1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የገጣሚዉ ብዕርና መድብሉ

ዓርብ፣ መጋቢት 29 2009

«የአብዱ ኪያርን ድንቅ ዜማ ስናደምጥ የዮሃንስ ሞላን መርካቶ ሰፈሬን ጨምሮ ስናነብ መርካቶ ከቅመምና ከጌሾ ከሽንኩርትና ከቅቤ ከድስትና ከባሊ ወዘተ ባሻገር ሰዉ እንደወጣባት ወይም ደግሞ የጥበብ ሰዉ እንዳወጣች ያየነዉና የተረዳነዉ ሁላችንም አሁን በቅርብ ይመስለኛል።» ሁለገቧ የጥበብ ንግስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ

https://p.dw.com/p/2apFH
USA | Buchvorstellung von Port Yohannes Mola im Tayitu Cultural & Educational Center
ምስል Tayitu Cultural & Educational Center

የገጣሚዉ ብዕርና መድብሉ

ጂጂ ሽባባዉ የሚያደንቃት ሙዚቀኛ ናት። ሙዚቃዋን ሲያዳምጥ፤ ሥነ-ግጥም እንዲቋጥር ከሚገፋፉዉ መካከል አንደኛዋ የጥበብ ሰዉ ይላታል። እድገቱ መርካቶ፤ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን በአማኑኤል፤ ካቴድራልና በየካቲት 23 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ አጠናቆአል። አራተኛ ክፍል ሳለ በዓለም የኤድስ ቀን ለተማሪዎች የግጥም ዉድድር ጥሪ ቀርቦ ካሸነፈ በኋላ ዉስጡ እምቅ የግጥም ችሎታ እንዳለዉ በግልጽ እንዲታየዉ ይናገራል። የመጀመርያ ዲግሪዉን በአዋሳ ዩንቨርስቲ በስታትስቲክስ ዘርፍ ካገኘ በኃላ በዝያዉ በተማረበት ዩንቨርስቲ በረዳት መምህርነት ለአራት ዓመታት አገልግሎአል። በቀጣይ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪዉን በሥነ- ህዝብ ጥናት የሥነ- ተዋልዶ ጤና ትምህርት ዘርፍ ተከታትሎአል። በተለያዩ የአገር ዉስጥና የዉጭ መስራያ ቤቶችም አገልግሎአል።  

«የብርሃን ልክፍት» በሚል ርዕስ የመጀመርያ የግጥም መድብሉን ግንቦት 8 ቀን  2005 ለአንባቢ አቅርቦአል።  ዮሃንስ የብርሃን ሰበዞች በሚል ርዕስ ሁለተኛ  መጽሀፉን የመጀመርያዉ መጽሐፉ ለአንባቢ በበቃ በሦስተኛዉ ዓመት ግንቦት፤  2008 ዓ.ም ሁለተኛዉን የግጥም መድብል ለአንባብያን አቅርቦ ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ በዋሽንግተን ዲሲ የመጽሐፍ የመድብሉን በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል መድረክ ላይ አስተዋዉቆአል።  ግጥም ለኔ ይላል፤ ዮናስ ሞላ፤

Logo Tayitu Cultural & Educational Center
ምስል Tayitu Cultural & Educational Center

« የሥነ-ግጥም ትርጓሜን ከዚህ ቀደም የተለያዩ ገጣሚዎች አስቀምጠዉታል። እሱም ላይ አዲስ ነገር ላልጨምር እችላለሁ። በኔ አመለካከት ደግሞ ሥነ-ግጥም ለስሜት ቅርብ የሆነ ስታወሪበትም ቀሎሽ የምትናገሪበት ሰዎችም ሲያዳምጡት ልክ እንደዝያዉ ቀሎአቸዉ የሚመለከቱትና በፈለገዉ መልኩ እንዲፈቱት የምትተይዉ ነገር ነዉ። እንዲህ ነዉ ተብሎ የማትረጅዉ፤ በተበጀዉ የርዕስ ማዕቀፍ ዉስጥ የምትንቀሳቀሽበትና፤ ሰዉ በፈለገ መልኩ እንዲመለከተዉ የምናደርግበት ዉበትና ፍልስፍና አስተሳሰብ የታጨቀበት ጽሑፍ ነዉ ብዬ አስባለሁ»      

ግጥምን በቀላሉ እንደሚቋጥር የሚናገረዉ ዩሃንስ ሞላ፤ መጀመርያ ሊቋጥር ያሰበዉን ሃሳብ በመጀመርያ በዉስጡ አብላልቶ ከዝያ በወረቀት ያሰፍረዋል። ጉዳዩ እለታዊ ቅጽበታዊ ከሆነም እንዲሁ ሃሳቡን በግጥም ከሽኖ ግጥሙን ለመደርደር ጊዜ እንደማይወስድበት አጫዉቶናል።  

የመርካቶ ልጅ ዮሃንስ እንካ ሰላምትያ፤ ኮበላንኮ ዴበላንዲ ሁሉንም በግጥም ይጫወት ነበር።  ለመርካቶ ልጆችም አዲስ አይደለም እንደ ዮሃንስ። ሆያ ሆዬን ከደረሰ ዋናዉ ገጣሚ  ዮሃንስ ነበር።  ግጥምን መጻፍ የጀመርኩት ይላል ዮሃንስ በመቀጠል፤

«ግጥምን መፃፍ የጀመርኩት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ልጅ ሳለሁ ነዉ። የዓለም የኤድስ ቀንን አስመልክቶ የግጥም ዉድድር ነበር። እዝያ ላይ ተሳትፊ አንደኛ ወጥቻለሁ። የቋጠርኳት የግጥም እርዕስ «ኤድስ ምንድን ነዉ» የሚል ነበር።

የዛሬ 20 ዓመታት ግድም ዓለም አቀፉን የኤድስ ቀንን በማስመልከት የሥነ-ግጥም ዉድድር ማሸነፉን የሚናገረዉ ዮሃንስ ሞላ ከዝያም ታዋቂዎቹን ኢትዮጵያዉያን ገጣሚዎች ስራ በማየት ብዕሩን ከወረቀት ማገናኘት ጀመረ።

«ከዝያ በኋላ የመርካቶ ልጆችነንና ብሽሽቁ እንካሰላንትያ በምንንትያ የምንባባልበት ሁሉ በግጥም ነበር። በግጥም ነበር የምንነጋገረዉ ። ሆያሆዬ ሲመጣ ጭፈራ አለ፤ ግጥሞች ማዉጣት አለ። በዉስጤ የተለመደዉን መከተል አለመፈለግ ነበረብኝ። ከዝያ በኋላ ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ የማስታዉሰዉ የተለያዩ ሰዎችን ግጥሞች እንደምገለብጥ አስታዉስ ነበር። ገልብጬ አነባቸዉ ነበር። እናቴ የምታንጎራጎራቸዉን እየፃፍኩ አነብ ነበር። አድጌም የእጅጋየሁ ሽባባዉን የዘፈን ግጥሞች ጽፊ አነባቸዉ ነበር።» 

USA | Buchvorstellung von Port Yohannes Mola im Tayitu Cultural & Educational Center
ምስል Tayitu Cultural & Educational Center

ገጣሚ ዮሃንስን አገር ቤት የምታዉቀዉ የሥነ-ግጥም ቤተሰብ አባልዋ ሰናይት ሙሉጌታ ባለፈዉ አርብ በዋሽንግተን አካባቢ በነበረዉ የገጣሚ ዮሃንስ ዝግጅት ላይ ተገኝታለች።  

«ግጥም ሃሳባችንን በጣም በተመጠኑና ዉብ በሆኑ ቃላት የምንገልጽበት ነዉ። ሰዎች በግጥም የሚተላፍ መልክት ቶሎ የመረዳት አዝማምያ እንዳላቸዉ ይታያል። በአጠቃላይ ግጥም የትኛዉንም የሕይወታችንን ቀለም፤ ደስታም ይሁን ሃዘን ፤ ትዝብትም ይሁን ፤ ምጥን ባሉ ቃላት ለአንባብያን እንዲገባቸዉ አድርገን የምናቀርብበት አንዱ የሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ነዉ። »     

በዩናይትድ ስቴትስ ሲኖር ስምንት ወር ግድም የሆነዉና በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል መድረክ ላይ መጽሃፉን ለማስተዋወቅ በመቻሉ ደስተዉንና ምስጋናዉን የሚገልፀዉ ገጣሚ ዮሃንስ ሞላ በዝግጅቱ ላይ ብዙ ታዳሚ እንደነበር ገልጾአል። ገጣሚ ሰናይት ሙሉጌታ በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል የራስዋን የግጥም መድብል አስተዋዉቃለች።  

 ቃለ-ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንብዛለን። 

 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ