1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ ክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የከፋው ጥቃት 

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2 2009

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታሕ አል-ሲሲ ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከፈጸማቸው ሁለት የቦምብ ጥቃቶች በኋላ በአገራቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል። የጸጥታ ተንታኞች ፅንፈኛው ታጣቂ በመካከለኛው ምሥራቅ የተሻለ መረጋጋት በሚታይባት ግብጽ የኃይማኖት ውጥረት ለመቀስቀስ ውጥን አለው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

https://p.dw.com/p/2b0gX
Ägypten nach Anschlag auf Kirche inTanta
ምስል Reuters/M. Abd el Ghany

IS tries to export Iraq-style sectarian tactics to Egypt - MP3-Stereo

ግብፃውያን ትናንት በአሌክሳንድሪያ ከተማ በአጥፍቶ ጠፊ የቦንብ ጥቃት የተገደሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ተሰናበቱ። በቅዱስ ሚና ገዳም የተፈጸመው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ እና ሐዘን ያረበበት ነበር።«ዛሬ ንጹኃን ወጣቶቻችንን ተሰናበትናቸው። ነፍሳቸው በሰላም እንዲያርፉ ነገርኳቸው። ነገር ግን ሐዘን ልቤን ሰብሮታል።» 

በአሌክሳንድሪያ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሶስት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ 17 ሰዎች ሲገደሉ 48 ቆስለዋል። ጥቃቱ ያነጣጠረው ግን በአሌክሳንድሪያ ብቻ አልነበረም። ከዋና ከተማዋ ካይሮ በ130 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የታንታ ከተማ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ  በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 27 ሰዎች ተገለዋል። የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆሳዕና ዕለትን በሚያከብሩበት እለተ-እሁድ በተፈጸመው ጥቃት 78 ሰዎች ቆስለዋል። በታንታ ከተማ የሚገኘው ቤተ-ክርስቲያን ቄስ ታውፊቅ ኮቤይሽ ሐዘን ከተጫናቸው መካከል አንዱ ናቸው።«እመኑኝ-በዚህ አስከፊ ወቅት አስቀያሚ ህመም እና ግራ መጋባት እየተሰማን ነው። ከእኛ ጋር በአንድ አገር የሚኖሩ፤ ፍቅር እና ጓደኝነትን የተጋራናቸው እና ጠንቅቀን የምናውቃቸው ሰዎች እንዲህ አይነት ድርጊት ይፈፅሙብናል ብለን አልጠበቅንም።»
የኃይማኖት አባቱ ታውፊቅ ኮቤይሽ መሰል ድርጊት አልጠበቅንም ይበሉ እንጂ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጥቃት እና በደል ሲፈጸምባቸው የመጀመሪያው አይደለም። መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ታሕሪር የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ተቋም እንደሚለው የዕሁድ ዕለቱን ጨምሮ ባለፉት ወራት 26 ጥቃቶች በግብፅ የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ተፈጽመው 88 ሰዎች ተገድለዋል። 
መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገው የቻንታም ሐውስ የፖሊሲ ጥናት ተቋም የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ዴቪድ ቡተር ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ቡድን ታጣቂዎች በግብፅ የኃይማኖት ውጥረት ለመፍጠር አብያተ-ክርስቲያናቱን ዒላማ አድርጓል ብለው ያምናሉ።
«ባለፈው ጥር ወር ካይሮ በሚገኘው ካቴድራል ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ነበር። በቅርቡም በሰሜናዊ የሲና በርሐ አልይሪሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በክርስትና እምነት ተከታዮች የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት ተፈፅሞ ለመሰደድ ተገደው ነበር። ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ሆነ ብሎ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ዒላማ አድርጓል። አብያተ-ክርስቲያናቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቀላል በመሆናቸው በታጣቂዎቹ ተመርጠዋል ማለት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በግብፅ ሕዝብ መካከል ኃይማኖታዊ ውጥረት ለመፍጠር እና የጸጥታ ኃይሎች የከፋ እርምጃ እንዲወስዱ በመተንኮስ  ተጨማሪ ችግር ለመፍጠር የታቀደ ጭምር ነው።»
በዕለተ- እሁድ ለተፈጸሙት ጥቃቶች ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃላፊነት ወስዷል። ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታሕ አል-ሲሲ የጦር ሰራዊቱን በመላ አገሪቱ ያሰማሩ ሲሆን የሶስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል። መንግሥታቸው ግን የክርስትና እምነት ተከታዮችን ደኅንነት ለመጠበቅ ቸልተኛ ነው እየተባለ ይተቻል።
«አናሳዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ለበርካታ ዘመናት በፅንፈኛ የእስልምና እምነት አራማጆች ጥቃት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል። የመንግሥት ባለስልጣናቱ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ሐዘኔታ የላቸውም። ለእነሱ በሚያደርጉት የጸጥታ ጥበቃም ትጉ አይደሉም። ሲሲ በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ሲመጡ የክርስትና እምነት ተከታዮቹ በሙርሲ ደጋፊዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ፅንፈኛ እስልምና የሚያራምዱት ወገኖች ለሚፈፅሙት ጥቃት የክርስትና እምነት ተከታዮቹ የሲሲ ጥብቅ ደጋፊዎች ሆነዋል፤የሙስሊም ወንድማማቾችን ይቃወማሉ የሚሉ ክሶችን ለማሳመኛነት ያቀርባሉ።» ይላሉ ዴቪድ ቡተር
በአሜሪካው የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በፅንፈኝነት ላይ ምርምር የሚያደርጉት ሙክታር አዋድ ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን ለግብፅ የከፋ ኃይማኖታዊ ውጥረት ደግሶላታል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። «የግብፅን ፋሲካ ኢላማ ማድረግ ቀዝቃዛ ግን ደግሞ የተጠና የቡድኑ ሥልት ነው።» የሚሉት አዋድ እንደ ኢራቅ ያለ ኃይማኖታዊ ውጥረት በግብፅ ለመቀስቀስ ቡድኑ መወጠኑን ይናገራሉ። የጸጥታ እና ደኅንነት ተንታኞችም የአልሲሲ መንግሥት በዚህ ወር መገባደጃ የሮማ ካቶሊካዊት ሊቃነ-ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ የሚጎበኙዋትን አገር ከኹከት መታደግ ስለመቻሉ ሥጋት አላቸው።

Ägypten Anschlag auf Christen in Tanta
ምስል Getty Images/AFP/Stringer
Ägypten Trauernde vor der koptischen Kirche Saint Mark in Alexandria
ምስል Getty Images/AFP/M. El-Shahed


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ