1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንዱን ንግድ የሚመለከተው ጉባዔ በዠኔቭ

ረቡዕ፣ ጥር 10 1998

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚካሄደው ንግድ መካከል ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያገለግለው ግንድ ወደ አሥር ሚልያርድ ዶላር ይሸፍናል።

https://p.dw.com/p/E0e5
ለኤክስፖርት የተዘጋጀ ግንድ
ለኤክስፖርት የተዘጋጀ ግንድምስል dpa - Bildarchiv

በመሆኑም፡ የግንዱ ንግድ በተለይ ለአንዳንድ አዳጊ ሀገሮች ኤኮኖሚ ከፍተኛ ትርጓሜ ይዞዋል። ይሁንና፡ ይህንኑ የግንድ ንግድ ለማንቀሳቀስ በሚወሰደው ርምጃ በያመቱ ወደ አሥራ አምስት ሚልዮን ሄክታር መሬት ደን የሚመነጠርበት አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎዋል። የተፈጥሮ አካባቢን ለመከባከብና ዘላቂ የሆነ የደን አጠቃቀምን ለማበረታታት፡ እንዲሁም፡ ከግንዱ ንግድ ተጠቃሚ የሆኑትን ሀገሮች የገቢ ምንጭን ለማረጋገጥ በማሰብ የተመ የንግድና የልማት መሥሪያ ቤት ስለግንዱ ንግድ የወደፊት አሠራር ለመምከር በዠኔቭ ስብሰባ ጀምሮዋል። እስከጥር ሀያ ሦስት ድረስ የሚቆየው የዤኔቩ ስብሰባ እአአ ከ 1999 ዓም ወዲህ የሚሠራበትንና በ 2006 ዓም መጨረሻ የሚያበቃውን ስምምነት የሚተካ አዲስ ውል ለማውጣት ይሞክራል።


በአሁኑ ጊዜ የሚሠራበት ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያገለግለው ግንድ ንግድ ተመልካች ውል የተመ የንግድና የልማት መሥሪያ ቤት ካወጣቸው ለምሳሌ ለብዙ አዳጊ ሀገሮች ኤኮኖሚ ትልቅ ትርጓሜ የያዙትን የወይራ ዘይት፡ ካካዎ ወይም ጥጥን የመሳሰሉ ጥሬ አላባ ተመልካች ውሎች መካከል አንዱ ነው። ስምምነቶቹ አምራች ሀገሮች በጥሬ አላባዎቻቸው ሁነኛ በሆነ ዘዴ በመጠቀም ለዘላቂው ኤኮኖሚያዊ ልማት እንዲያውሉት የሚረዱ ናቸው። ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያገለግለውን ግንድ ንግድን የሚመለከተው ስምምነት ግን ሌላም ተጨማሪ ዓላማ እንዳለው የዠኔቩን ስብሰባ በመምራት ላይ የሚገኙት የኡንክታድ የብራዚል አምባሳደር ካርሎስ ፓራንሆስ ሲያስረዱ፡
« ውሉ ልዩ ነው፤ በአንድ በኩል የጥሬ አላባ ተከላካይ ስምምነት ነው፤ በሌላ ወገን ግን ደኖችን ለዘለቄታው የመንከባከብና ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያገለግለውን ግንድ ምርት የማረጋገጥ ዓላማ ይዞ የተነሳ ነው። መደበኛ የጥሬ አላባ ስምምነት ቢሆንም፡ ዋነኛው ዓላማው ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያገለግለውን ግንድ ንግድ ማነቃቃት ነው። »
ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያገለግለው ግንድ ንግድ ስምምነት ለደን እንክብካቤ ሁነኛ ድርሻ የሚያበረክት ቢሆንም፡ የዝናብ ገቡን ደን ከምንጠራ ለማዳን የተደረሰ ስምምነት አለመሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ የዓለም አቀፉ የግንድ እንክብካቤ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ማኖዌል ሶብራል ፊሎ አስረድተዋል። ድርጅቱ የደኖችን ኅልውና ለዘለቄታው ለመጠበቅ የሚያስችሉ ቴክኒኮች እና ዕውቀቱን፡ እንዲሁም፡ ተጨማሪ መርሐ ግብሮችን ለሚመለከታቸው ሀገሮች ያቀርባል።
ግሪንፒስና ሮብንውድን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ድርጅቶች ስምምነቱ ዝናብ ገቡን ደን እና በዚሁ አሃባቢ የሚገኙትን ጥንታውያኑን ነዋሪዎች ኅልውና በመንከባከብ ፈንታ የግንዱን ንግድ ብቻ ለማነቃቃት የሞከረ ነው በሚል አጣጥለውታል። በዚሁ ሰበብ የተፈጠረው ልዩነት አሁን በዠኔቭ የሚካሄደውን ድርድር አዳጋች አድርጎታል። ግንዱን በንግድ ወደ ሀገራቸው የሚያስገቡት የአውሮጳ ኅብረትን የመሳሰሉ ወገኖች አዲስ ይውጣ በሚባለው ስምምነት ላይ የደኑ ጥበቃ ሀሳብ እንዲጠቃለል ሀሳብ አቅርበዋል፤ ከግንዱ ንግድ ባያመቱ ወደ አሥር ሚልያርድ ዶላር ገቢ የሚያገኙትና ይህንኑ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚሹት አምራቾቹ ሀገሮች ለደኑ ጥበቃ መርሐ ግብሮች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ግንዱን በኢምፖርት የሚያስገቡት ሀገሮች እንዲሸፍኑ ጠይቀዋል። ይህ ግን አዳጋች እንደሚሆን የዓለም አቀፉ የግንድ እንክብካቤ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፊሎ ሲያስረዱ፡ « ድርጅቲ ደንን ለመንከባከብ ካወጣቸው መርሐ ግብሮች መካከል እስካሁን አርባ ከመቶው በተግባር አልተተረጎመም። በተለይ አዳጊዎቻ ግንዱን ላኪ ሀገሮች ገዢዎቹ ሀገሮች መርሐ ግብሩን በገንዘብ እንዲደግፉ የሚለውን ጥያቄአቸውን በድርድሩ ላይ በዋነኝነት አቅርበዋል። » ነው ያሉት። የኡንክታድ አባል ሀገሮች ይውጣ በሚባለው አዲስ ስምምነት ላይ መስማማት አለመስማማታቸው የገና በግልፅ አልታወቀም፡ ግን፡ የዠኔቩ ድርድር ከከሸፈ የዝናብ ገቡን ደን እየተጠበቀ የግንዱን ንግድ ለማነቃቃት ያስችላል ተብሎ የተሰማው ተስፋ መና እንዳይቀር ፓራንሆስ ሠግተዋል።