1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የጤፍ የባለቤትነት መብትን የማስመለስ ዘመቻ

ረቡዕ፣ ግንቦት 1 2010

የኢትዮጵያውን እና ኤርትራውያን ብቻ ምግብ ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ጤፍ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አድማሱን አስፍቶ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ ይመረት ይዟል፡፡ ለጤና ተስማሚነቱ ከተመሰከረለት በኋላ ደግሞ የፈላጊዎቹ ቁጥር ጨምሯል፡፡ በዚህ መሀል ግን ኢትዮጵያ ተነጠቀችው የሚባለው የጤፍ የባለቤትነት መብት ብዙዎችን ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2xSZK
Bildergalerie Äthiopien Teff
ምስል DW/J. Jeffrey

የጤፍ የባለቤትነት መብትን የማስመለስ ዘመቻ

ፕሮፌሰር መላኩ ገቦየ ይባላሉ፡፡ በብሪታንያ ሌስተር ከተማ በሚገኘው ደሞንት ፎርት ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ የንግድ ህግ መምህር ናቸው፡፡ በሚያስተምሩበት የህግ ዘርፍ የግብርና ምርቶች እንዴት እንደሚበየኑ የሚተነትን ባለ 488 ገጽ መጽሐፍ ከዓመታት በፊት ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በየጊዜው በሚያሳትሟቸው ጥናታዊ ጽሁፎችም የግብርና ምርቶችን  ከዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት አሰራር አንጻር ፈትሸዋል፡፡ ከእርሻ ምርቶች ጋር በተያያዘ ለልባቸው ቅርብ የሆነ አንድ ጉዳይ ግን ሲከነክናቸው ቆይቷል፡፡ 
ጉዳዩ የጤፍ የባለቤትነት መብት በአንድ የኔዘርላንድስ ድርጅት ተወሰደ መባሉ ነው፡፡ እንደእርሳቸው የዓለም አቀፍ የንግድ ጉዳዮችን ስራዬ ብለው በሚከታተሉ ዘንድ ብቻ ሳይሆን ለመረጃ ቅርብ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንንም ጭምር ለዓመታት ያነጋገረው የዚህ ውዝግብ መንስኤ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት የተደረገ አንድ ውል ነው፡፡ ፕሮፌሰር መላኩ ውሉ እንዴት እንደተደረገ እና ያስከተለውን ጦስ ያብራራሉ፡፡ 

“[በጎርጎሮሳዊው] መጋቢት 2003 አካባቢ በኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ድርጅት እና በሆላንዱ ኤስ ኤንድ ሲ በሚባል ኩባንያ መካከል የመግባባት ሰነድ ተፈረመ፡፡ በዚያ መሰረት ለእነሱ ወደ 1400 ኪሎ የሚሆን፣ ወደ 14 ኩንታል ወይም ከዚያ በላይ የሚሆን 12 አይነት ዝርያ ያላቸው የጤፍ አይነቶች ምርምር እንዲደረገባቸው ወደ ሆላንድ ተላኩላቸው፡፡ ከዚያ በኋላ እነርሱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ይህን እያደረጉ በጎን ሐምሌ 2003 ላይ የሆላንድ መንግስት ቢሮ ሄደው የባለቤትነት መብት (ፓተንት) ይገባናል ብለው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት [ ያኔ] ያወቀ አይመስልም፤ ቢያውቅ ኖሮ ያነሳው ነበር ብለን ስለምንገምት ማለት ነው፡፡

Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

ከዚያ በኋላ በዓመቱ ሐምሌ 2004 ላይ ይሄ ኩባንያ ስሙን ቀይሮ HPF I፣ የሚባል ኩባንያ ሆኖ ለአውሮፓ ፓተንት ቢሮ የባለቤትነት መብት ይገባኛል ብሎ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይሄን እያደረጉ እያሉ በሚያዝያ 2005 ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ኮንትራንት ተፈራረሙ፡፡ በዚያ ውል (ኮንትራት) መሰረት የሆላንዱ ኩባንያ ጤፍን በአውሮፓ ገበያ እንዲያስተዋውቅላቸው፣ የተለያዩ ስራዎች እንዲሰራ ነው ስምምነቱ የተፈረመው፡፡ ከዚያ በኋላ ህዳር፣ ታህሳስ 2007 አካባቢ HPF I ለሚባለው ኩባንያ የባለቤትነት መብቱ ተሰጣቸው፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ እነርሱ ራሳቸው ከሰርን ብለው ከገበያ ወጡ፡፡ ያ ሲሆን ግን ያ የተቀበሉት የባለቤትነት መብት ሲከስሩ የት ሄደ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ያ የባለቤትነት መብት የትም አልሄደም፡፡ የመጀመሪያው የባለቤትነቱን መብት ያገኘው ኩባንያ ሰዎች ሌላ ኩባንያ ፈጥረው፣ የኩባንያው ዳይሬክተሮች ሆነው በአሁኑ ሰዓት እየተጠቀሙበት ነው ያሉት” ይላሉ ፕሮፌሰር መላኩ።  

በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ለአንድ ምርት አሊያም ያንን ምርት ለመስራት ለሚያስፈልገው ሂደት የባለቤትነት መብት እንዲሰጠው የሚጠይቅ አካል ሶስት ነገሮች ማሟላት እንዳለበት ፕሮፌሰር መላኩ ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያው መመዘኛ የነገሩ አዲስነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መብት በሚጠየቅበት ምርት ላይ የተጨመረ ፈጠራ ነው፡፡ ሶስተኛው መስፈርት ለጠቀሜታ ወይም ለተግባር የመዋሉን (industrial application) ጉዳይ የሚመዘነበት ነው፡፡ ፕሮፌሰር መላኩ የኔዘርላንድሱ ኩባንያ የባለቤትነት መብቱን ሲያገኝ ያቀረባቸውን ሰነዶች በእነዚህ ሶስት መመዘኛዎች ፈትሸውታል፡፡ ከሶስቱ ውስጥ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው ኩባንያው ፈጥሬያቸዋለሁ የሚላቸው ነገሮች ላይ ነው ይላሉ፡፡   

“የመጀመሪያው አዲስ መሆን አለበት ነው፡፡ ግሎተን የሚባል ችግር ላለባቸው ሰዎች፣ ሰውነታቸው መፍጨት ለማይችሉ ሰዎች፣ ከግሎቱን ነጻ የሆነ ምግብ ማቅረብ እችላለሁ ብሎ ነው የቀረበው፡፡ አዲስነቱ በዓለም ደረጃ ከታየ ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይዛው የኖረችው ምግብ ነው፡፡ ነገር ግን እዚያ ቦታ ላይ ሲያቀርበው ቢያንስ ቢያንስ ይህንን ልናልፈው እንችላለን፡፡ አዲስነቱን እንደተውኩት ሁሉ የኢንዱስትሪ ጠቀሜታ የሚለውን ነገር የተውኩበት ምክንያት ለምንድነው? መጀመሪያውኑ እንደመመዘኛ የሆነበት ምክንያት ራሱ ዝም ብሎ ንደፈ ሀሳባዊ የሆኑ፣ ፍልስፍናዊ የሆኑ ፈጠራዎች ለፓተንት እንደማይገቡ ለማድረግ፣ የፓተንት ዓላማ ገበያ ላይ የሚቀርብ ዕቃን ሊያመርቱ የሚችሉ ፈጠራዎችን በደንብ ለማስገዛት (regulate) የተዘጋጀ ስለሆነ ነው፡፡  

ሁለተኛው ደረጃ፣ የተፈጠረውን ነገር ምንድነው? ብለን ስንነሳ የሚያስቀው ነገር ጤፍ እንዴት እንደሚፈጭ፣ እንዴት እንደሚቦካ፣ እንዴት እንደሚጋገር እኔ የፈጠርኩት ዘዴ አለ ብሎ የሚነገረን እናቶቻችን ለዘመናት፣ በሺህ ዓመታት ለሚቆጠሩ ጊዜያት ሲያደርጉ የነበረውን ነገር ነው አውሮፓ ሄዶ አዲስ ነገር ፈጥሬያለሁ ብሎ የመጣው፡፡ ያ ማለት ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ከጤፍ የተመረተ ማንኛውንም ምርት ወይም ደግሞ ጤፉን ወደ አውሮፓ ልከን አውሮፓ ውስጥ ከጤፍ የተመረተ ብስኩት፣ ፓስታ፣ ገንፎ፣ ማንኛውም ነገር ሊሆን ይችላል በአውሮፓ ገበያ እንዳይሸጥ መከልከል እንደሚያስችል ስናይ ነው ከመሳቅ ወደ ማልቀስ የምንሄደው ማለት ነው” ሲሉ ቁጭት በሚነበብበት ድምጽ ይገልጻሉ።ፕሮፌሰር መላኩ ኩባንያው ይህንን መብቱን ተጠቅሞ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ብቻ አይደለም የሚያሳስባቸው፡፡ ከተለያዩ ቦታ ያገኟቸው መረጃዎችን ጠቅሰው “ኩባንያው የባለቤትነት መብቱን ተጠቅሞ በዚያ መስክ ሊሰማሩ የሚፈልጉ ባለሙያዎችን እያስፈራራ ነው” ሲሉ ይከሳሉ፡፡ “በኩባንያ ደረጃ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ” ሲሉም ያክላሉ፡፡ 

Bildergalerie Äthiopien Teff
ምስል DW/J. Jeffrey

የጤፍ የባለቤትነት መብት ጣጣ ቶሎ እልባት ካልተገኘለት ከዚህም የባሱ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የተሰማቸው ፕሮፌሰር መላኩ እንደእርሳቸው ጉዳዩ ካሳሰባቸው ሰዎች ጋር ተቀናጅተው ግንዛቤ የመፍጠር ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ የዘመቻቸው መነሻ መንግስታዊው የኢትዮጵያ የአእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ባለፈው የካቲት ወር ከጤፍ የባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ ያወጣው መረጃ ነው፡፡ ጽህፈት ቤቱ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የጤፍ የባለቤትነት መብት ለኢትዮጵያ ለማስመለስ የተቋቋመው ኮሚቴ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ 

በጽህፈት ቤቱ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ብሩክ ወርቅነህ በኔዘርላንዱ ኩባንያ የተያዘውን የጤፍ የባለቤትነት መብት ለማስመለስ እየተደረገ ስላለው ጥረት እና ስለውሳኔዎቹ ማብራሪያ አላቸው፡፡ “የጤፍ ባለቤትነት መብትን ለማስመለስ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በመጀመሪያ ደረጃ እንደሀገር አቀፍ ጉዳይ ተይዞ የሚመለከታቸው አምስት መስሪያ ቤቶች የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት፣ የብዝሃ ህይወት [ኢንስቲትዩት]፣ የግብርና ምርምር [ኢንስቲትዩት] እነዚህ ሆነው ኮሚቴ ተቋቁሞ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ ንግግሮች ወይም ደግሞ ከኩባንያው ውይይት በሚካሄድበጽ ጊዜ ኩባንያው አካሄዱን እየቀያየረ እስከዛሬ ድረስ ሊቆይ ችሏል፡፡ ከሰርኩኝ በሚል እና ሌሎች ምክንያቶች በማቅረብ ኩባንያው ተገቢውን ምላሽ አይሰጥም ነበር፡፡ ስለዚህ ያንን የሚመለከታቸው አካላት፣ እነዚህ መስሪያ ቤቶች በአንድ ላይ በመሆን ሶስት የእንቅስቃሴ መንገዶች አወጡ፡፡ 

ከሶስቱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ዲፕሎማሲ አንዱ ነው፡፡ ውጭ ጉዳይ ነው አንዱ መስሪያ ቤት፡፡ በውጭ ጉዳይ አማካኝነት ዲፕሎማሲው እየተደረገ ዲፕሎማሲው ካልሰራ አንደኛው አማራጭ የህዝብ ንቅናቄ እንዲኖር ወይም ደግሞ ተገቢ ያልሆነ የባለቤትነት መብት ስለወሰደ ያንን የሚቃወም (defaming) በህብረተሰቡ፣ በህዝብ ዘንድ እንዲሰራጭበት ነው፡፡ ሌላኛው በህግ አግባብ ለመክሰስ እና የባለቤትነት መብቱን ለማስመለስ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው” ይላሉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው።

DW Euromaxx - 50k - Zignie4
ምስል Lena Ganssmann

የአእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የጀመረው ጥረት ያነቃቃቸው እነ ፕሮፌሰር መላኩ በራሳቸው የጀመሩት የማህበራዊ መገናኛዎች ዘመቻ ከጽህፈት ቤቱ ሁለተኛ አማራጭ ጋር የተጣጣመ ሆኗል፡፡ በዘመቻው የኔዘርላንድሱ ኩባንያ በአውሮፓ የባለቤትነት መብት ያገኘበት የዕውቅና ሰነድ ተያይዞ ውግዘት ሲደርስበት ሰንብቷል፡፡ የኔዘርላንድሱ ኩባንያ በአሜሪካም የባለቤትነት መብት አግኝቷል ተብሎ በዘመቻው መጀመሪያ ተጠቅሶ የነበረ ቢሆንም ስህተት መሆኑ ተደርሶበት በስተኋላ መታረሙን ፕሮፌሰር መላኩ ያስረዳሉ።  ኩባንያው በአሜሪካ “አመለከተ እንጂ እውቅና አልተሰጠውም” ይላሉ መምህሩ።

የዩኒቨርስቲ መምህሩ የጤፍን  የባለቤትነት መብት ማስመለስ ከተሰኘው ዘመቻቸው ምን ለማሳካት እንዳሰቡ እንዲህ ያብራራሉ፡፡ “የአእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የሚባለው «ጤፋችንን ማስመለስ አለብን» ብለው እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ እና ያንን ሲጀምሩ በተቃራኒው በኩል በጣም ጠንካራ የሆነ መከላከል እንደሚደረግ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀረብ ያለ መረጃ ያለን ሰዎች እርግጠኞች ነን፡፡ ስለዚህ በህዝብ ዘንድ ይህ ነገር ምን ማለት እንደሆነ እንዲታወቅ ነው የማህበራዊ መገናኛዎች ዘመቻው የተጀመረው፡፡

እስካሁን ድረስ ኢመደበኛ በሆነ ሁኔታ ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ አለን ብዙ ሰዎች ግን ያንን መልክ አስይዞ አስፈላጊ ሲሆን ወደፊት የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ ፍርድ ቤት ሄደው ለመሟገት እንዲችሉ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ አንደኛ በገንዘብ፣ ሁለተኛ በተለይም ደግሞ አውሮፓውያን ራሳቸውን ይሄ የባለቤትነት መብት አለኝ የሚለው ኩባንያ እንዴት አስቂኝ እና አሳዛኝ ስራ እየሰራ፣ የኢትዮጵያን ገበሬዎች ዕድል እየነጠቀ እንዳለ እንዲያውቁ የማህበራዊ መገናኛዎች ዘመቻ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡ እንጂ ስራው በአጠቃላይ ሄዶ ሄዶ በህግ መሰረት ነው መታየት ያለበት፡፡ ለፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርበታል፡፡ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ጫና ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚያ ነው እንግዲህ ይህን እንቅስቃሴ የጀመርነው” ሲሉ ያገባኛል የሚል ሁሉ ሊሳተፍበት ይገባል ስለሚሉት ዘመቻቸው አብራርተዋል።    

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ