1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨረቃ ቤቶች በወለጋ

ሰኞ፣ ጥር 5 2006

በኦሮሚያ ክልል፣ ምስቃቅ ወለጋ ዞን፣ ኣንዳንድ የኣገርጉቴ ከተማ ኗሪዎች የከተማው ኣስተዳደር ህገወጥ ግንባታ በሚል ሰበብ የመኖሪያ ቤቶቻችንን እያፈረሰብን ነው ይላሉ። በዚሁ አጋጣሚ በጸጥታ ኃይሎች ተደብድበው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ኣሉ ሲሉም ያማርራሉ።

https://p.dw.com/p/1Aprb

ለከተማው ልማት ሲባል ህገወጥ ግንባታዎችን የማፍረሱ ሂደት እንደሚቀጥል የገለጸው የከተማይቱ መስተዳድር ግን በዚህ ኣጋጣሚ የተደበደበ ሰው የለም ሲል ኣስተባብሏል።

በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ጅዳ አያና ወረዳ፣ አንገርጉቴ ከተማ ውስጥ መሆኑ ነው፤ ኣንዳንድ የከተማይቱ ኗሪዎች የጨረቃ ቤት በሚል ሰበብ የከተማይቱ ኣስተዳደር መኖሪያ ቤቶቻችንን እያፈረሰብን ነው ይላሉ። የጨረቃ ቤት ማለት ቅሬታ ኣቅራቢዎቹ እንደሚሉት፣ ጭለማን ተገን በማድረግ በምሽት የተገነቡ ህገወጥ ቤቶች ማለት ነው። ኣንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማይቱ ኗሪ ዛሬ ለዶቸቬሌ እንደነገሩት ከሆነ እንዲያውም በኦሮሚያ ፈጥኖ ደራሽ የጸጥታ ኃይሎች በሚታገዘው የከተማይቱ ኣፍራሽ ግብረ ኃይል ወከባና ድብደባም ጭምር ደርሶባቿል። እርምጃው ኣድልዎ የታከለበት ነውም ተብሏል።

China Erdbeben Qinghai April 2010 Flash-Galerie
ምስል AP

የከተማይቱ ከንቲባ፣ አቶ ሙሉጌታ በቀለ እንደሚሉት በእርግጥ በኣንገርጉቴ ከተማ ብቻም ሳይሆን በዞኑም ሆነ በኦሮሚያ ክልል በኣጠቃላይ ህገወጥ ግንባታዎችን የማስወገድ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል። ይህ ማለት ግን አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ በክልላዊው መንግስት ህግ እና ወጥ በሆነ መመሪያ መሰረት እንጂ በዘፈቀደ ወይንም በኣድልዎ የሚከናወን ኣይደለም።

«እንደ ኣገር ህገወጥ ግንባታዎችን ኣስመልክቶ መንግስት ያወጣው ኣዋጅ እና መመሪያ ኣለ። በዚሁ መሰረት በህገወጥ መንገድ የከተማይቱን ማስተር ፕላን ኣፋልሰው የጨረቃ ቤቶችን በሚገነቡት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል። ኣግባብነትም ኣለው ብዬ ኣምናለሁ። ይህ ሲሆን ግን በኣንድ ወይንም በሌላ ምክኒያት በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን የማንም ይሁን ብቻ ህገወጥ ግንባታ በኣጠቃላይ መፍረስ ይኖርበታል። እናም ያው በመመሪያው መሰረት በተወሰኑ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል»

ህጋዊ ግምባታም እንኩዋን ቢሆን ከከተማ መስተዳድር የግንባታ ፈቃድ ሳይኖር፣ ከአጥር ጀምሮ ማንኛውም ግንባታ ሊከሄድ ኣይችልም ያሉት አቶ ሙሉጌታ እነዚህ ግለሰቦች ግን የግንባታ ፈቃድ ቀርቶ የቦታ ፈቀድ ሳይጠይቁ በመንግስት ቦታ ላይ የመሬት ሽሚያ ኣካህዷል ሲሉም ከሷል።

«የከተማውን መስተዳድር ፈቃድ ሳይጠይቁ ፕላኑን በማፋለስ የመሬት ሽሚያ ያደረጉ ግለሰቦች ህገወጥ ግንባታቸውን ከመንግስት መሬት ላይ እንዲያስነሱ በተደጋጋሚ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰቶ በአዋጁ መሰረት ቤታቸው ላይ ቢለጠፍላቸውም ፈቃደኛ ሊሆኑ ባለመቻላቸው በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተወስዷል።» በዚሁ ኣጋጣሚ አካላዊ ጉዳት የደረሰበት ሰውም እንዳለ ተጠቅሷል።

እስከኣሁን ከ 5 – 10 የሚሆኑ ቤቶች እና መሬት ለመያዝ ሲባል የተሰሩ አጥሮች መፍረሳቸውን የገለጹት የአንገርጉቴ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ በቀለ የተደበደበ ግለሰብ ስለመኖሩ ግን ፈጽሞ ሐሰት ነው ሲሉ ኣስተባብሏል።

«ይህ በእርግጥ ሐሰት ነው። ምንድነው የሆነው፣ ግብረ ኃይሉ ላማፍረስ ከስፍራው በሚደርስበት ሳዓት ኣንዲት ሴት፣ የልብ በሽታ ስላለባት ይመስለኛል፤ ቤቴ ለምን ይፈርሳል? የት እገባለሁ? እያለቀሰች ድንገት ተዝለፍልፋ ወደቀች። እኛም ሁኔታውን ኣይተን ለጊዜው ኣልፈናታል። ወደፊት ምን ልናደርግ እንደምንችል እየመከርን ነው። እንዲያው በስፍራው ያሉ የህገወጥ ግንባታ ባለቤቶች ሆን ብለው ያራግቡታል እንጂ ሴትየዋን የነካት ሰው ግን የለም።»

በከተማይቱ ኣስተዳደር መግለጫ መሰረት የኣንገርጉቴ ከተማ ዘጠኝ ያህል የተለያዩ ብሔረሰቦች በጋራ የሚኖሩባት ስትሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በከተማይቱ ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በጨረቃ ቤቶች ላይ የተጀመረው የማፍረስ ዘመቻም ቢሆን የዚሁ የልማት እንቅስቃሴ አካል ነው ተብሏል።

ጃፈር ዓሊ

ነጋሽ መሓመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ