1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግል ቤት ገንቢ ኩባንያዎች

ረቡዕ፣ መስከረም 11 2009

አዲስ አበባ ላይ ያተኮረው እና የግል ኩባንያዎች የተሰማሩበት የቤቶች ግንባታ ዘርፍ ባለፉት አመታት ከፍተኛ እድገት አሳይቷል ቢባልም እንደታሰበው ግን ውጤታማ አይመስልም። በአማላይ ማስታወቂያዎቻቸው ደንበኞች ለመሳብ የሚሞክሩት ኩባንያዎች በተደጋጋሚ ከቤት ገዢዎች ጋር በችሎት ሙግት ውስጥ ሲገቡ ታይተዋል።

https://p.dw.com/p/1K6Ce
Äthiopien Hausbau
ምስል DW/E. Bekele

የግል ቤት ገንቢ ኩባንያዎች

አዲስ አበባ ሲኤምሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገነቡ ቅንጡ ቤቶች ከ604,120 እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ያወጣሉ። በቦሌ በመገንባት ላይ የሚገኙት ቅንጡ ቪላዎች ከሁለት ሚሊዮን 400 ሺህ ብር በላይ የተተመኑ ሲሆን በዋንኛነት በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ ናቸው። በየካ ክፍለ ከተማ በ200 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር በመገንባት ላይ የሚገኘው የቻይናው ጸሀይ ሪል ስቴት ቤቶች እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር እንደ ተተመኑ በማሻሻጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ቅንጡ የመኖሪያ ቤቶች በመገንባት ሥራ ላይ የተሰማሩት የግል ኩባንያዎች በዋንኛነት አዲስ አበባ ላይ አተኩረዋል። አቶ ሲሳይ ዘነበ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ፖሊሲ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተባባሪ ሊቀ-መንበር ናቸው።
ባለፉት አስር አመታት በታየው ኤኮኖሚያዊ እድገት፤ከውጭ አገራት የሚላከው ገንዘብ እና በዋና ከተማዋ የሚታየው የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንቅስቃሴ መጨመር ለቅንጡ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት እድገት ዋንኛው ምክንያት እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በ980ዎቹ መገባደጃ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ብቅ ያሉት የግል ኩባንያዎች በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጠዋል። ከቀዳሚዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ጃክሮስ ሪል ስቴት ኩባንያ ከ250 ደንበኞቹ ወደ 27 ሚሊዮን ብር ቢሰበስብም ኪሳራ ገጥሞት ባለቤቱ ለእስር ተዳርገዋል። ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግስት አዲስ አበባ የተረከበው የባለአደራ አስተዳደር ሰፊ መሬት ለዚሁ የቤት ግንባታ ማዘጋጀቱ በርካታ ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ አግዟል። በ2002 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ 1,500 ኩባንያዎች በቤት ግንባታው ዘርፍ እንዲሰማሩ ፈቃድ ሰጥቶ ነበር። ኩባንያዎቹ የሚያንቀሳቅሱት የገንዘብ መጠን ቢጨምርም የአዲስ አባን የቤት እጥረት በመቅረፉ ረገድ ግን እምብዛም የተሳካላቸው አይመስልም።
Äthiopien Hausbau
ምስል DW/E. Bekele
አቶ ሲሳይ ዘነበ የቤት ግንባታው ዘርፍ ከፍ ያለ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ የሥራ ዘርፍ እንደሆነ ይናገራሉ። የአቅርቦት እጥረት እና የሕብረተሰቡ የመግዛት አቅም ውስንነትም ሌላው ፈተና ነው ባይ ናቸው።
በቤት ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከደንበኞቻቸው ገንዘብ ሰብስበው ግንባታውን ማጠናቀቅ ቃል በገቡበት ጊዜ ባለማጠናቀቃቸው ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ ይስተዋላል። አብዛኞቹ ክሶች ለቤት ገዢዎች ተፈርደዋል።አክሰስ ሪል ስቴት ከደንበኞቹ እና ፕሬዝዳንቱ ውዝግብ ውስጥ ከመውደቁ በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከገዢዎች ሰብስቦ ነበር። አቶ ሲሳይ ዘነበ የኢትዮጵያ የቤት ግንባታ ዘርፍ የራሱ መተዳደሪያ ሕግ ያስፈልገዋል ሲሉ ይናገራሉ።
በቤት ግንባታው ዘርፍ የተማሩ የግል ኩባንያዎች በአማላይ ማስታወቂያዎቻቸው ደንበኞቻቸውን ለመማረክ ይጥራሉ። ኩባንያዎቹ እና ማስታወቂያዎቻቸው ቃል የገቡትን ማሳካት ሲሳናቸው ከደንበኞቻቸው ጋር ከፍርድ ቤት ሙግት ይገጥማሉ። ይህ ባለፉት አስር አመታት በተደጋጋሚ የተስተዋለ ክስተት ነው። አቶ ሲሳይ ግን ዘርፉ በእውቀት ሊመራ እንደሚገባ ያምናሉ።
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ