1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብር ተቃዉሞ በኦሮሚያ

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ሐምሌ 10 2009

የኢትዮጵያ መንግስት በሃገሪቱ ዉስጥ የሚገኙ ነጋዴዎች የቀን ገቢያቸዉ ተገምቶ ግብር እንዲከፍሉ የሚለዉን ዉሳኔ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

https://p.dw.com/p/2ggu7
Äthiopien Addis Abeba Kaffee Wirtschaft Roza Melese
ምስል DW/James Jeffrey

Oromia: Protest surge due to tax hike - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተዉ የቀን ገቢ ግምት የሚደረገዉ «የግብር ከፋዮችን የንግድ እንቅስቃሴ መሠረት ባደረገ እና በገቢ መርማሪዎች የህሊና ዳኝነት ላይ ተመስርቶ» እንደሆነ ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ በህብረተሰቡ ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን በማኅበራዊ መገናኛዎች እየተገለጸ ይገኛል። በኦሮሚያ ክልል በሻሸማኔ፣ ጅማ፣ ወሊሶ፤ በቡሌ ሆራና በአምቦ ከተማዎች የሚገኙ ነጋዴዎች ተቃዉሞ እያደረጉ እንደሚገኙ ዶይቼ ቬሌ ያነጋገራቸዉ የዓይን እማኞች አረጋግጠዋል።

ስማቸዉ እንዳይጠቅስ የጠየቁን የአምቦ ነዋሪ የከተማይቱን የዛሬ ውሎ እንዲህ ገልጸውልናል። ነዋርዉ: «የትራንስፖርትም ሆነ የሱቆች አገልግሎት ከዛሬ ጥዋት ጀምሮ የለም። መንገድ ላይ ሰዎችን ስታይ ፊታቸዉን ጨምድደው የሚሄዱበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ። ይህም ሊሆን የቻለበት የቀን ገቢ ትመናን ተከትሎ የሚከፍሉት የግብር መጠን በባለሃብቶችና በነጋዴዎች ላይ በመጨመሩ ነዉ። ይህም ቁጣ ቀስቅሷል።»

በአምቦ ባለፈዉ ሳምንት አንድ የኮካ ኮላ ማመላለሻ እና የደህንነት አባላት የሚጠቀሙበት መኪና ላይ ጉዳት መድረሱን የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ ቅዳሜ እለትም ከጸጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሁለት ሰዎች መቁሰላቸዉን መስማታቸዉ ይናገራሉ። ከዚያን ወዲህ ህብረተሰቡ በፍራቻ እንደንሚንቀሳቀስ  ነዋሪው ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል ፖሊሶች ከተማዋን ከላይ እስከታች ተቆጣጥረው እንደሚገኙም አስረድተዋል።

ሌላ የአምቦ ተወላጅ ነኝ ያሉን ግለሰብ በቡራዩ ከተማ በጫማ ንግድ ስራ ላይ መሰማራታቸዉን ይናገራሉ። የአሁኑ የግምት ተመን ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ «ስራዉን ላቆም ነዉ» ይላሉ። ነዋርዉ: «ጭማሪ ሲደረግ እኮ በቀን ገቢ በትክክል ታይቶ ቢገመት ችግር የለዉም። ግን ያደረጉት ምንድነዉ፣ ለምሳሌ በቀን 50 ብር የማያስገባ 500 ብር ያስገባል ብሎ ከገመቱ የቤት ኪራይ ከፍሎ፣ ሌሎችም ወጭዎች ከፍሎ ግብሩን መክፈል በጣም ከባድ ነዉ። ይህ ትክክል አይደለም።»

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በቡራዩ ሱቆች ክፍት ቢሆኑም፣ የህዝብ መመላለሻዎች አገልግሎት መስጠት ባያቋርጡም «ከተማዋ ቀዝቀዝ ብላለች» ይላሉ። አስኮ መናኸርያ አካባቢ እንደሚገኙ ተናግረው በዚያ አንድም መኪና እንደማይገኝ ተናግረዋል።

በወሊሶ ከተማም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ የሚያስረዱት ሌላ ግለሰብ «ጥዋት ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የሰዎች ጩኸት ነበረ» ይላሉ። 

የቀን ገቢ ግምት ከተደረገ በዋላ በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢ ያሉ ነጋዴዎች ቅሬታቸዉን እንዳሰሙ የሚናገሩት የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ይህንንም ተከትሎ ክልሉ የገቢዎች ጽህፈት ቤቶች ጉዳዮች እየታዮ፣ ችግሮችም እየተፈቱ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። በዛሬው ዕለት በክልሉ ባሉ ከተሞች የህዝብ ማመላለሻ እና የሱቅ አገልግሎቶች መቋረጥን በተመለከተ ደግሞ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

የፖለቲካዉም ሆነ የኢኮኖሚዉን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት የወሊሶዉ ነዋሪ በጉዳዩ ላይ «መንግስት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አልሰራም» ይላሉ።

በክልሉ መንግስት በኩል የግንዛቤ ማስጨበጫ በሚገባ እንደተሰጠ የሚናገሩት አቶ አዲሱ ነገር ግን «ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ» ጠቅሰዋል።

መንግስት ያደረገዉ የቀን ገቢ ግምት እንዴት እንደሚመለከቱት በዶይቼ ቬሌ የፌስቡክ ድህረ ገፅ ላይ ዉይይት አካሄድን ነበር። አዜብ ቶላ የተባሉ ተከታታያችን «ገቢ መርማሪዎች እነማን ናቸው? ስርዓቱ የተዋቀረው በሌብነት ላይ እና በዘረኝነት ላይ ነው» ሲሉ ግርማ በቀለ ደግሞ «ማንም በሰራው ስራ ከሚያገኘው ገቢ ግብር መክፈል አለበት። ፍትሐዊ ግብር ማስከፈል ደግሞ የመንግስት ሐላፊነት ነው» ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ