1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀረ-ካፒታሊዝም ሰልፍ

ሰኞ፣ ጥቅምት 6 2004

ባለፈዉ ቅዳሜ ለንደን የተደረገዉን ሕዝባዊ ሠልፍ የተከታተሉት ብሪታኒያዊዉ ደራሲ አፍሺን ራታንዚ እንዳሉት የብሪታንያ መገናኛ ዘዴዎች የሠልፈኛዉን ጥያቄ፥ አለማና ብዛቱን፥ መዘገብ የሚገባቸዉን ያክል አልዘገቡም።እና ለንደን ዉስጥ ቢያንስ የዚያን ቀን ለደራሲዉ የፕረስ ነፃነት አልነበረም።

https://p.dw.com/p/RrPL
የፀረ-ካፒታሊዝም ሰልፍ-ኒዉ ዮርክምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com

የሐምሳ ሐገራት-ዘጠኝ መቶ ሐምሳ-አንድ ከተሞች በፀረ-ካፒታሊዝም በጣሙን በገንዘብ ሥርዓቱ ተቃዉሞ ሠልፍ ተጥለቀለቁ።ፓሪስ የተሰበሰቡት የቡድን ሃያ-አባል ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮች ሥጋት ግን የአዉሮጳ የገንዘብ ተቋማት ክስረት ነበር።የተቃዉሞ ሠልፉ ጥንካሬ ሰበብ ምክንያት፥ የካፒታልስቱ ሥርዓት እንዴትነት የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሶሶሎጂ ሙሕር ፕሮፌሰር ጂ ዊልያም ዶምሆፍ-ባለዉ ሐምሌ ባሳተሙት መጣጥፋቸዉ አሜሪካን የሚገዛዉ ማነዉ? ብለዉ ይጠይቃሉ።ዶምሆፍ እራሳቸዉ መልስ አላቸዉ ዓለምን የምትመራዉ ብቸኛ ልዓለ ሐያል ሐገርን የሚገዙት ጥቂት ባለጠጎች ናቸዉ-የሚል አይነት። የዶምሆፍ መጣጥፍ ከመታተሙ ከጥቂት አመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳተመዉ ጥራዝ እንደሚያመለክተዉ ከግማሽ የሚበለጠዉን የዓለምን ሐብት የሚቆጣጠሩት ሰዎች ከዓለም ሕዝብ ሁለት በመቶ የሚሆኑት ናቸዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚ ልማት ክፍል ያሳተመዉ ይኸዉ ጥናት እንደሚለዉ የዓለምን አብዛኛ ኢኮኖሚ ከሚቆጣጠረዉ ከሁለት በመቶ ከማይበልጠዉ ሰዉ ዘጠና በመቶዉ የሚገኘዉ ሰሜን አሜሪካ፥ አዉሮጳ፥ ጃፓንና አዉስትሬሊያን በመሳሰሉ የእስያ-ፓስፊክ ሐገራት ነዉ።

Occupy-Bewegung in Berlin Flash-Galerie
የፀረ-ካፒታሊዝም ሰልፍ-በርሊንምስል dapd

ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ የሚበልጡት ድሆች ከዓለም ከኢኮኖሚ ያላቸዉ ድርሻ ባንፃሩ ጥናቱ እንዳረጋገጠዉ አንድ ከመቶ ብቻ ነዉ።ለረጅም ጊዜ እንደሚታመነዉ የድሐ ሐብታሙ የሰፋ-ክፍተት ወይም የሐብት ክምች-ድሕነቱ የማይታረቅ ልዩነት-የሚታየዉ በክፍለ ዓለማት ወይም በሐገራት መካካል ነበር።

ይሕ በርግጥ ሐሰትነት የለዉም።አሜሪካ-ምዕራብ አዉሮጳና ጃፓን በሁሉም መስክ ዓለምን ይመራሉ።አፍሪቃ ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ከሁሉም ዓለም በድሕነት አረንቋ ትዳክራለች።ሰሜን አሜሪካ፥ ምዕራብ አዉሮጳ፥ ጃፓን አዉስትሬሊያ በልፅገዋል ሲባል ግን ፕሮፌሰር ዶም ሆፍ እንደሚሉት አሜሪካዊ-ሁሉ፥አዉሮጳዊ-ጃፓናዊ በሙሉ በየሐገሩ ከተከማቸዉ ሐብት ተጠቃሚ፥ ሐብት ለማከማቸት የሚደረገዉ ሽሚያ ተካፋይ-ሐብት የማግበስበሱ ሥርዓት ዉሳኔ ሰጪ አካል ነዉ-ማለት አለመሆኑ ሊጤን ይገባል።

ከዩናይትድ ስቴትስ ሐብት 34.6 ከመቶዉን የሚቆጣጠሩት ከሐገሪቱ ሕዝብ አንድ ከመቶ የሚሆኑት የኩባንያ ባለቤቶች ናቸዉ።የኩባንያ፥ የባንክ ሥራ አስኪያጆች፥ልዩ ባለሙያዎችና የመለስተኛ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ደግሞ ከሐገሪቱ ሐብት ከግማሽ የሚበልጠዉን ይቆጣጠራሉ።የሁለቱ ድምር ከአሜሪካ ሕዝብ ሃያ በመቶዉን ይይዛል።እነዚሕ ሃያ በመቶዎቹ ናቸዉ ከሐገሪቱ ምጣኔ ሐብት ከሰማንያ አምስት በመቶ የሚበልጠዉን የሚቆጣጠሩት።የተቀረዉ ሰማንያ በመቶ የሚሆነዉ ሕዝብ ከሐገሪቱ የደለበ ሐብት የሚደርሰዉ አስራ-አምስት ከመቶዉ ብቻ ነዉ።

በ2008 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) መጀመሪያ ዩናይትድ ስቴስን አከታትሎ የተቀረዉን ዓለም የመታዉ የምጣኔ ሐብት ድቀት የዓለምን ምጣኔ ሐብት በሚቆጣጠሩት ወገኖች ሥሕተት ወይም ሰሞኑን አደባባይ የወጡት ተቃዋሚዎች እንደሚሉት በሐብታሞቹ ስግብግብነት ምክንያት የደረሰ መሆኑ አላነጋገረም።የሐብታሞቹ ሐገራት መንግሥታት አብዛኛዉ ደሐ ሕዝብ የሚከፍለዉን ቀረጥ እያነሱ ለነዚያዉ ኪሳራዉን ላደረሱት ሐብታሞች መደጎሚያ ሰጥተዋል።ደሐዉ ተቀጣሪ ባንፃሩ በኪሳራ ሰበብ ከየሥራዉ እንዲፈናቀል ተደርጓል።

የዩናይትድ ስቴትስ የአክስዮን ገበያና ግዙፍ የገንዘብ ማዕከል የሚገኝበት «ዎል ስትሪት» የተሰኘዉን አካባቢ «እንቆጣጠር» የሚል መፈክር አንግበዉ አደባባይ የወጡትን ብሶተኞች ቁጣ ያቀጣጠለዉም ወትሮም ከምጣኔ ሐብቱ እድገት ትንሽ ወይም ምንም የተጠቀሙት ድሆች የኪሳራዉ ሰለቦች መሆናቸዉ ነዉ።ይሕ ነዉ-ዲሞክራሲ ጠየቀ ሠልፈኛዉ።«ሐገራችን ስትጠፋ ድሆቹ የትነበርን»-አለ አንዱ።«ተሸጠናል»-ቀጠለ።

መልስ ይሆን ይሆን?

በ1960 እና ሰባዎቹ «ተነሱ እናንት የረሐብ እስረኞች» ነበር-የብሰተኞቹ የተቃዉሞ መፈክር-ወጉ።ዛሬ የያኔዉ መፈክር ብዙም የለም ወይም አልተሰማም።«እኛ ዘጠና ዘጠኝ በመቶዎች ነን» በሚል አዲስ መፈክር ተለዉጧል።የአመፅ-ተቃዉሞ ምክንያት ምናልባት አለማዉም ከኒዮርክ ተቃዉሞ ሠልፈኛ አስተባባሪዎች አንዱ ብሬይን ፊሊፕስ እንዳሉት ተመሳሳይ ነዉ።

Occupy Wall Street Proteste in London Großbritannien
የፀረ-ካፒታሊዝም ሰልፍ-ለንደንምስል DW

«መንግሥቱን አስወግደን ዳግም ማዋቀር እንደልጋለን።የግዙፍ ኩባንያ ሊሒቃን እርምጃ ሰልችቶናል ።አንድ በመቶዎቹ ሁሉንም ነገር ተቆጣጥረዉ ምጣኔ ሐብታችንን ማሽመድመዳቸዉ በቃን።እና አሁን መሠረት ጥለናል።ከእንግዲሕ ወደ ኋላ እንደማንመለስ አስታዉቀናል።ዩናይትድ ስቴትስን እንቀይራለን።እና ዓለምንም እንቀይራለን።»

መቶዎች ኒዮርክ የጀመሩት ፀረ-ካፒታሊዝም ተቃዉሞ ሚሊዮኖችን ለማሳተፍ መላዉ ዩናይትድ ስቴትስን ለማዳርስ ከሳምንታት በላይ አልፈጀበትም።የአዉሮጳ ከተማ-አደባባዮች የኒዮርኩ የተቃዉሞ ሠልፍ ከመጀመሩ ከወራት በፊት ጀምሮ ከሥራ ማቆም አድማ-ተቃዉሞ ሠልፍ ተላቀዉ አያዉቅም። አድማ ሠልፉ በተደጋጋሚ የተደረገዉ ግን ምጣኔ ሐብታቸዉ በከሰረዉ ወይም የመክሰር ሥጋት በተጋረጠባቸዉ እንደ ግሪክ፥ አየርላንድና ስጳኝን በመሳሰሉት ሐገራት ነበር።

የሕዝባዊዉ ሠልፍ-ተቃዉሞ ከሰሜን አፍሪቃ ጀምሮ-የአረብ ሐገራትን ነካክቶ፥ አዉሮጳን ዳብሶ ኒዮርክ-ሰንብቶ፥ አሜሪካን አዳርሶ አዉሮጳ ሲመለስ እስያንም ጨምሮ አርገፈገፋት።የሠልፉ አስተባባሪዎች እንዳስታወቁት ባለፈዉ ቅዳሜ በሚሊዮን የሚቆጠር የሐምሳ ሐገራት ሕዝብ በዘጠኝ መቶ ሐምሳ አንድ ከተሞች አደባባይ ወጥቶ የካፒታሊዝም ሥርዓት በተለይም የገንዘብ መርሁን ተቃዉሟል።

የአንዳድ ከተሞች ሠልፈኛ ከፀጥታ አስከበሪዎች ጋር መጋጨት፥ መቆራቆሱ አልቀረም።ብዙ ስፍራ ብዙዎችም ታስረዋል።በተለይ ኢጣሊያ ርዕሠ-ከተማ ሮምና ሁለተኛይቱ ትልቅ ከተማ ሚላን አደባባይ የወጣዉ ሠልፈኛ የፖሊስ ከባድ ድብደባና አፈና በመቃወም ሕንፃና መኪኖችን እስከማጋየት ደርሷል።በሌሎቹ በአብዛኞቹ ከተሞች የተደረገዉ ሠልፍ ግን ሠላማዊ ነበር።

የኮሎኝ-ጀርመን ሠልፈኞች።

በርሊን፥ ፍራንክፈርት ኮሎኝ ሌሎችም የጀርመን ትላልቅ ከተሞች የካፒታሊስቱን ሥርዓት በተለይም የገንዘብ መርሑን በሚቃወመዉ ሠልፈኛ መጥለቅለቃቸዉን ያዩት የጀርመኑ የገንዘብ ሚንስትር ቮልፍጋንግ ሸወብለ የሰልፈኛዉን መልዕክት ከልብ እከታተለዋለሁ ብለዉ ነበር።

«በታላቅ ትኩረት ነዉ የምከታተለዉ።የምር አድርጌ ነዉ-የማየዉ።ከወራት በፊት ጀምሮ ለአቻዎቼ ጉዳዩን አንስቻለሁ።አሁንም እዚሕ ለቡድን ሐያ-አባል ሐገራት ባልደረቦቼ አስቻለሁ።ፖለቲካዉ ሕግ ይደነግጋል እንጂ እኛ በገበያዉ ብቻ እንደማንመራ ግልፅ ማድረግና ማሳየት መቻል አለብን።በብዙዎች ዘንድ ያለዉ እምነት በገበያ እንደምን መራ ነዉ።ይሕን አስተሳሰብ መስበር መቻል አለብን።አለበለዚያ ቀዉሱ የማሕበረ-ምጣኔ ሐብታዊ እና የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲያዊዉ ሥርዓት ድቀትም ይሆናል።

የጀርመንን ጨምሮ ቡድን ሃያ ተብሎ የሚጠራዉ ሥብስብ የሚያስተናብራቸዉ ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮች እስከ ትናንት ድረስ ፓሪስ-ፈረንሳይ ዉስጥ ተሰብስበዉ ነበር።ተሰብሳቢዎቹ የጀርመኑ የገንዘብ ሚንስትር እንዳሉት አደባባዮችን ሥላጨናነቀዉ ሕዝባዊ ሠልፍ ማንሳታቸዉ አልቀረም። የስብሰባዉ ዋና አላማ ግን የዓለምን ምጣኔ ሐብታዊ በጣሙን የገንዘብ ቀዉሱ የደረሰበትን ደረጃ መገምገም ነበር።

ዋና ትኩረቱ ደግሞ ግሪክን በመሳሰሉ የአዉሮጳ ሐገራት የደረሰዉ ኪሳራና መላዉ የዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚ ሐገራትን የሚያሰጋዉ ድቀት የሚወገድበት ሥልት እንጂ ለተቃዉሞ ሠልፈኛዉ መልስ መስጠት አልነበረም።በካፒታሊስቱ ስርዓት ተገፋን ያሉና የሚሉ ወገኖችን የአደባባይ ጩኸት ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ግዙፍ መገናኛ ዘዴዎችም ሰልፈኞቹ እንደሚሉት ተገቢዉን ትኩረት አልሰጧቸዉም።

የቱኒዚያ እና የግብፅ ሕዝብ በየረጅም ገዢዎቹ አገዛዝ ላይ ሲያምፅ «ፌስቡክን» የመሳሰሉት የዘመኑ የኤሌክትሮኒክ ቴክኖሎጂ ዉጤቶች ያበረከቱት አስተዋፅኦ የዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የጠዋት ማታ ርዕሥ ነበር።የሊቢያ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ገዢዉን መቃወም ሲጀምር ለፓሪስ-ለንደን፥ ዋሽንግተን መሪዎች ተቃዉሞዉ የዓለምን ምርጥ ጦር ድጋፍ የሚያስፈልገዉ ነበር።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ የጦር አዉሮፕላኖች ድብደባ-ድል ለቢቢሲ፥ ለአል-ጀዚራ፥ ይሁን ለሲኤን ኤን የሰዓት-በሰዓት ትኩስ፥ ትልቅ ዜና ነበር።

የመማር-የመስራት እድል የተነፈጉ ወይም ያጡ የለንደን ወጣቶች ባለፈዉ ነሐሴ ሲያምፁ በብሪታንያ መንግሥት፥ በብሪታንያና በአብዛኞቹ ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎችም «ጋጠወጦች» ተባሉ።የቱኒዚያና የግብፅን ወጣቶችን ለአድማ-ሠልፍ ፈጥነዉ በማገናኘታቸዉ የተወደሱ፥ የተመሰገኑ፥ የተደነቁት «ፌስቡክን»ና ሌሎች የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም የለንደን ወጣቶችን ሲያገናኙ ተወገዙ፥ ወይም ተዘጉ።
ባለፈዉ ቅዳሜ ለንደን የተደረገዉን ሕዝባዊ ሠልፍ የተከታተሉት ብሪታኒያዊዉ ደራሲ አፍሺን ራታንዚ እንዳሉት የብሪታንያ መገናኛ ዘዴዎች የሠልፈኛዉን ጥያቄ፥ አለማና ብዛቱን፥ መዘገብ የሚገባቸዉን ያክል አልዘገቡም።እና ለንደን ዉስጥ ቢያንስ የዚያን ቀን ለደራሲዉ የፕረስ ነፃነት አልነበረም።

«የብሪታንያ ፖሊስ በጣም አደገኛ ሥልት እየተከተለ ነዉ።ሰዎች ሰልፉን እንዳይቀየጡ፥ ጋዜጠኞች ከሠልፈኛዉ ጋር እንዳይገናኙ እያገዱ ነዉ።የብሪታንያ ሕዝብ በመላዉ ሐገሪቱና በዓለም ሥለሚደረገዉ ሠልፍ እንዲያዉቅ ዋና ዋና መገናኛ ዘዴዎች የዘገቡት በጣም ትንሽ ነዉ።ሠልፈኞቹ እራሳቸዉን እንደሚገልፁት ዘጠና-ዘጠኘ በመቶ የሚሆነዉ ሕዝብ ጥያቄን የብሪታንያ ሕዝብ እንዳያዉቀዉ ተደርጓል።በጣም አደገኛ ሥልት ነዉ።እና ዛሬ ለንደን ከተማ ዉስጥ በርግጥ የፕሬስ ነፃነት የለም።»

የፕረስ ነፃነት።የመገናኛ ዘዴዎቹ ባለቤትስ ማነዉ-የነዉ ጥያቄዉ? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ