የጃፓን እና የቻይና መሪዎች ጉብኝት በኢትዮጵያ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2006አቤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ሞዛንቢክን፣ ኣይቮሪኮስትን እና ወደ ማዕከላዊው ምስራቅ ተሻግረው ደግሞ ኦማንን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም ማፑቶ ላይ ለሞዛንቢክ የ 577 ሚሊየን የን ብድር ይፈቅዳሉ ተብለው የሚጠበቁት ኣቤ ለኢትዮጵያም ቢሆን ለእንፋሎት ኃይል ማመንጫ የሚውል የ 10 ቢሊየን የን ብድር እንደሚፈርሙ ለማወቅ ተችሏል። የኣሁኑ የጃፓን መሪዎች ጉብኝት ተንታኞች እንደሚሉት በጥሬ ኃብት ኣቅርቦት በበለጸገችው ኣፍሪካ በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣውን የቻይናን እንቅስቃሴ ለመጋፈጥ ነው ተብሏል።
የቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርም በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ መሰንበታቸው ሲታወቅ የሁለቱ ኣገሮች መሪዎች በተመሳሳይ ሳዓት ኢትዮጵያን መጎብኘት በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ፉክክር በተለይም ኣፍሪካን ኣስመልክቶ እየተካረረ መምጣቱን እንደሚያመለክት ብዙዎች ይገምታሉ።
የኢትዮጵያው ጠ/ሚ ቃ/ኣቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን ኣስቀድሞ የተያዘ ፕሮግራም በመሆኑ የሁለቱ ተቀናቃኝ ኣገሮች መሪዎች ጉብኝት መገጣጠሙ የኣጋጣሚ ጉዳይ ነው ይላሉ።
በኢትዮጵያ የቢዝነስ ህክምና ተቐም መስራች የሆኑት፣ የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ አቶ ኣህመድ ባቶሌ በበኩላቸው የቻይና ፈጣን ግስጋሴ ከጃፓንም ኣልፎ ምዕራባውያንንም ጭምር እያሳሰበ መቷል ይላሉ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ታሪካዊ ጠባሳ ወዲህም ቢሆን በአካባቢያቸው በደሴት ይገባኛል ጥያቄ የሚወዛገቡት ጃፓን እና ቻይና በኢኮኖሚ ፉክክርም ገላጋይ የታጣላቸው ባላንጣዎች እየሆኑ ከመጡ ውለው ኣድሯል። በተለይም ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምታደርገው ፈጣን ግስጋሴ ጃፓንን ከገበያ እየገፋች በመምጣቷ የኣሁኑ የቶኪዮ መፍጨርጨርም የትርፍ ብቻም ሳይሆን ተንታኞች እንደሚሉት የህልውና ጉዳይም ጭምር ነው ተብሏል።
ጃፈር ዓሊ
ኣርያም ተክሌ