1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅና የእስራኤል ስምምነት 30ኛ ዓመት

ሰኞ፣ መጋቢት 21 2001

ስምምነቱ በርግጥ ለእስከዚያ ዘመኑ አለም አዲስ፣ ለዚያ ምድር ታሪካዊ፥ ለሕዝቡ የሰላም ተስፋ ፈንጣቂ ነበር።

https://p.dw.com/p/HMvX
ሳዳትና ቤገንምስል dpa

የቴል አቪቭ መሪዎች የማረኩትን ግዛት የማጣቸዉ ሐዘን-ቁጭት፣አዉራ ጠላታቸዉን ከሌሎቹ በመነጠላቸዉ ድል-ድምቀት ከሰመ።የጦር ሜዳ ድላቸዉን በድርድርም የመድገማቸዉ ኩራት- በሰረ።የካይሮ ገዢዎች ዘር-ወገናቸዉን ጠላት የማድረጋቸዉ ኪሳራ፣ ሐያል-ጠላቶቻቸዉን በመወዳጀታቸዉ ትርፍ ተጣጣ። የተቀሙትን ግዛት የማስመለሳቸዉ-ደስታም በሰረ።ዋሽግተኖች የሞስኮ ጠላቶቻቸዉን የመብለጣቸዉ ኩራት፣ ቴሕራን ያጡትን ካይሮ በማግኘታቸዉ እፎይታ ተካሰ።ግብፅና እስራኤል የሰላም ዉል ተፈራረሙ።አብዛኛዉ አረብ የጤሰበት፣አለም በቅይጥ ስሜት የቆዘመበት ስምምነት ባለፈዉ ማክሰኞ-ሰላሳኛ አመቱን ደፈነ። የስምምነቱ እንዴትነት፤የዛሬ ዉጤቱ ምንነት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።

ድምፅ

እስራል ሕዝብ ፅናት፥ የመሪዎቹን ብልሐት፥ የአደራጅ ደጋፊዎቻቸዉን ቁርጠኝነት ይጠራጠር የነበረ-ከነበረ የ1948ቱን ጦርነት ዉጤት ማጤኑ በቂ ነዉ።እስራኤል በ1967ቱ ጦርነት የተቀዳጀችዉ ድል ግን ለፅኑ ሕዝቧ ኩራት፤ ለብልሕ መሪዎችዋ ክብር፣ ዩናትድ ስቴትስን ለመሳሰሉ ፍፅም ወዳጆችዋ ደስታ፣ ለአረብ-ሐፍረት፥ለሶቬየት ሕብረትና ለተባባሪዎችዋ ሐዘን፥ ለቀሪዉ አለም ድንቅ ሐቅ ነበር።

ድሉ የአረብ ሕዝብ መሪዎቹን እየቀየረ፣ አዳዲስ ተቋማትን እየፈጠረ፣ በፊት ከሶቬቶት ኋላ ከሌሎች እያበረ ለሌላ ዉጊያ ከመሰነቅ እልሕ ዶለዉ እንጂ በሐፍረት ተሸማቆ ለአሸናፊዎች እንዲገዛ አለማስገደዱ ነዉ ጭንቁ።የምዕራብ-ምሥራቅ ባላንጦች አረብ-አይሁድን የማዋጋታቸዉን ያክል ሁለቱን ወገኖች እንሸመግላለን ያላሉበት ዘመን የለም።የሁለቱ ወገኖች መሪዎችም አይሁድን-ለድል ኩራት-ቅጨቱ፤ አረብን ለሽንፈት ሐፍረት ግመቱ የመዘወራቸዉን ያክል ድርድርን እንቢኝ ያሉበት ጊዜ ከነበረ ጥቂት ነዉ።

የድርድሩ አማራጭ ከተጨባጭ ዉጤት የደረሰዉ፥ ከሞላጎደል-እስካሁን የፀናዉ ግን መጋቢት ሃያ-ስድስት 1979 የተፈረዉ ብቻ ነዉ።ስምምነቱ በርግጥ ለእስከዚያ ዘመኑ አለም አዲስ፣ ለዚያ ምድር ታሪካዊ፥ ለሕዝቡ የሰላም ተስፋ ፈንጣቂ ነበር።ተፈራራሚዎቹ ደግሞ አፈራራሚዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጂሚ ካርተር ካርተር ያኔ እንዳሉት ጀግኖች።

ድምፅ

«ሁለት መሪዎች፥-በሕዝቦች ታሪክ ለረጅም ጊዜ (የሰፈረዉን) የሚመሩት፥ ፕሬዝዳት አንዋር አል-ሳዳት እና ጠቅላይ ሚንስትር ሜናኸን ቤገን፥ሰዎችንና የጦር መሳሪያዎችን ወደ ዉጊያ አዉድ ካዘመቱ ታላላቅ ጄኔራሎች በላቀ ድፍረት፥ጀግንነት፥ብልሐትና አነቃቂነት ይሕንን ዘመቻ መርተዋል።»

ከትሩማን-እስከ አይዘናወር፥ ከኬኔዲ እስከ ጆንሰን፥ ከኒክሰን እስከ ፎርድ በጅምር የተወቱትን ካርተር ዳር አደረሱት።ወይም ለማድረስ ተገደዱ።1973-ጥቅምት ስደስት።አረብ በፆም እየጠወለገ ነዉ።ከበዛዉ በራስ የመተማመን ስሜት ጋር የአረብ ጦር በረመዳን ይተናኮለናል ብሎ ያልገመተዉ አይሁድ ዮም ኩፐር ለተሰኘዉ በአል ፌስታ በየሥፍራዉ ታድሟል።

የግብፅ ጦር ሲናይ በረሐ- የሠፈረዉን፣ የሶሪያ ተባባሪዉ ጎላን ኮረብታ የመሸገዉን የእስራኤል ጦር በቅፅበት ሲደቁሱት-የነበረዉ ሁሉ እንዳልነበረ ሆነ።ሃያ-ቀን ያዋጋዉ ጦርነት የተጠናቀዉ በርግጥ በእስራል የበላይነት ነበር።አረቦቹ መጀመሪያ ላይ የተቀዳጁት ድል ግን ለካይሮ-ቴል አቪቭ፣ ለዋሽግተን ሞስኮ ጠንካራ የማስጠንቀቂያ ደወል ነበር።

ለማስጠንቀቂያዉ ምላሽ ሔንሪ ኪንሲንጀር የፕሬዝዳት ጄራልድ ፎርድን-አንድሬ ጎሮሚኮ የሊዮንድ ብሬዥኔቭን፣ ዋና ፀሐፊ ኩርት ቫልድ ሐይም የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ትዕዛዝ ለማስፈፀም ደፋ ቀና ይሉ ገቡ።ግብፅና እስራኤልን ለማስታረቅ የዤኔቫዉ ጉባኤ የተሰኘዉ ስብስብ-ለአራት አመት መከረ።በዉይይት-ምክክሩ መሐል የሶቬት ሕብረት ጦር አፍቃኒስታንን ወረረ።የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች የዩናያይትድ ስቴትስን ታማኝ ወዳጅ ሻሕ ፓሕሌቭን አስወግደዉ ቴሕራንን ተቆጣጠሩ።

ሊባኖስ በርስ በርስ ጦርነት እየነደደች ነዉ።ግጥጥሞቹ ክስተቶች በሐገራቸዉ ወዳጅና ጥቅም ላይ የሚያደርሰዉን ጥፋት ጠንቅቀዉ የተረዱት ጂሚ ካርተር በጄኔቩ ዉይይት ሊተማማኑ፥አዲስ በያዙት ሥልጣን እስከሚደላደሉ መቆየት አልፈለጉም።የካርተር መልዕክተኞች ለካይሮና ለቴል አቪቭ መሪዎች በድብቅ ቃል እንደገቡ ሳዳት በጄኔቩ ድርድር ትዕግሥታቸዉ ማለቁን አስታወቁ።ዝነኛ-መልዕክታቸዉንም አሏት።

«ሰላም ለማምጣት የትም-እሔዳለሁ።» «እየሩሳሌምም ጭምር።» አልቀሩም።የመጀመሪያዉ የአረብ መሪ ለእስራኤል ምክር ቤት ንግግር-አደረጉ።ጠቅላይ ሚንስትር ሜናኸን ቤገንም የመጀመሪያዉን የአረብ መሪ ለማስተናገድ የመጀመሪያዉ የአይሁድ መሪ ሆኑ።1977።በሁለተኛ አመቱ ደግሞ ንጉስ ፋሩቅ ቀዳማዊ፣ ጄኔራል መሐመድ ነጉብ፤ ኮሎኔል ገማል አብድናስር ያልቻሉ ወይም ያልፈቀዱትን ሳዳት ቻሉ።ፈቀዱ።የሰላም ዉል ፈረሙ።ዋሽንግተን።

ድምፅ

«በወረሱትና በልዩ የታሪክ እዉቀታቸዉ የታወቁት የግብፅ ሕዝቦች የዚሕን መልዕክት ትርጉምና ዋጋ ገና ከጅምሩ-ጀምሮ ተገንዝበዉታል።»

ሳዳት አበሉ ማለት አይቻልም።የቃል-ፊርማቸዉን ገቢራዊነት ማየት ግን አልቻሉም።ተገደሉ።ጥቅምት 6-1981።ስምምነቱ ለግብፅ የሲናይ ግዛትን አስመልሶላታል።የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤልን ወዳጅነት አትርፎላታል።የሰወስትዮሽ ከተሰኘዉ የንግድ ልዉዉጥ ጠቀም ያለ ገቢ፥ ከአሜሪካ ወፈር ያለ ድጎማ አስገኝቶላታል።ለግብፅ ሕዝብ፥ ለጥቅል አካባቢዉ ሠላም የፈየደዉ ነገር መኖሩ ግን በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።ስምምነቱ በተረፈረመ በሰላሳኛ አመቱም ዛሬ ግብፃዊዉ አናፂ እስራኤልን አናምንም ይላል።

ድምፅ

«እስራኤልሎችን ማንም አያምንም።ዛሬ የሚናገሩትን በሚቀጥለዉ ቀን ይረሱታል።ይሕ ሠላም ከከፋ ሁኔታ ተከላክሎልናል።ያለዉ ግን በወረቀት ላይ ብቻ ነዉ።እስራኤል እንዳሔድ ታግደናል።በተለይም የጋዛዉን ጭፍጨፋ፥ በተገደሉትን ሕፃናት በጭራሽ ልንረሳዉ አንችልም።ከመቶ አመት በኋላም ቢሆን ሰዎች የተለየ ነገር አይናገሩም።በዚሕ ሁኔታ ሰላም አይቻልም።»

ሜናኸን ቤገንም ስምምነቱ ለሳቸዉ ክብር፥ ኩራት፥ለሐገር-ሕዝባቸዉም የሰላም ዋስትና መሆኑን አስረግጠዉ ነበር።

ድምፅ

«የመጣሁት ከእስራኤል ነዉ።ከፅዮናዉያን ምድር።ከየሩሳሌም።እንደ አይሁድ ሕዝብ ልጅ፥እንደ ሆሎኮስት ትዉልድ አባልነቴ እዚሕ በመቆሜ ክብርና ኩራት ይሰማኛል።»

በርግጥም ከዴቪድ ቤን ጎሪዮን እስከ ሞሼ ሻሬት፤ ከሌቪ አሽኮል እስከ ጎልዳ ሚር፤ ያልፈለጉ፣ ወይም ያቃታቸዉን ቤገን በማድረግ መፈለጋቸዉ ቢከበሩ፥ ቢኮሩ አያንሳቸዉም።ሥምምነቱ ለእስራኤል ትልቅ ጠላት ቀንሶላታል።ዘላቂ ሰላም ፀጥታዋን ማስከበሩ፥ የአረብን ወዳጅነት ማትረፉ ግን፥ በግብፅ የእስራኤሉ አምባሳደር ሻሎም ኮኸን በቀደም እንዳሉት አጠያያቂ ነዉ።

ድምፅ

«የሕዝብ ለሕዝብ ዉይይት የለም።ከግብፅ ጋር ሠላሳ አመት የዘለቀ የሠላም አለን።ሰላም ከሌለበት ሰላም ያለበት ዘመን ይበልጣል ማለት ነዉ።አሁንም ቢሆን ግን አዳዲስ (የግብፅ) ትዉልድ እየመጣ ነዉ።ለነሱ እስራኤል ማለት ፍልስጤሞችን የሚገድሉ ወታደሮች የምታዘምት፥ ከድንበር ማዶ ያለች ጠላት ናት።ይሕ ግን እዉነት አይደለም።ይሕ ሥዕል የሳንቲሙን ያንድ ወገን ገፅታ ብቻ የሚያሳይ ነዉ።ሁሉንም አያመለክትም።ይሕ ሊስተካካል ይገባዋል።»

ከካርተር በኋላ ሬጋን እስከ ቡሽ የተፈራረቁት የአሜሪካ መሪዎች አረብ-እስራኤልን ለማስታረቅ ሞክረዋል።የዛሬ ሰላሳ አመት ሳዳትን ያወገዙ፥ ምናልባት በመገደላቸዉ የተደሰቱ አረቦች ከእስራኤል ጋር ተደራድረዋል።ከቤገን በሕዋላ ከሻሚር እስከ ኦልሜርት የተፈራረቁት የእስራኤል መሪዎችም እንዲሁ።በተጨባጭ የሰላም ዉል የፈረሙት ግን አንድ ነበሩ-ይትሳቅ ራቢን።ፊርማቸዉ ሳይደርቅ ልክ እንደ ሳዳት በወገኖቻቸዉ ተገደሉ።

አሁንም ጥብቁ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት ከፍልስጤሞች ጋር ሰላም ለማዉረድ ዝግጅ ናቸዉ።

ድምፅ

«ፍልስጤሞች በኛ መንግሥት ዉስጥ ለሰላም፣ ለፀጥታና የፍልስጤሞችን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ የሚተባበር እንዳላቸዉ ሊገነዘቡት ይገባል።»

ኔታንያሁ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን ያደረጉትን የሚያዉቅ፣ ሊበርማንን የመሳሰሉ የመንግሥታቸዉ ተሻራኪዎችን አለማ-የሚረዳ፥የኔታንያሁን ቃል ለማማን በርግጥ ይተናነቀዋል። እስራኤል ከግብፅ ሌላ ከዮርዳኖስ ጋር የፈራረመችዉ የሰላም ዉል እንደፀና ነዉ።ባለፉት ሰላሳ አመታት ከሰብራና ሻቲላ-እስከ ቤይሩት፥ ከረመላሕ እስከ ጋዛ የሆነና የሚሆነዉን የሚያገናዝብ ግን አምባሳደር ኮሆን ያሉትን የሳንቲሙን ሌለኛ ገፅታ ማየት በርግጥ ይከብደዋል።

Dw,Wikipedia

ነጋሽ መሐመድ

►◄