1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ፕሬዚደንት የጃፓን ጉብኝት

ረቡዕ፣ መጋቢት 28 1997

የጀርመን ፕሬዚደንት የጃፓን ጉብኝታቸውን ዛሬ በኮበ ከተማ አበቁ። ከለር በዚሁ ጉብኝታቸው ወቅት የጀርመንን ገፅታ በጃፓን ኅብረተ ሰብ ዘንድ በይበልጥ ለማስተዋወቅ ሞክረዋል።

https://p.dw.com/p/E0ep
የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ከለር እና የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ዩኒኺሮ ኮይዙሚ
የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ከለር እና የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ዩኒኺሮ ኮይዙሚምስል AP

እርግጥ፤ ጃፓናውያኑ የጀርመንን የዕድገት ደረጃ በሚገባ ቢያውቁም፡ ስለጀርመን ያላቸው አመለካከት ቀዝቀዝ ያለ ነው። ይህንን ለመለወጥ ሲባል ጀርመን በጃፓን በወቅቱ በከፈተችውና አንድ ዓመት ሙሉ በሚቆየው ትርዒት ኤኮኖሚዋን እና ባህልዋን ብቻ ሳይሆን፡ የአኗኗር ዘዴን፡ ፋሽን፡ ሥነ ጥበብ እና ሙዚቃን የመሳሰሉ የተለያዩ የኑሮ ዘርፎችን በተለይ ለወጣቱ የጃፓን ኅብረተ ሰብ ታስተዋውቃለች።


በጀርመን አኳያ ያለው ወዳጃዊው አመለካከት ሰሞኑን የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ከለር በቶክዮ የጀርመን ዓመት የተሰኘው ትርዒት መልካም ጅምር እንዲያገኝ ረድቶዋል፤ ይህ ሁኔታ እንዲሁ እንዲቀጥል ከተፈለገም ተግቶ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ጀርመናዊው ርዕሰ ብሔር አመልክተዋል። ሁለቱን ሀገሮች የሚያመሳስሉዋቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ያስታወሱት ከለር በሁለቱም ሀገሮች የኤኮኖሚያዊው ዕድገት ላይ ዝግመት መታየቱን፡ ብዙው የሁለቱ ሀገሮች ኅብረተ ሰብ ከፊልም እያረጀ መሄዱን እና የተሐድሶው ለውጥም ከብዙ ጥረት በኋላ መነቃቃቱን ከለር አስታውቀዋል። ይሁንና፡ ጀርመን በአዳጋች ጊዜ ከጃፓን ትምህርት ልትቀስም እንደምትችል ከለር በማስረዳት፡ « በአዳጋች የኤኮኖሚያዊ ዕድገት ወቅት፡ በምርምሩ ሥራ ላይ ቁጠባ አለማድረጉ ለኤኮኖሚ ዕድገት እና አዳዲስ የሥራ ቦታ ለመክፈት፡ ማለትም የቀጣዩ ትውልድ የወደፊት ዕጣ ለማስተካከል የሚያስፈልገውን አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር አስችሎዋል፤ ነበር ያሉት። በውጭ ፖለቲካ ሂደትም ላይ ጃፓንና ጀርመን የዓለሙን መንግሥታት ድርጅት ለማጠናከር ባንድነት እንደሚሠሩ፡ እንዲሁም ሁለቱም ተሐድሶ በሚደረግበት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ጃፓን በእሥያ ከቻይና ጎን ዋነኛዋ የጀርመን የንግድ ተጓዳኝ የሆነችበት ድርጊት ለሀገራቸው የያዘውን ትርጓሜ ከለር በማመልከት በአውሮጳም ጀርመን ዋነኛዋ የጃፓን የንግድ ተጓዳኝ መሆናን ገልፀዋል። ይህ አነጋገራቸው አስተናጋጆቻቸውን ጃፓናውኣይን ቢያረጋጋም፡ የጀርመን ትኩረት ካለፉት ዓመታት ተፋጣኙን የኤኮኖሚ ዕድገት ማሳየት በያዘችው ቻይና ላይ ማረፉ የማይካድ ሐቅ ነው።
የጀርመን ፕሬዚደንት በጃፓናዊትዋ የአይቺ የተከፈተውን የዓለም ሀገሮች የተሳተፉበትን የኤክስፖ ትርዒት ጎብኝተዋል። በዚሁ ትርዒት ላይ ጀርመንና ፈረንሣይ በኤክስፖ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርቶቻቸውን በአንድ አዳራሽ ለእይታ አቅርበዋል። ጀርመን ከሌሎች ምርቶች ጎንም ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆነውን ከፍተኛ ሥነ ቴክኒክ በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።