1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክ ሕዝበ ዉሳኔ መልዕክት

ሰኞ፣ ሰኔ 29 2007

መግባባት ከተፈለገ አበዳሪዎችም ወደ አቴናዎች ግማሽ ርቀት መሔድ እንዳለባቸዉ ግልፅ ነዉ።የአበዳሪዎቹ የጋራ አቋም የዩሮ ሸርፍ አባል ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮች ለነገ-ከተቀጠረዉ ስብሰባቸዉ በኋላ ይለያል።ሁለቱ ወገኖች ሁነኛ አግባቢ መፍትሔ ካላገኙ የአቴናዉ አስተምሕሮት ነገ ሊዝቦን፤ ማድሪድ፤ አልፎ ተርፎ ሮማም አይደገምም ማለት ጅልነት ነዉ።

https://p.dw.com/p/1FtfD
ምስል Reuters/Marko Djurica

የግሪክ ሕዝበ ዉሳኔ መልዕክት

የግሪኩ ጠቅላይ ሚንስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ዴሞክራሲ የተወለደባት ሐገር ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ዉሳኔ አሉት።ተቃዋሚያቸዉ አንቶኒዮ ሳማራስ ባንፃሩ እራስን በራስ «ማጥፋት» ብለዉት ነበር።ግሪክ በርግጥ እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ የአበዳሪዎችዋን ቅድመ ግዴታ በሕዝበ ድምፅ «እንቢኝ» አለች።እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉ ግሪኮችን ወክለዉ ቅድመ ግዴታዉን «እንቢኝ» ብለዉ ሲሟገቱ፤ ሲያሟግቱ፤ ሕዝብን ለእንቢታ ሲያደራጁ የነበሩት የገዘብ ሚንስትርም፤ የአበዳሪዎችን ግዴታ አለመቀበል እራስን በራስ ከማጥፋት የቆጠሩት የተቃዋሚዎች መሪም ሥልጣናቸዉን እኩል ለቀቁ።ግሪክ ተቃራኒ ዕዉነት።

ሴትዮዋ አልወሰኑም።እንደ ብዙዉ የአቴናዊ ሁሉ ብዙ ነገር የሚያዉቁ አይመስሉም።አልገባቸዉም።አንዱን ግን በርግጠኝነት ያዉቋታል።«ከዚሁ ሁሉ ምሥቅልቅ መግባት አልነበረብንም።» እያሉ ይገልጹታልም።«የትኛዉን መምረጥ እንዳለብኝ አላዉቅም።አዎ ወይስ እንቢኝ።ምን ማለት እንዳለብኝ አላዉቅም።ነገሮች እንዲሕ እስኪመሰቃቀሉ ድረስ ይሕን ያሕል ርቀት መጓዝ አልነበረብንም።»

በ2008 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዩናይትድ ስቴትስን አከታትሎ የሌላዉን የምዕራብ ዓለም ምጣኔ ሐብት ያሽመደመደዉ ኪሳራ-ዓመታት የተጠራቀመዉ የአጭበርባሪዎች ቅጥፈት ዉጤት መሆኑ ብዙ አላጠያየቀም።

Spanien Demonstranten Referendum Griechenland
ምስል picture-alliance/dpa/Manu Fernandez

ብዙ-ያለማጠያየቁን ያክል ግን ትክክለኛዉ ዕዉነት ብዙ እንዲወጣ፤ ብዙ እንዲያነጋግር የአቴናዋ የዋሕ አይነቱ ብዙዉ ተጎጂ ሕዝብ እንዲያዉቀዉ አልተደረገም።አልተፈለገምም።ለነገሩ ጥቂት ደፋሮች እንዳሉት ከፖለቲከኞች-እስከ ባንክ ገዢዎች፤ ከኩባንያ ባለቤቶች እስከ መገናኛ ዘዴ መሪዎች፤ ከዩኒቨርስቲ ምሑራን፤ እስከ ተንታኞች ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የማጭበርበር-ቅሌቱ ተካፋይ-ደግሞ በተቃራኒዉ መፍትሔ ፈላጊም በሆኑበት ዓለም ትክክለኛዉ እዉነት ይፋ መሆን በሚገባዉ ጊዜና መጠን ይፋ ባይሆን ሊያስደንቅ አይገባም።

የማያስደንቀዉ አዉነት እንደ አብዛኞቹ የአዉሮጳ ሐገራት ሁሉ ግሪክ ላይ የታየዉም ያኔ ነበር።የትልቂቱ ቱጃር ሐገር ትልቅ ምጣኔ ሐብት ባፍጢሙ በተደፋ ማግሥት።2009።ጠቅላይ ሚንስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ግሪክ ዴሞክራሲ የተወለዳበት ሐገር ናት።

«እኛ ዴሞክራሲ የተወለደባት ሕገር ሕዝብ ነን።ሕዝበ ዉሳኔ ለማድረግ የሸዉብለ (የጀርመኑ የገንዘብ ሚንስር) ወይም የዲየሴልብሎሕን(የዩሮ ቡድን መሪ) ፈቃድ አንጠብቅም።»

ሁለቱም እዉነት ነዉ።ግሪክ እንደ ፍልስፍና፤ እንደ ሳይንስ፤ እንደ ቴክኒክ፤ እንደ ሥነ-ጥበብ ሁሉ ዴሞክራሲን ከስሙ-እስከ ፅንሰ ሐሳቡ ለአዉሮጳ በአዉሮጳ በኩል ለተቀረዉ ዓለምም ያበረከተች ሐገር ናት።እንደ ሁሉም ሥልጣኔ ሑሉ ከየትኛዉም የአዉሮጳ ሐገር ቀድማ ድራክማ በሚል ሸርፍ መገበያየት የጀመረች የገንዘብ ፋይዳን ለአዉሮጳ ያስተዋወቅች ሐገር ናት።

በ2009 መክሰሯ ሲነገር አብሮ የወጣዉ መረጃ ግን ያቺ የእዉነት፤የነብስ፤ የሕይወት፤ እዉቀት፤ሲዘራ-ሲታጨድባት ምዕተ-ዓመታት ያስቆጠረችዉ ሐገር ወደ ቀጣፊ፤ ዘራፊ፤ሙስኛ፤ አጭበርባሪዎች መፈንጫ ምንድርነት መለወጥዋ ነበር የተጋለጠዉ።የግሪክ መንግሥትና የገንዘብ ተቋማት ባለሥልጣናት ግሪክ አባል ለሆነችባቸዉ ማሕበራት፤ ተቋማትና ለሕቧም ጭምር ለረጅም ጊዜ የሚያቀርቡት ዘገባ ሐገሪቱ ያለባትን ኪሳራ በተለይ ከገቢዋ ወጪዋ መብዛቱን እየደበቁ ነበር።

በ2002 አገልግሎት መስጠት የጀመረዉ የዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን መሪዎችዋ ለሸርፉ ማስተባባሪያ ባንክ ያቀረቡት ሠነድም የተጭበረበረ ነበር።የዩሮ ቡድን፤ የአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክ፤ የዓለም ገንዘብ ድርጅት የሚባሉት የግሪክ አበዳሪዎቿም ሆኑ፤ ግሪክ አባል የሆነችባቸዉ የአዉሮጳ ሕብረት፤ የሰሜን አትላንቲካ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት፤የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወዘተ የሚባሉት ማሕበራት አጭበርባሪዎችን ለመቅጣት አልሞከሩም።

Yanis Varoufakis tritt zurück (Symbolbild)
ምስል picture alliance/dpa/Y. Kolesidis

የየተቋማቱ ወይም የየአባል መንግሥታቱ መሪዎች ወይም ባለሥልጣናት አጭበርባሪዎችን ከመቅጣት፤ መገሠፅ ይልቅ ለግሪክ በጣሙን ለባንኮችዋ ማበደርን ነዉ የመረጡት።አጭበርባሪ ጥፋተኞች ሳይቀጡ፤ እኒያዉ አጭበርባሪዎች፤ ወይም ምትኮቻቸዉ ለሚመሯቸዉ የገንዘብ ተቋማት ከ2010 ጀምሮ የተንቆረቆረዉ ገንዘብ ለግሪክ ሕዝብ ለልጅ-ልጁ-ልጁ የሚተርፍ ዕዳ-ነዉ የተከመረበት።

ትናንት ሥልጣን የለቀቁት የግሪክ የገንዘብ ሚንስትር ያኒስ ቫሮፋኪስ እንዳሉት የግሪክ ሕዝብ አምስት ዓመት የተከመረዉ ዕዳ በቃኝ ያለዉ እሳቸዉን ጨምሮ አዳዲስ መሪዎቹን የመረጠ ጊዜ ነዉ።ጥር።«የግሪክ ሕዝብ ጥር ሃያ-አምስት (በሰጠዉ ድምፅ) አምስት ዓመት የዘለቀዉ አስመሳይነት ይብቃ ብሏል።ግሪክ ከኪሳራ ትወጣለች እየተባለ ላለፉት አምስት አመታት በየጊዜዉ እንዳዲስ የተሰጣት ብድር ግሪኮችን አድክሟል።ልጆቻቸዉ እና የልጅ ልጆቻቸዉ በደማቸዉ፤ በላባቸዉን እና በእንባቸዉ ለመክፈል ይገደዳሉ።»

ግሪክ ዛሬ ከ342 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ዕዳ አለባት።አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ 193 ቢሊዮን ግድም ነዉ።ዕዳዋ ከዓመታዊ ገቢዋ ከ197 ከመቶ ይበልጣል።በያንዳዱ ሴኮንድ ከ720 ዶላር ወለድ መከፈል አለበት።እያንዳዱ ግሪካዊ ሰላሳ ሁለት ሺሕ ዩሮ ባለ ዕዳ ነዉ። ግን አስራ-አንድ ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝብ ሃያ-አምስት ከመቶዉ፤ ከወጣቱ ደግሞ ከሐምሳ ከመቶ የሚበልጠዉ ሥራ የለዉም።

ግሪኮች ይሕ ሁሉ ዕዳ የሚያናጥርባቸዉ መሪዎቻቸዉ አጭበርባሪ፤ አድርባይ፤ ጥቅም አሳዳጅ ሥለ ሆኑ ብቻ አይደልም።ተንታኞች እንደሚሉት አበዳሪዎቻቸዉም ብዙ የማይሻሉ በመሆናቸዉ ጭምር እንጂ።የአበዳሪዎች ይሁኑ የሌሎቹ ማሕበራት፤ መንግሥታትና ተቋማት መሪዎች ጥፋተኞችን ሳይቀጡ ላለፉት አምስት ዓመታት ከየሕዝባቸዉ የተሰበሰበ ግንዘብ እያፈሱ ግሪክ ላይ ዕዳ-የመቆለላቸዉን ሰበብ ምክንያትን አንዳዶች እነሱ ወይም ድርጅቶቻቸዉ ሥለሚጠቀሙ ይላሉ።የዋሕነት የሚሉም አሉ።ብዙዎች ግን እነሱ ማናቸዉ-እና ግሪኮችን የሚቀጡት-ባዮች ናቸዉ።

Griechenland Premierminister Alexis Tsipras
ምስል picture alliance/ZUMA Press/A. Vafeiadakis

ይሁንና የግሪክ ሕዝብ ትናንት በሰጠዉ ድምፅ አበዳሪዎች ያቀረቡትን የቁጠባ ግዴታ እንቢኝ ያለዉ የተወሳሰበዉን ሴራ ጠንቅቆ ሥላወቀ፤ የአዋቂዎችን ምክር፤ ትንታኔ ሥለተረዳ ወይም በትክክል ሥለተገነዘበ አይደለም።ጥቂቶች ሲከብሩ-ሲነስሩ የሚያዉ አብዛኛዉ ሕዝብ በዕዳ፤ ብችግር፤ ሥጋት እየተሸማቀቀ የሌሎችን ትንታኔ ማድመጥ መከታተሉ አላስፈለጊዉ አይደለምም።እና ወሰነ።-

«ለሲፕራስ፤ ማለት አይሆንም ብዬ ነዉ ድምፅ የሰጠሁት።ምክንያቴ ግልፅ ነዉ ሌሎች አዉሮጳዉያን ከግሪኮች የበለጠ መብት አላቸዉ።ዉጪ ሐገር ስጓዝ ይሕን አይቼዋለሁ።»አዩም አላዩ እሳቸዉ ያሉበት ጎራ ከ61 ከመቶ በበለጠ ድምፅ በቅድመ ግዴታ የተሞላዉን የአበዳሪዎችን ዕቅድ ዉድቅ አድርጎታል።የሕዝቡ ዉሳኔ ለጠቅላይ ሚንስትር ሲፕራስ መንግሥት ጠንካራ ድጋፍ፤ ወደፊት በሚደረገዉ ድርድርም ብርቱ ምርኩዝ ነዉ-የሚሆን።የግሪክ ሕዝብ የአበዳሪዎችን ቅድመ ግዴታ እንቢኝ አለ ማለት አንዳዶች እንደሚሉት ግሪክ ከዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚነት ወይም ከአዉሮጳ ሕብረት ትወጣለች ማለት አይደለም።የተቃዋሚዉ ፓርቲ መሪ አንቶኒዮ ሳማራስ ከሕዝበ ዉሳኔዉ በፊት እንደገለፁት እራስን ማጥፋትም አይደለምም።ግሪክ ከአዉሮጳ ሕብረት አይደለም አስራ-ዘጠኝ ሐገራትን ከሚያስተናብረዉ የዩሮ ሸርፍ አባልነት እንኳን ለመዉጣት በርካታ፤ ሕጋዊ፤ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መሟላት አላባቸዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ሲፕራስ ትናንት ያገኙትን ድል አጓጉል ተርጉመዉ አበዳሪዎችን ከተጋፉ የአበዳሪ ተበዳሪዎች ዉዝግብ ዳግም የማይጦዝበት፤ ዉዝግቡ ግሪክን ከየማሕበራቱ ገፍትሮ ለማስወጣት ሰበብ የማይሆንበት ምክንያት የለም።ግሪክ የሚኖሩት ጀርመናዊዉ ተንታኝ የንስ ባስቲያን እንደሙሉት ሲፕራስ ጠንቀቅ ማለት አለባቸዉ።

Griechenland Jubel nach Referendum
ምስል Reuters/Dimitris Michalakis

«ለጠቅላይ ሚንስትር ሲፕራስ በግላቸዉ ታላቅ ድል ነዉ።ለሚያደርጉት ድርድርም ግልፅ ድጋፍ ነዉ።ይሕን ድል ግን አጓጉል እንዳይተረጎሙት መጠንቀቅ አለባቸዉ።ይሕን ግልፅ ድል ከፓርቲያቸዉ ጥቅም ይልቅ ለድል ያበቃቸዉን የሕዝባቸዉንና የሐገራቸዉን ጥቅም ለማስከበር ሊያዉሉት ይገባል።»

የግራ ፖለቲካ አቀንቃኙ ጠቅላይ ሚንስትር ከድል በኋላ ያስተላለፉት መልዕክት የተለሳለሰና የአበዳሪዎችን ቅሬታና ቁጣ ለማለዘብ ያለመ ነዉ።ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት አበዳሪዎችን «አሸባሪ» ብለዉ የተቹ ወይም የሰደቡት የገንዘብ ሚንስትር ያኒስ ቫሮ ፋኪስ ሥልጣን ለቀዉ ገለል ብለዋል።

ከኮት ከራቫት ይልቅ-ሸሚዝ-ቲሸርት፤ ከመኪና ይልቅ ሞትር ብስክሊት የሚወዱት የምጣኔ ሐብት አዋቂ የትናንቱ ድል ባለቤት መሆናቸዉ ምንም አያጠያይቅም።ይሁንና የሚሰማቸዉን እንደተሰማቸዉ የሚያናገሩት ሰዉዬ ለዘመኑ ፖለቲካ በተለይ ከአበዳሪዎች ጋር ለሚደረግ ድርድር አይሆኑም።ቫሮፋኪስ ከሚንስትርነቱ ቦታ ዞር ያሉት ባለፉት አምስት ወራት በቀጥታ ንግግራቸዉ ያበሳጩዋቸዉን የአበዳሪዎች ሹማምንት ልብ ለማማለል ተደርጎም ነዉ የታየዉ።

ለግሪክ በአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክ፤ በዓለም ገንዘብ ድርጅትም፤ በዩሮ ተጠቃሚ ሐገራት ቡድንም ብሎ እስካሁን ከፍተኛዉን ብድር የሰጠችዉ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫልተር ሽታይ ማየር አሁንም ኳሷ ግሪክ ሜዳ ላይ ናት ይላሉ።

«ዉጤቱ ግልፅ ነዉ።ግልፅ እንቢኝ መሆኑን ያረጋግጣል።በመጀመሪያ ደረጃ ይሕን መሠሉን ዉጤት መቀበል አለብን።አብዛኛዉ የግሪክ ሕዝብ ድምፁን የሰጠበት ሕዝበ-ዉሳኔ ነዉ።ዋሳኙ ጉዳይ ከእንግዲሕ የሚቀጥለዉ እርምጃ ነዉ።እርምጃዉ ከየትም በፊት ግሪክ ዉስጥ ነዉ መወሰድ ያለበት።ሥለዚሕ ኳስዋ ያለችዉ አቴን ነዉ።»

ይበሉ እንጂ መግባባት ከተፈለገ አበዳሪዎችም ወደ አቴናዎች ግማሽ ርቀት መሔድ እንዳለባቸዉ ግልፅ ነዉ።የአበዳሪዎቹ ግልፅና የጋራ አቋም የዩሮ ሸርፍ አባል ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮች ለነገ-ከተቀጠረዉ ስብሰባቸዉ በኋላ ይለያል።ሁለቱ ወገኖች ሁነኛ አግባቢ መፍትሔ ካላገኙ የአቴናዉ አስተምሕሮት ነገ ሊዝቦን፤ ማድሪድ፤ አልፎ ተርፎ ሮማም አይደገምም ማለት ጅልነት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ