1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥምቀት ክብረ-በአል በዓለሙ የቅርስ መዝገብ

ሐሙስ፣ ጥር 11 2009

«ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ» በተከታታይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ዘንድሮ በተለይ በጎንደር ከተማ በከፍተኛ ድምቀት እየተከበረ መሆኑ ተነግሮአል። ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ ከሃይማኖታዊ በአልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳውም የጎላ ነዉ

https://p.dw.com/p/2W4im
Äthiopien Epiphanie in Addis Abeba
ምስል Thomas Haile

ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳውም የጎላ ስለሆነ በሀገር ዉስጥ ካለዉ ማኅበረሰብ በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና መንፈሳዊ ተጓዦች የሚታደሙበት በዓል በመሆኑ እንዲሁም የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ቀልብ እየሳበ በመምጣቱ የአከባበር ሥነ-ስርዓቱን በተመ የትምሕርት፤የሳይንስና የባሕል ድርጅት በ«UNESCO» ጥበቃ ስር በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመረዉ ጥረት መጠናቀቁ ተሰምቶአል። በዚህ ዝግጅታችን የጥምቀት በዓል አከባበርን ይዘን በተለይ በዘንድሮዉ በጎንደር ስለሚካሄደዉ ልዩ አከበር፤ በክብረ በዓሉ ላይ ስለሚነገሩት ሥነ-ቃሎች እንዲሁም በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በዓሉን እንዴት እንደሚከብሩት እንቃኛለን።

ምሁራን ጥምቀት ለሚለው ቃል መነከር ፣ መታጠብ የሚሉ ትርጓሜዎችን ይሰጡታል፡፡የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ይባላል፡፡ የከተራ እለት/ ጥር 10 ማለት ነው/ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ ፤ የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዞአቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ።  መምህር ካሳይ ገብረዝጊአብሔር የጥምቀት በዓል አመጣጥን እንዲህ ይገልጹታል።

Äthiopien Epiphanie in Addis Abeba
ምስል Thomas Haile

በኢትዮጵያ  ከዋዜማዉ ከከተራ ጀምሮ በመከበር ላይ የሚገኘዉ የጥምቀት በዓል ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በክብር ወጥተው በሕዝቡ እልልታ፣ ሽብሽባ እና በካህናቱ ውብ ያሬዳዊ ዜማ ወደ ወንዝ አልያም ወደተዘጋጀ የዉኃ ቦታ በመውረድ ሕዝቡን በሰፊው የሚያሳተፍበት የጥምቀት ሥነ-ስርዓት ተከናዉኗል። በዓሉ በተለይ በጎንደር ከተማ በድምቀት በመከበር ላይ መሆኑን በስልክ የነገሩን የጎንደር ከተማ ባህል ቱሪዝምና ወጣቶችና ስፖርት መምርያ ኃላፊ አቶ አስቻለዉ ወርቁ ተናግረዋል። የብዙ ታቦታት ሀገር የሆነችው ይህች ከተማ በዓይነቱ ለየት ያለ ባሕረ ጥምቀትም አላት። ይህ የአፄ ፋሲል መዋኛ የነበረው ታሪካዊ ባሕረ ጥምቀት ለጥምቀት በዓሉ ትልቅ ሞገስን የሚሰጥ ነው። ለዚሁ ለጥምቀት በዓል የከተማዉን ዝግጅት በተመለከተ አቶ አስቻለዉ ወርቁ በጥምቀተ ባህሩ አካባቢ መቀመጫ መድረክ ተዘጋጅቶአል፤ እስከ 50 ሚትር የሚረጭ የዉኃ ማስተላለፍያም ተዘጋጅቶአል፤ የከተማዋ እንግዶች የሚያርፉበት በቂ ሆቴልም አለ። የደህንነት ስጋት የለም ሌቦችን ለመጠበቅ አካባቢዉ ላይ የቆመየፖሊስ ጣብያም ተዘጋጅቶአል ሲሉ ተናግረዋል።      

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት የማይዳሰሱ ቅርሶች ዓመታዊ ጉባዔን ለመጀመርያ ጊዜ ያስተናገደችዉ ኢትዮጵያ የጥምቀት ክብረ በዓልን በዓለሙ የቅርስ መዝገብ ለማካተት ዝግጅቱ መጠናቀቁን የነገሩን በኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የሕዝብና ዓለም አቀፍ ዳይሪክተር አቶ ጌትነት ይግዛዉ ንጉሴ ከተቋሙ የመጡ ባለሞያዎች እቦታዉ ላይ ይገኛሉ። በርግጥ ክብረ በዓሉን በዓለሙ ቅርስ ለማስመዝገብ የሚደረገዉ ሥራ በአንድ ጊዜ የሚጠቃለል እንዳልሆነ ተናግረዋል።  

ውብና ድንቅ የሆነዉን ይህን ክብረ በዓል ለማክበርና ለማየት  አገር ተሻግረው የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ከዓመት ወደ ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ ሃገርን በማስተዋወቁ ረገድ ጠቀሚታዉ የጎላ መሆኑ እሙን ነዉ። በጥምቀት በዓል ላይ በሚታዩት ባህላዊ ጭፈራዎች ላይ ከሚሰሙት ሥነ-ቃሎች መካከል ጥቂቶቹን መምህር ካሳይ ገብረዝጊአብሔር እንዲህ ሰፋ ያለ ማብራርያ ሰተዉናል።

Äthiopien Epiphanie in Addis Abeba
ምስል Thomas Haile

በሃይማኖታዊና በባህላዊ በዓልነቱ የሚታወቀዉ የጥምቀት በዓል በድምቀት የሚከበረዉ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድም ነዉ። በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ኃላፊና የኮሎኙ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን  ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ፤ በጀርመን በሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ የበዓሉን አከባበር የሥራ ቀን በመሆኑ በሁለኛ ደረጃ በአዉሮጳ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ወቅት በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ በአንድድ ቀን ባይዉልም ቅሉ በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል። ።

መልካም በዓል እየተመኘን በሠላም በጤና የዓመት ሠዉ እንዲለን በመመኘት ቃለ ምልሱን የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ድምፁን ከድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ