1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የገንዘብ ማውጫ ማሽን መገጣጠሚያ በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ጥር 11 2008

«መላ ኢንዱስትሪስ» ይባላል ድርጅቱ። አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖችን ኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጠምን ጨምሮ፤ የኤሌክሮ ሜካኒካል ቁሶችን ማምረት ነው ዋነኛ ዓላማው። ድርጅቱ የተለያዩ ማሽኖችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገጣጠም እና ለማምረት በ50 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው ከሦስት ዓመት በፊት ነው።

https://p.dw.com/p/1HhD3
EU-Parlament Abstimmung über Banken Konten und Alternativkraftstoffe Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa

የገንዘብ ማውጫ ማሽን መገጣጠሚያ በኢትዮጵያ

አሁን አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ገጣጥሞ በመጨረስ ከባንክ የመክፈያ ስልት ጋር ስምም መሆናቸውን ለማጣራት በዝግጅት ላይ ነው። ሙከራው ስኬታማ ከሆነ፤ ድርጅቱ በአምስት ዓመት ውስጥ ከ10,000 እስከ 15,000 አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖችን በገበያ ላይ የማዋል ዕቅድ ነድፏል።

ለሆነ አንዳች አንገብጋቢ ነገር ገንዘብ አስፈለገዎት እንበል። ገንዘቡ በእጅዎ የለም። የደመወዝ ቀን ገና ነው። የፈለጉትን ገንዘብ በፍጥነት ሊሰጥዎት አለያም ሊያበድሮት የሚችል ሰውም በአጠገብዎት የለም። ባንክ ቤቶች ደግሞ ተዘግተዋል። ገንዘቡን አኹኑኑ ነው የሚፈልጉት። ድሮ ድሮ ገንዘቡን የሚሰጥዎ ሰው እስኪያገኙ፣ የደመወዝ ቀን እስኪደርስ ወይንም ባንክ ቤቱ እስኪከፈት መጠበቅ ግድ ይል ነበር።

አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖች አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ወዲህ ግን መጠበቅ ግዴታ አይደለም። በማንኛውም ጊዜ ወደ አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኑ (ATM) ሄደው ገንዘብዎን ማውጣት ይችላሉ። ማሽኑ የባንክ ቤት ሠራተኛ በሌለበት ገንዘብ ለማውጣት የሚያገለግል አውቶማቲክ መሣሪያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1800 እስከ 2000 ግድም አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖች እንዳሉ ይጠቀሳል። የ«መላ ኢንዱስትሪስ» መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ናዖል አዲሱ በፋብሪካቸው መመረት ስለጀመረው አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽን ያብራራሉ።

አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ መሣሪያ (ATM)የተፈለሰመው ከ50 ዓመት ግድም በፊት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1967 ዓመት ነው። በርካቶች መሣሪያውን የፈለሰመው አሜሪካዊው የንግድ ሰው ሉተር ሲምጂያን እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም ይኽ ውስብስብ መሣሪያ እንዲፈጠር የበርካታ ተመራማሪዎች የአዕምሮ ጭማቂ እንዳስፈለገ ተጽፎ ይገኛል። የመሣሪያው መፈልሰም ቀደም ሲል በባንክ ሠራተኛ እየተቆጠረ ይሰጥ የነበረውን ብቸኛ የገንዘብ አከፋፈል ስልት ቀይሮታል።
የ«መላ ኢንዱስትሪስ» መስራቾች ይኽን መሣሪያ በስፋት ማምረት ይሻሉ። የድርጅቱ መሥራች እና ባለቤት ወ/ሮ ሊሊያ ኃይሉ በኢንፎርሜሽን ሲስተም የትምኅርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው። ከባለቤታቸው ጋር የመሠረቱት ድርጅት ውስጥ የጠቅላላ ሥራ ቁጥጥር ኃላፊ ናቸው። የገንዘብ ማውጫ ማሽኖችን (ATM ) ኢትዮጵያ ውስጥ ገጣጥሞ ለማቅረብ ምን አነሳሳቸው?

ድርጅቱ ከአውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ መሣሪያ በተጨማሪ ሌሎች አራት መሣሪያዎችንም የማምረት ዕቅድ አለው። በተለያዩ የመገበያያ ሥፍራዎች አገልግሎት ላይ ሊውል የሚችል ከኮምፒውተር ጋር የተገናኘ የገንዘብ መክፈያ መሣሪያ (point of sale) ለማምረት ጥናቱ ተጠናቋል። ግለሰቦች በየቤታቸው ምግባቸውን የሚያሞቁበት መሣሪያ (Microwave)፣ የባንኮች የገንዘብ መቁጠሪያ መሣሪያ፤ እንዲሁም ለነዳጅ ማደያዎች የሚያገለግል ነዳጅ እየሳበ የሚያወጣ መሣሪያ ለማምረት በእንቅስቃሴ ላይ መኾናቸውን የድርጅቱ መስራች ባለትዳሮች ተናግረዋል።

Griechenland Geldautomat außer Betrieb
ምስል Getty Images/AFP/S. Mitrolidis

ላለፉት 10 ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ ግዙፍ ባንኮች እና የገንዘብ ተቋማት ውስጥ የኮምፒውተር ሶፍትዌሮችን በማደራጀት ሲሠሩ የቆዩት አቶ ናዖል አዲሱ በኮምፒውተር ሣይንስ የማስተርስ ዲግሪ አላቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም የሠሩት በኢንፎርሜሽን ሣይንስ ዘርፍ ነው። አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ መሣሪያ ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረብ ውስብስብ እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ መኾኑን ያብራራሉ።

ይኽን ውስብስብ አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ መሣሪያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ውስጥ እንደፈለሰመው የሚነገርለት አሜሪካዊው ሉተር ሲምጂያን በወቅቱ መሣሪያውን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ከፍተኛ ፈተና እንደገጠመው ይነገራል። ለመጀመሪያ ጊዜ ገጣጥሞ የሠራውን የገንዘብ ማውጫ መሣሪያ ለኒው ዮርክ ሲቲ ባንክ እንደምንም አሳምኖ ካቀረበ ወዲኽ ግን የመሣሪያው ተጠቃሚዎች እየተበራከቱ መኼዳቸው በታሪክ ሠፍሮ ይገኛል።
ወደ 10 የሚጠጉ ሠራተኞችን በመቅጠር ሥራ የጀመረው «መላ ኢንዱስትሪስ» ባለቤቶች የስነ ቴክኒክ ዕውቀቱን የገበዩት በዩናይትድ ስቴትስ ቆይታቸው ነው።

በ«መላ ኢንዱስትሪስ» ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የሶፍትዌር ኢንጂነሮች፣ ኮምፒውተር በመገጣጠም እና የኢንተርኔት መረቦችን በመዘርጋት የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው መኾናቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጠዋል። ከ25 ዓመት በላይ የሥራ ልምድ ያለው የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያ፤ እንዲሁም አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ መሣሪያዎችን በማደስ፣ በመገጣጠም እና በማምረት ከ30 ዓመት ያላነሰ ልምድ ያካበተ ባለሙያ በድርጅቱ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ድርጅቱ ወደፊት እስከ 25 የሚደርሱ ብቃት ያላቸው ሠራተኞችን እንደሚያቅፍ ባለቤቶቹ አስታውቀዋል።

በእርግጥም አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ መሣሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጠም የጀመሩት ባለትዳሮቹ ሙከራቸው ተሳክቶ ልክ እንደ አሜሪካዊው ሉተር ሲምጂያን ምርታቸውን በቅርቡ በስፋት ገበያ ላይ የማዋል ሕልም ሰንቀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Girokonto für Jedermann
ምስል picture-alliance/dpa/A. Warmuth

አዜብ ታደሰ