1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋሉፕ ጥናት እና የኢትዮጵያውያን አስተያየት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 24 2009

የአሜሪካው ጋሉፕ የጥናት ተቋም በያዝነው ወር መጀመሪያ ይፋ ባደረገው "ሕግ እና ሥርዓት በዓለም" የተሰኘ ጥናት ኢትዮጵያን አስተማማኝ ደኅንነት ካለባቸው አገራት ጎራ መድቧታል። በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ አልጄሪያን፤ርዋንዳን፤ሞሮኮን እና ግብፅን ተከትላ ከአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የጥናቱ ውጤት ግን ለኢትዮጵያውያን አልተዋጠላቸውም።

https://p.dw.com/p/2j6wS
Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

የጋሉፕ የጥናት ተቋም ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ የተሻለ ደኅንነት ካለባቸው የአፍሪቃ አገራት ጎራ ተመድባለች

በአፍሪቃ ለዜጎቻቸው ደኅንነት አስተማማኝ ከሆኑ አምስት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የአሜሪካው ጋሉፕ የጥናት ተቋም ይፋ ያደረገው ዓመታዊ ዘገባ ይጠቁማል። ጥናቱ ኢትዮጵያን ከዓለም ከ60ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጣት ከአፍሪቃ አምስተኛ ደረጃን ይዛለች።  "ሕግ እና ሥርዓት በዓለም" የተባለው ዘገባ ዜጎች በፖሊስ ላይ ያላቸውን መተማመን፤የስርቆት እና የጥቃት ድርጊቶች እንዲሁም በምሽት በሰላም መዘዋወር መቻል አለመቻልን የተመለከቱ ጥያቄዎች ላይ ተንተርሶ የተሰራ ነው። የደቡብ ወሎው አቶ አያሌው ግን ጋሉፕ ያነጋገራቸው ሰዎች እውነቱን አልነገሩትም የሚል እምነት አላቸው። በምኖርበት አካባቢ ዝርፊያ እና ስርቆት ይታያል የሚሉት አቶ አያሌው በተለምዶ ባጃጅ ተብለው በሚጠሩት ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ሰው እንደሚታገትም በዋትስአፕ በላኩልን መልዕክት ይናገራሉ።
ጋሉፕ ዘገባውን ሲሰራ 1,000 ሰዎች በአማርኛ ፤ በኦሮሚኛ ፤ በትግርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ቃለ-መጠይቅ ማድረጉን ገልጧል። እንደ አቶ አያሌው ሁሉ ስማቸውን ያልገለጡ ሌላ አስተያየት ሰጪ በጥናቱ የተካተቱ ሰዎችን ያጠይቃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት አዲስ አበባን ጨምሮ ከፍ ከፍ ባሉ ከተሞች በምሽት መንቀሳቀስ የሚታሰብ አይደለም።
በዋትስአፕ አስተያየታቸውን የላኩልን አንድ ግለሰብ "100% አገሩ ደህንነት አለው፡፡ለምሳሌ እኔ በኤርትራ ኣጠገብ በዓዲግራት ስኖር 100% ነፃነት ይሰማኛል፡፡" ብለዋል። ፌስቡክ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ገብረስላሴ ጌታሁን በበኩላቸው "አዲስ አበባ ሌሊት ሌሊት በየሰፈሩ ሰዉ አልባ ወይም ደካማ ያለበትን ቤት የሚሰርቅ ሌባ አለ።" ብለዋል። ሌላ በዋትስ አፕ አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰብ በተለይ በምሽት ለመንቀሳቀስ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር ላይ በምትገኘው ሞያሌ በሕክምና ሙያ የሚተዳደሩት ግለሰብ በከተማቸው አምሽቶ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ይናገራሉ።በጋሉፕ ጥናት መሰረት አልጄሪያ፤ርዋንዳ፤ሞሮኮ እና ግብፅ ለዜጎቻቸው ደኅንነት የተሻሉ ተብለው የተሻለ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል። 


እሸቴ በቀለ
 አርያም ተክሌ