1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግእዝ ፊደላትና ሥልጣኔ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12 2008

ትውልደ-ኢትዮጵያዊው አሜሪካዊ ሣይንቲስት የግእዝ ፊደላትን በስነ-ቴክኒኩ ዘርፍ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲጻፍ በማስቻላቸው በሚኖሩበት ዩናይትድ ስቴትስ የፈጠራ መብት ባለቤትነት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/1IYiG
iPhone 6 GeezEdit App
ምስል Dr. Abera Mola

የግእዝ ፊደላትና ሥልጣኔ

አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ የግእዝ ፊደላትን ለጽሑፍ አገልግሎት የሚጠቀሙ ቋንቋዎች የጽሑፍ አለያም የትየባ ስልት በስነ ቴክኒኩ ዘርፍ ወጥነት አይስተዋልበትም። በግእዝ ፊደላት በኮምፒውተር ለመጻፍ የሚያገለግሉ ሶፍትዌሮችን የሚያበለጽጉ ተመራማሪዎች የሚመሩበት የጋራ መሥፈርት ባለመኖሩም አንደኛው ጽሑፍ ከሌላኛው ጋር ሲጣረስ ይታያል። እንዲያም ሆኖ በኮምፒውተር እና ሌሎች ዘመናዊ የስነ-ቴክኒክ ውጤቶች ላይ ፊደላቱን ጊዜ እና ጉልበትን በመቆጠብ አቀላጥፎ ለመጻፍ የማስቻል የሶፍትዌር ማበልጸግ ሙከራዎች በተለያዩ ተመራማሪዎች ሲደረጉ ይስተዋላል።

ለድኅረ-ዶክትሬት ጥናት አሜሪካን ሀገር ሄደው መኖር ከጀመሩ 41 ዓመታትን አስቆጥረዋል። በእርግጥ ተምረው የተመረቁበት የሙያ ዘርፍ የእንስሳት ሕክምና ነው። ከሩብ ምዕተ-ዓመት በፊት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1982 ዓመት የግእዝ ፊደላትን ኮምፒውተር ውስጥ በማስገባት በሁለት ጥቁምታ እንዲጻፍ አድርገዋል፤ ዶክተር አበራ ሞላ።

በላቲን ፊደላት መተየቢያ የኮምፒውተር የጽሑፍ ገበታ ላይ ከ«ኤ» እስከ «ዜድ» 26 (A -Z)የተደረደሩ ፊደላት አሉ። ዶክተር አበራ ሞላ የኮምፒውተር የመጻፊያ ገበታ ላይ የሚገኙትን እነዚህን 26 የላቲን ፊደላት ጨምሮ ከ1 እስከ 0 የተደረደሩ ቁጥሮችን እንዲሁም ቀሪ ምልክቶችን፤ በጥቅሉ 47 ምልክቶችን ልክ እንደ እንግሊዝኛው በግእዙም በአንድ ጥቁምታ እንዲጻፉ ማድረግ ችለዋል።

ዶክተር አበራ በአማርኛ ቋንቋ በሳድስ የሚነገሩ ቃላት በርካታ መሆናቸው ሳድስ ፊደላትን ኮምፒተር ገበታ ላይ በአንድ ምት ወይንም ጥቁምታ መተየብ የአጻጻፍ ፍጥነትን ያሻሽላል የሚል እሳቤ አላቸው። ለአብነት ያኽልም ምግብ፣ ልብስ፣ ብርድ፣ ትምህርት፣ ድርቅ፣ የመሳሰሉት ቃላት ሙሉ ለሙሉ በሳድስ ድምጾች (ፊደላት) የሚጻፉ ናቸው። በተለምዶ ሳድስ ፊደላት በውስጣቸው የያዝዋቸውን አናባቢዎች በዶክተር ለማ የፊደል ገበታ መፃፊያ ስልት መተየብ አያስፈልግም።

ለአብነት ያኽል ምግብ የሚለውን የአማርኛ ቃል ብንመለከት ኮምፒውተር ላይ ለመተየብ «ኤም»፣ «ኢ»፤ «ጂ»፣ «ኢ»፣ «ቢ»፣ እና «ኢ» የተሰኙትን በጥቅሉ ስድስት የላቲን ፊደላት መጠቀም ያስፈልጋል። ሆኖም ስድስቱን የፊደል ቊልፎችን ከመጫን ይልቅ አናባቢው «ኢ»ን በማስቀረት «ኤም»፣ «ጂ» እና «ቢ» ፊደላትን ብቻ በመጫን ምግብ የሚለውን ቃል በሦስት ፊደላት በአማርኛ መጻፍ እንዲቻል ነው ያደረጉት። ከ47ቱ የተቀሩት ፊደላት በሁለት ምት አለያም ጥቁምታ የሚጻፉ ናቸው።

ዶክተር አበራ ሞላ ዲስ ፈጠራ ተብሎ የባለቤትነት መብት ዕውቅና በዩናይትድ ስቴትስ ካሰጣቸው ሌላኛው እመርታ መካከል የኮምፒውተር የጽሑፍ ገበታ ላይ በላቲን ፊደላቱ «ኤ» እና «ኢ» 14 ቀለማትን እንዲጻፍ ማስቻላቸው ነው። ቀደም ሲል የመተየቢያ ገበታው ላይ ሁለቱ ፊደላት በሁለት ጥቁምታ አለያም ምት ሲጻፉ ፊደላቱ ሊሰጡ የሚችሉት ስድስት ቀለማትን ብቻ ነበር።

የግእዝ ፊደላትን ከሁለት ዐሥርት ዓመት በፊት በኮምፒውተር ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉት ዶክተር አበራ ሞላ በተለያዩ ባለሙያዎች የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፉ ጠቅሰዋል። ሆኖም ግን አንዱ የሠራውን አለያም ያበለጸገውን ሶፍትዌር ሌላው መጠነኛ ለውጥ እያደረገ እንደፈለገ መቀያየሩ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል። የግእዝ ፊደል የኮምፒውተር አጠቃቀምን በተመለከተ የፈጠራ መብት ጥበቃ አለመኖሩ ወጥ አሠራር እንዳይሰፍን መሰናከል መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ያካተታቸው ፊደላት ከጥንት ፊደላት ሚመደቡ ናቸው። በዘመናችን ወደ አምስት መቶ የሚጠጉ የግእዝ ፊደላት በዩኒኮድ ታውቀው በኮምፒውተር እና መሰል የስነ-ቴክኒክ ውጤቶች ጥቅም ላይ ውለዋል። «ፊደላችን በዓለም ደረጃ ማንም ያውቀዋል፤ እውጪ ወጥቷል» ያሉት ዶክተር አበራ ሞላ «ለግእዝ የሚያስፈልገውን ነገር ማንም ሰው ሠርቶ አዲስ ነገር ሲፈጥር የፈጠራ ባለቤትነት መብት ማግኘት ይችላል» ሲሉም አክለዋል።

የግእዝ ፊደላት በስነ-ቴክኒኩ ዘርፍ ተገቢውን እድገት አላሳዩም ያሉት ዶክተር አበራ ሞላ የግእዝ ፊደላትን አዳብሮ መያዝ የኢትዮጵያውያን ፈንታ ነው ሲሉም አሳስበዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ