥልጠናዉ ሁለቱን ጠላቶች ለማቀራረብ ሊረዳ ይችል ይሆናል ይላሉ።ለብዙዎች ግን ከባድ ነዉ።የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የዉጪ መርሕ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኦሚድ ኑሪፖር ወታደራዊ ሥልጠናዉ የሱኒ፤ የሺዓ፤የኩርድ ጦር እየተባለ መሰጠት የለበትም ባይ ናቸዉ።የኢራቅ ጦር ተብሎ የጦሩን አንድነት መጠበቅ አለበት እንጂ።
ተሰናባቹ የአንጌላ ሜርክል ካቢኔ ደቡብ ሱዳን እና ማሊ የሰፈረዉ የጀርመን ጦር በየአለበት እንዲቆይ ወስኗል።

Symbolbild - Bundeswehr bildet kurdische Peschmerga aus
ምስል Bundeswehr/Florian Räbel/dpa
Bundesverteidigungsministerin Ursula von der Leyen Auf dem Weg nach Irak
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ