1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኖች የግፍ ታሪክ በናሚቢያ

ዓርብ፣ ግንቦት 28 2007

ጀርመን ከ 100 ዓመት በፊት በኦቶማን ቱርክ በ1,5 ሚሊዮን አርመናውያን ላይ የተፈፀመው ግድያ «የዘር ማጥፋት ድርጊት» ነው ስትል በይፋ ተቀብላለች። የጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ ቡንድስታግ ግን በጀርመን ቅኝ አገዛዝ ስር በነበረችው ባሁኗ ናሚቢያ በሄሬሮ ብሔር ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መካሄዱን አልተቀበለውም።

https://p.dw.com/p/1FbQF
Deutsches Reich Kolonialgeschichte Genozid an den Hereros
ምስል public domain

[No title]

ፖለቲከኞች እና የናሚቢያ ሰለባዎች ተወካዮች ግድያው የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን ለጀርመን በይፋ ለመቀበል ትክክለኛው ጊዜ አሁን መሆኑን አመልክተዋል።

« ጀርመን ግልጽ አቋም መውሰድ እና ሰለባዎቹን ከሚወክሉት ማህበራትም ጋ ግንኙነት መፍጠር አለባት። ለአርመናዊያኑ የሰጠችውን ዓይነት ትኩረት ለኛም ልትሰጥ ይገባል። »

ይህን የሚሉት በርሊን የሚገኙት የሄሬሮ ተወላጅ የሰለባዎቹ ተወካይ እስራኤል ካውናቲይኬ ናቸው። ጀርመን በናማ፣ ዳማራ እና ሳን ብሔሮች ላይ የተፈፀመው ግድያ የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን አምና መቀበል እንደለባት አሳስበዋል። ካውናቴኬ ይህን አቋም የያዙት ብቸኛው ሰው አይደሉም፣ በተለይ የጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ ቡንድስታግ በአርመናውያን ላይ የዘር ማጥፋት ድርጊት ተፈፅሞዋል በሚል አንድ ይፋ አቋም ከወሰደ ወዲህ የ አባባልን የሚጋሩት ድምፆች እየተበራከቱ መጥተዋል። የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጊዜ አይሽረውም በሚል ካውናትዬኬ ከብዙ ዓመታት ጀምረው በሄሬሮ ላይ የተፈፀመው ግድያ እንደ ዘር ማጥፋት ድርጊት እንዲታይ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል። እስካሁን ይህ ያልሆነበትን ድርጊት በብሔራቸው አንፃር እንደተፈፀመ የአድልዎ ተግባር እና ለሰለባዎቹ ክብር እንደመንፈግ እንደሚመለከቱት አስታውቀዋል።

Herero Israel Kaunatjike
እስራኤል ካውናቲይኬምስል picture-alliance/dpa

የጀርመን ጦር ነበር የ20ኛው ምዕተ ዓመት የመጀመሪያ የዘር ማጥፋት ወንጀል እአአ በ1904 ዓም በቀድሞዋ ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ በዛሬዋ ናሚቢያ ያካሄደው። በዚሁ አባባል የታሪክ ምሁራን እና የተመድ ይስማሙበታል። ጀርመናዊው ጀነራል ሎታር ፎን ትሮታ በዚያን ጊዜ የሄሬሮ ብሔር አባላት በቅኝ ገዢው አንፃር ዓመፅ ያነሱበትን ድርጊት ለመደምሰስ ባካሄዱት የጥቃት ዘመቻ ወደ 70,000 የሚጠጉ፣ ማለትም ከብሔሩ ተወካዮች መካከል 80%ን የሚሸፍኑት እና ግማሹን የናማ ብሔር አባላትን ተገድለዋል። ይህንኑ ግድያ የተመድ እአአ በ1948 ዓም የዘር ማጥፋት ወንጀል ብሎ ቢጠራውም፣ ጀርመን እስከዛሬ እንደ ዘር ማጥፋት ወንጀል መቀበሉ አዳግቷታል።

Herero-Aufstand 1904 Ausschnitt aus der Abschrift des Schießbefehls Trothas
የጀነራል ሎታር ፎን ትሮታ በጥይት ደብድቦ የመግደል ትዕዛዝምስል Bundesarchiv/R 1001/2089

የቀድሞዋ የጀርመን የልማት ትብብር ሚንስትር ሀይደማሪ ቪችሶሬክ ሶይል ከ11 ዓመት በፊት ናሚቢያን በጎበኙበት ጊዜ በሄሬሮ ብሔር ላይ ለተፈፀመው ለጅምላው ግድያ እንደ መንግሥት ተወካይ ይቅርታ ቢጠይቁም፣ የጀርመን መንግሥት እስከዛሬ ጥፋቱን ለመቀበል ዝግጁ አልሆነም። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ለምሳሌ እአአ በ2012 ዓም የሶሻል ዴሞክራቶቹ እና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ለቡንድስታግ የጀርመን መንግሥት በሄሬሮ ላይ የተፈፀመውን ግድያ የዘር ማጥፋት ነው ብሎ እንዲቀበለው የተለያዩ ማመልከቻዎች ቀርበዋል። ይሁንና፣ ነሀሴ፣ 2012 ዓም እአአ የታህሳስ ዘጠኝ ፣ 1948 ዓም የዘር ማጥፋት ወንጀል መቀጣጫ ውልን በመጥቀስ በሰጠው መልስ ላይ በ1904 ዓም ለተፈፀመው ግድያ ቅጣት የመስጫው ጊዜ አልፏል በሚል ማመልከቻውን ውድቅ ነበር ያደረገው። ከዚህ ባለፈ ደግሞ በናሚቢያ አኳያ ባለበት ሞራላዊ ኃላፊነት ሰበብ ከዚችው ሀገር ጋር የተጠናከረ ትብብር በማድረግ ላይ መሆኑን አመልክቶዋል። በዚሁ ትብብር መሠረት፣ ጀርመናውያኑ ቅኝ ገዢዎች ለምርምር ወደ ሀገራቸው ከወሰዱት አጥንት አፅም መካከል ለምሳሌ፣ ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት ገደማ 18 የጭንቅላት አጽም ለናሚቢያ ልዑካን ያስረከቡበት ድርጊት ይጠቀሳል። ይሁንና፣ ይህ ትብብር ጥፋትን አውቆ ከመቀበል ጋ የሚያገናኛው ነገር እንደሌለ ነው እስራኤል ካኑትይኬ ያስታወቁት። ቱርክ በአርመናውያኑ ላይ የፈፀመችው ግድያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመሆኑ በቡንድስታግ ውስጥ የተካሄደው ክርክር ለሄሬሮዎች ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ሊያስገኝ እንደሚችል ተስፋ ማድረጋቸውን ለሰለባዎቹ የሚሟገቱት እስራኤል ካኑትይኬ ገልጸዋል።

Deutschland Namibia Geschichte Charité gibt Gebeine zurück
ምስል picture-alliance/dpa

« እኛ የምንፈልገው በይፋ ይቅርታ እንድንጠየቅ ነው። እና ፣ ወደዚሁ ግብ የሚያደርሰው እንቅስቃሴ አሁን የተጀመረ ይመስለኛል። »

ቱርክ በአርመናውያኑ ላይ የፈፀመችው ግድያ የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን በይፋ እውቅና የሰጠችበት የቡንድስታግ ክርክር ለጀርመን በሄሬሮ ብሔር ላይ የዘር ማጥፋት መፈፀሙን አምና ለመቀበል ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ ወቅት ነው ሲሉ ነበር ቪችሶሬክ ሶይል የተናገሩት።

« ሌሎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ የራስን ጥፋት አውቆ መቀበል እና ጥፋቱንም በስም ጠቅሶ መቀበል ያለብን ይመስለኛል። »

ቴሬዛ ክሪኒንገር

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ