1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት እና ሱዳን

ሐሙስ፣ ግንቦት 19 1996

የሱዳን መንግሥትና የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ጦር ኤስ ፒ ኤል ኤ ዓማፅያን የሀያ አንድ ዓመቱን የርስበርስ ጦርነት ለማብቃትና ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት የሚያስችላቸውን የሰላም ውል በትናንቱ ዕለት በኬንያ መዲና ናይሮቢ አቅራቢያ ናይቫሻ ተፈራረሙ።

https://p.dw.com/p/E0ky

ይህ በዚህ እንዳለ፡ የርስበርሱ ጦርነት ባዳቀቀው የሀገሪቱ ከፊል ጊዚያዊ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መጥቶዋል፤ ይሁንና፡ ይኸው ሁኔታ በቅርቡ ሊሻሻል እንደሚችል የጀርመናውያኑ ምግብ ድርጅት ተወካዮች ተስፋቸውን ትናንት ከበርሊን ገልፀዋል። የጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት ቡንድስታክም የሱዳንን ጊዚያዊ ሁኔታ አስመልክቶ ትናንት ሰፋ ያለ ክርክር አካሂዶ ነበር።

የጀርመናውያኑ ምግብ ድርጅት በሱዳን የምግብ ርዳታ ክፍፍሉን የሚጀምርበትን ፈቃድ አሁን ከሱዳን መንግሥት በጽሑፍ ያገኘበት ድርጊት ለደቡባዊ ሱዳን ሕዝብ የመጀመሪያውን የተስፋ ጭላንጭል ፈንጥቆዋል። ሁኔታዎች በቅርቡ ሊሻሻሉ መቻላቸውን አህም ገና በጥርጣሬ የሚመለከቱት የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ሀንስ ዮአኺም ፕሮይስ እንዳመለከቱት፡ ድርጅታቸው ባለፈው ወር በምዕራባዊ የሱዳን ከፊል ወደምትገኘው የኩቱም ከተማ አንድ ሺህ ቶን የምግብ ርዳታ አድርሶ በመጠባበቅ ላይ ነው። ከሱዳን ውጭ ያከማቸውን አሥራ አራት ሺህ ቶን የርዳታ እህልንም በቅርቡ ለተችገሩት ሱዳናውያን ማድረስ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልፀዋል።

የጀርመናውያኑ የምግብ ድርጅት ከዓለም የምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር በደቡብ ሱዳን ግዙፍ ሰብዓዊ መቅሠፍት እንዳይፈጠር ለማከላከል ይሞክራል። ባካባቢው የሚገባው መጪው የክረምት ወራት የርዳታ ክፍፍሉን ሥራ አዳጋች ሊያደርገው ወይም ከናካቴው ሊያኣስቆመ የሚችልበት ሥጋት መደቀኑን ነው ፕሮይስ ያስረዱት። እእየከፋ የሄደውን የሱዳን ጊዚያዊ ሁኔታ አስመልክቶ የጀርመናውያኑ ፌዴራዊ ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ክርክር ላይ የሶሻል ዴሞክራቶቹና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች በጋራ አንድ ማመልከቻ አቅርበው፡ ይኸው ማመልከቻቸው የምክር ቤቱን እንደራሴዎች ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ሊያልፍ ችሎዋል። በቀረበው ማመልከቻ መሠረት፡ የሱዳን መንግሥት ወደፊት የምግቡን ርዳታ ክፍፍል እንዳያከላክል ተጠይቆዋል፤ የአውሮጳ ኅብረትም የአፍሪቃ ኅብረት ለሚያካሂዳቸው የሰላም ተልዕኮዎች ፊናንስ ነኩን ርዳታ እንዲሰጥ ሀሳብ ቀርቦዋል። የተ መ ድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የሱዳን መንግሥት በዳርፉር አካባቢ የሚንቀሳቀሱት ሚሊሺያዎች የጦር መሣሪያ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ስምምነቱን ይሰጥ ዘንድ ትናንት ያሳሰበበትን ጥያቄ የምክር ቤቱ እንደራሴዎች ደግፈዋል። ከዚህ ጎንም፡ የጀርመን ኤኮኖሚ ተራድዕ ሚንስትር ቪችሶሬክ ሶይል በሱዳን መንግሥት ላይ የጦር መሣሪያ ዕገዳ እንዲያርፍ ጠይቀዋል። ይህንኑ ዕገዳ የአውሮጳ ኅብረት ካሳረፈ ሰንበት ማለቱን ሚንስትርዋ በማስታወቅ፡ የተ መ ድ ቢያንስ ተመሳሳዩን ርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የሱዳን መንግሥት ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ ለሱዳን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ሊያኣውቅ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል። ቪችሶሬክ ሶያል በዚሁ ጊዜ ካለፉት ብዙ ወራት ወዲህ አዳጋችና አደገኛ ቢሆንም ለተቸገረው የሱዳን ሕዝብ ርዳታ ለማቅረብ የሞከሩ ድንበር የማይገድባቸው የሐኪሞች ድርጅት፡ የጀርመናውያኑ ቴክኒክ ድርጅትና የተ መ ድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤትን የመሳሰሉ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን አመሥግነዋል።