1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠብታ መስኖ በቡርኪና ፋሶ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2005

የመሬት ሃብትን በአግባቡ ተጠቅሞ በምግብ እህል ራስን መቻል ከፍተኛዉ የአፍሪቃ ሀገሮች ፈተና እንደሆነ እየታየ ነዉ። በርካታ ሀገሮች የተፈጥሮ ሃብቶችን በጥንቃቄ ተጠቅመዉ ህዝባቸዉን ለመመገብ ጥረት ይዘዋል።

https://p.dw.com/p/18M8V
ምስል DW/P. Hille

ከቆዳ ስፋቷ ጥቂቱን ብቻ ለእርሻ ማዋል የተሳካላት ቡርኪና ፋሶ ይህን ህልሟን ለማሳካት የጠብታ መስኖ እንቅስቃሴዋን አጠናክራለች። ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ቡርኪና ፋሶ የእርሻ ዘርፏ የተስፋፋ፤ ምርቷ የተትረፈረፈ የዳቦ ቅርጫት የምትባል ዓይነት አይደለችም። በሳህል ቀጣና መዳረሻ በምትገኘዉ በዚህች ሀገር ወደ16 ሚሊዮን ገደማ የሚሆን ህዝቧ አራት ሚሊዮኑ በቂ ምግብ አያገኙም። በዚህ ምክንያትም የዓለም ዓቀፍ ምግብ ርዳታ ጥገኛ ናት። ከ1990ዎቹ አንስቶ ግን ቡርኪና ፋሶ የመስኖ ስልቶችን በማስፋፋት የእርሻ ምርቷን በእጥፍ ለማሳደግ ስትጥር ትታያለች። ባለሙያዎች በቀጣይ ዓመታት አዎንታዊ ለዉጦች እንደሚታዩ ከወዲሁ ይናገሩላታል።

ማንዶ አዳያ የዉሃ መርጫ ሞተሩን እጀታ አራት ጊዜ አዞረዉ መርጫዉን ለማስነሳት። ማሽኑ በዝግታ ተነሳ እና መሬት ዉስጥ ከሚገኘዉ ማጠራቀሚያ ዉሃ መሬት ላይ ቀስ እያለ መርጨት ጀመረ።

Burkina Faso Landwirtschaft Ouagadougou Obstbauer
ምስል DW/P. Hille

በመሠረቱ አዳያ የዉሃ ማጠራቀሚያዉን መክፈቻ ሲያዞር ዉሃዉ መሬት ላይ ፈስሶ የሙዝና የማንጎ ዛፎቹን ሲያለብሳቸዉ አይታይም። ይልቁንም መሬቱ ላይ ከተያያዘዉ የዉሃ መሳቢያዉ አፍንጫ የዉሃ ጠብታዎች እየወጡ ቀስበቀስ መሬቱን ያረሰርሳሉ። አዳያ ላቡን ከፊቱ ጠረገ። በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ማዕከላዊ ግዛት የፍራፍሬ እርሻዉን አስፋፍቷል። በደረቁ የፀደይ ወቅት በአካባቢዉ የሚቀቱ መጠን 35 ዲግሪ ይደርሳል። ከዚህ አካባቢ የሳህል በረሃ በመኪና የሁለት ሰዓት ጉዞ ርቀት ላይ ነዉ የሚገኘዉ። እዚህ ታዲያ ዉሃ እንደልብ የማይገኝ የተፈጥሮ ሃብት ነዉ። ለዚህ ነዉ ማንዶ አዳያ የዉሃ ማጠራቀሚያ ስልት ለመትከል የተገደደዉ። በዝናብ ወራት ዉሃ ያጠራቅማል፤ ደረቁ ወቅት ሲመጣ ደግሞ በዘረጋዉ መስመር አማካኝነት ዉሃዉን በቀጥታ ወደአትክልቶቹ ያደርሳል። ከዚያዉም ላይ የፀሐዩ ግለት ያተነዋል። ሆኖም ከትናንሾሾቹ ቀዳዳዎች አፈሩ ዉስጥ ጠብ ጠብ እያለ የሚገባዉ በሰዓታት ዉስጥ ያረሰርሰዋል። ቀደም ሲል አዳያ በባልዲ በቀን ሁለቴ የፍራፍሬ ዛፎቹን ማጠጣት ነበረበት።

«በጠብታዉ ምስኖ በጣም ደስተኛ ነኝ። ነገሮች ሁሉ ቀለል ብለዉልኛል። አሁን በቀን አንዴ ብቻ ነዉ የዉሃዉን መርጫ ማስነሳት የሚኖርብኝ ከዚያም ቢያስፈልገኝ መተኛት ሁሉ እችላለሁ። በፊት ግን ሁሉንም ራሴ ማድረግና መቆጣጠር ነበረብኝ። አሁን ግን ሌሊቱን ሁሉ ዉሃዉ አትክልቶቹን እንዲያጠጣ ማድረግ እችላለሁ።»

Burkina Faso Landwirtschaft Ouagadougou Bauer auf dem Feld
ምስል DW/P. Hille

ማንዶ አዳያ ዛሬ በደረቅ ወራት ሁሉ በቂ የዉሃ ክምችት ስላለዉ ምርቱ ከድሮዉ አሁን ጨምሮለታል፤ የጠብታ መስኖ ስልት ትርጉም አለዉ ለእርሱ።

ማንዶ አዳያ በማጭድ የሙዝ ምርቱን እየቆረጠ ወደቅርጫት እርካታ ከፊቱ እየተነበበ ይከታል። በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል መቶ ክሎ ሜትር ርቀት ላይ ዋና ከተማ ኦጋዱጉ ላይ የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር ይገኛል። ሰይዲና ኦማር ትራዉሬ መስኖን የሚመለከቱ ጉዳዮች ተጠሪ ናቸዉ። አዳያ ከእሳቸዉ ዘርፍ ነዉ ለጠብታ መስኖ ስልቱ የገንዘብ ድጋፍ ያገኘዉ።

«መንግስት የጠብታ መስኖን የማስፋፋት መርሃግብር ዘርግቷል። ገበሬዎች በዚህ አማካኝነትም ለመስኖ የሚያስፈልጉ እቃዎችን ያገኛሉ፤ መንግስት ሁለት ሶስተኛዉን ይደጉማል።»

እሳቸዉ እንደሚሉት ለዚሁ ጉዳይ በያዝነዉ የጎርጎሮሳዊዉ ዓመት መንግስት ወደስድስት ሚሊዮን ዩሮ በጀት መድቧል። የትራዉሬ ምኞት አንድነዉ ቡርኪናፋሶ ሀገራቸዉ ከምግብ እህል ምርት በርከት ያለ ገንዘብ አትርፋ ማየት።

«ቢያንስ ወደጎረቤት ሀገሮች የምንልካቸዉ ምርቶች አሉን። ለምሳሌ ቲማቲምና ሽንኩር ወደጋና፤ ናይጀሪያ ወይም ወደአይቮሪኪስት እንልካለን። እናም ትኩረታችንን መስኖ ላይ አድርገን ቴክኒዎሎጂዉን ብናሻሽል፤ ያለንን እምቅ አቅም መጠቀም እንችላለን ብዬ አስባለሁ፤ እናም ምርቶቻችን በመላዉ ምዕራብ አፍሪቃ አልፎም ወደዓለም ዓቀፍ ገበያዎች መላክ እንችላለን።»

Burkina Faso Landwirtschaft Tröpfchenbewässerung Ouagadougou
ምስል DW/P. Hille

ቡርኪናፋሶ ዉስጥ ለእርሻ ከሚሆነዉ መሬት የታረሰዉና በመስኖ የተዳረሰዉ አምስት በመቶ የሚሆነዉ ብቻ ነዉ። ያለዉ አቅም ከፍተኛ መሆኑን ሽቴፋን ኖይ ይናገራሉ። የጀርመን የልማት ባንክ ተጠሪ የሚመሩት መስሪያ ቤት የቡርኪናፋሶን የመስኖ ፕሮጀክት በገንዘብ ይደግፋል። ግብርናዉ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ይቻል ይሆን? ሽቴፈን ኖይ፤

«ቡርኪናፋሶ የአነስተኛ ገበሬዎች እንቅስቃሴ ያለባት ሀገር ናት። ትላልቅ የእርሻ ተቋማት እንቅስቃሴ በሀገሪቱ አልተለመደም በልማዱም ተቀባይነት የለዉም። እዚያ ጋ ለመድረስ ረዥም ጉዞ ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ የህዝብ ብዛት ከመጨመሩ ጋ በተገናኘ ከፍተኛ ጫና በዚህ ረገድ ይታያል። የሀገሪቱ ህዝብ በየዓመቱ 3,2 በመቶ ይጨምራል። በተቃራኒዉ የቆዳ ስፋቱ ከዚህ በላይ ማምረት አይችልም።»

ባለሃብቱ ሎረንት ስትራቫቶ በዚህ ምክንያት በአነስተኛ እርሻ ዘርፍ ተሰማርተዋል። ኢጣሊያዊዉ ስትራቫቶ አራት በአራት ሜትር በሆነችዉ የእርሻ ቦታቸዉ መሃል ቆመዉ ይታያሉ። የበሰሉና መልካቸዉ የተለያየ ፍሬዎች በአረንጓዴ ቅጠሎቻቸዉ መካከል ብቅ ብቅ ብለዉ ይታያሉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ለትርፍ ያልቆመዉ ዓለም ዓቀፍ የልማት ፕሮጀክት በአነስተኛ ገበሬዎች ደረጃ የሙከራ ተግባሩን እያከናወነ ነዉ።

«ያ ማለት ከዚህ የምናገኘዉ ትርፍ የለም፤ በአንፃሩ ገበያዉን ለማሳደግ እንሞክራለን።»

ከምንም በላይ እዚህ የሚከናወነዉ በጠብታ የመስኖ ተግባር ምን ያህል ዉሃ መቆጠብ እንደሚቻል ማሳየት ነዉ። ስትራቫቶ ራሳቸዉ አርሶ አደር አይደሉም፤ በቡርኪናፋሶ የተጠቀሰዉ ድርጅት ዳይሬክተር ናቸዉ። የጠብታ መስኖ ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ያሳያሉ። በእጃቸዉ የያዙትን የዉሃዉን ማንቀሳቀሻ አራት ወይም አምስት ጊዜ ሲገፉ ዉሃዉ መፍሰስ ይጀምራል። ዉሃዉ ወደማሳዉ በተዘረጉት ቀጫጭን ቧምቧዎች አማካኝነት የበቀለዉን የቃሪያ ተክል ያጠጣል። መስመሩ ከዋናዉ ወደቀጫጭን ቧንቧዎች ዉሃዉን ያወርዳል፤ ወደአትክልቱ ሲደርስ ደግሞ እጅግ ይቀጥናል፤ ዉሃዉም ቀስ በቀስ እጅም ለትነት ሳይጋለጥ ይንጠባጠባል።

Burkina Faso Landwirtschaft Ouagadougou Markt Lebensmittel
ምስል DW/P. Hille

«ነገሩ ያን ያህል አብዮት የሚባል ዓይነት አይደለም። በመካከለኛዉ ምስራቅ የሚገኙ ሀገሮች እስራኤል፤ ዮርዳኖስ ወይም የደቡብ አዉሮጳ ሀገሮች ይህን ለሀገራቸዉ እርሻ መጠቀም ከጀመሩ ሰነባብተዋል። እዚህ ሳህል አካባቢ ግን የጠብታ መስኖ አብዮት ሆኗል፤ ለምን ወደዚህ ከመጣ ገና ቅርብ ጊዜዉ ስለሆነ ማለት ነዉ።»

ስትራቫቶየጠብታመስኖቡርኪናፋሶዉስጥበእርሻዉዘርፍአብዮትእንዲያስከትልይሻሉ።በዚህም ገበሬዎች ምርቶቻቸዉን በአንድ ሶስተኛ ከፍ እንዲያደርጉ ይፈልጋሉ፤ በተጨማሪም ገበሬዎች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ነዉ የሚፈልጉት። ምክንያቱም በግንቦት ወር በሀገሪቱ ገበሬዎች ምንም ዉሃ አይኖራቸዉም። ሆኖም በጠብታ መስኖዉ አማካኝነት እርሻዉን የሚያጠጣ ከሆነ ከማጠራቀሚያዉ ዉሃዉን ስለማያጣ በየጊዜዉ የማጠጣት እድል ይኖረዉና ተጨማሪ ቲማቲምና ሽንኩርት ማምረት ይችላል። በዚህ አጋጣሚም ወትሮ ከሚያገኘዉ አስር እጥፍ ዋጋዉን ከፍ አድርጎ የመጠየቅ እድሉ ይኖረዋል። በዚህም ለመስኖ የሚያገልግሉ መሳሪያዎችን የገዛበትን ዋጋ በአንድ ዓመት ዉስጥ ይመልሳል። በእጅ የሚሰራ ዉሃ ማንቀሳቀሻ፤ የፕላስቲክ ማጠራቀሚያ እና የመስኖ ዉሃ ማዉረጃ ቧንቧዎችን አራት ዩሮ ሂሳብ ያገኛሉ። በዚህ አማካኝነት ወርድና ስፋቱ አምስት ጫማ በአምስት የሆነ የእርሻ ቦታ ማጠጣት ይቻላል።

«ገበሬዎች ጠቀም ያለ ገንዘብ ማግኘት ከቻሉ ከዚህ የሚበልጡና ዉድ የሆኑ የመስኖ ስልቶችን መግዛት ይችላሉ። ይህ ማለት እንደፎልክስ ቫገን እና እንደሜርሰዲስ ማለት ነዉ። እኛ ፎልክስ ቫገን ነን፤ የጠብታ መስኖ መጠቀሚያ ስልቶችን ለህዝቡ እናቀርባለን።»

ማሽኑ ደግሞ ደጋግሞ የአኩሪ አተር ምርቱን እየተመላለሰ ያሻል፤ በእሱ መመላለስም ተጨማሪ የአኩሪ አተሮች ከልጣጫቸዉ ይላቀቃሉ። ስታራቫቶ የተጠራቀመዉን የአተር ስብስብ በእርካታ ያስተዉላሉ፤ በርከት ያለ ኪሎ ተጠራቅሟል። የዘንድሮዉ ምርት ከገመቱት በላይ ከፍ ብሏል፤ በመጨረሻ የታየ ስኬት መሆኑ ነዉ። የአኩሪ አተር ሰብሉ ከዚህ በፊት ከሚያገኘዉ በግማሽ ባነሰ ዉሃ ለምርት መብቃቱን ነዉ የተናገሩት። የጠብታ መስኖ ስልት ዉሃን ብቻ ሳይሆን ማዳበሪያንም በመቆጠብ ዉሃን ከትነት በማዳን በተለይ ሙቀት በሚበዛባቸዉ አካባቢዎች ምርትን እንደሚያሳድግ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ፒተር ሂለ

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ