1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብፅ የዓለም ባንክ በገላጋይነት እንዲገባ ጠየቀች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 17 2010

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ሹማምንት ጋር ሲመክሩ ውለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ያነጋገሩት ሽኩሪ ከኢትዮጵያ አቻቸው ከዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋርም ውይይት አካሄደዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2py1H
Außenminister von Ägypten und Äthiopien
ምስል DW/G.T. Hailegiorgi

ግብፅ የዓለም ባንክ በገላጋይነት እንዲገባ ጠየቃለች

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ነበር ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የተገናኙት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን በጽህፈት ቤታቸው በመገኘት ያነጋገሯቸው ሽኩሪ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብደልፈታ አልሲሲ የተላከላቸውን መልዕክት አድርሰዋል፡፡

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ለመምከር ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ሽኩሪ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋርም ውይይት አካሄደዋል፡፡ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ሆነው ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅትም የአባይ ጉዳይ ተነስቷል፡፡

"ግብፅ ኤኮኖሚያዊ እድገት ለኢትዮጵያ ያለውን ፋይዳ እውቅና ትሰጣለች" ያሉት የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን ለማስተዳደር ወሳኝ መሆን ያለበት ሳይንስ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የዓለም ባንክን "ገለልተኛ እና ወሳኝ" ሲሉ የጠሩት ሽኩሪ ፖለቲካዊ ትርጓሜዎችን እና ማምታታቶችን አስወግዶ ድርድር ሊያመቻች ይችላል ሲሉ አክለዋል።

ዶ/ር ወርቅነህ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ግንባታ የከፋ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ተናግረዋል፡፡ ግብፅ አቅርባዋለች የተባለውን ንድፈ-ሐሳብ እንደሚመለከቱትም ገልጸዋል። የሁለቱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተለው ዘጋቢያችን ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ ያደረሰንን ዘገባ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ

ነጋሽ መሐመድ