1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታዉ ምክር ቤትና ጀርመን

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 2 2003

የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለጀርመን-የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር በአምደ-መረቡ እንዳሰፈረዉ «ለአለም ሠላም የሚደረገዉ ጥረት የሚዘወርበት እምብርት ነዉ።»

https://p.dw.com/p/Pclt
የፀጥታዉ ምክርቤትምስል AP

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ «አዉሮጳና ሌሎች» የሚባለዉን ክፍል በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት የሚወክሉ ሁለት ሐገራትን ዛሬ ይመርጣል።ለሁለቱ መቀመጫዎች ጀርመን፥ ፖርቱጋልና ካናዳ እየተወዳደሩ ነዉ።ጀርመን ሁለት አመት የሚዘልቀዉን መቀመጫ ለማግኘት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ሥታደርግ ነዉ የከረመችዉ።ዛንድራ ፔተርስማን እንደዘገበችዉ ጀርመን ከተለዋጩ መቀመጫ ባለፍ ወደፊት ይሻሻላል ተብሎ በሚታመነዉ በምክር ቤቱ ዉስጥ ቋሚ መቀመጫ ለመግኘት መጣር የጀመረችዉ ዳግም ከተዋሐደች ጀምሮ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝሩ ዝሩን አጠናቅሮታል።

የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለጀርመን-የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር በአምደ-መረቡ እንዳሰፈረዉ «ለአለም ሠላም የሚደረገዉ ጥረት የሚዘወርበት እምብርት ነዉ።» የዚያኑ ያክል አለም አቀፉ ድርጅት ባጠቃላይ፥ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት፥ በተለይ በአዲስ መንገድ ይዋቀር የሚለዉ ሐሳብ ጀርመን ዳግም ከተዋሐደች ወዲሕ ከምትከለዉ አብይ የዉጪ መርሕ አንዱ ነዉ።

የቀድሞዉ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐንስ ዲትሪች ጌንሸር በዉሕደቱ ማግሥት እንደ ጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1991 ይሕን የሐገራቸዉን አለማ አንስተዉት ነበር።-
«የተዋሐደችዉ ጀርመን ላንዴና ምንጊዜም ከነፃነትና ከዲሞክራሲ፥ ከሰብአዊ መብት እና ከሰዉ ልጅ ልዕልና ጎን በፅናት ትቆማለች።እኛ አለም የሚገጥማትን ፈተና ለመቋቋም እንደ አንድ አዉሮጳና ጀርመን በጋራ መቆም እንፈልጋለን።በዚች ዓለም የሚገኝ ማንኛዉንም ሰዉ እንደራሳችን የምንወድ መሆናችንን በአለም የሚገኝ ሰዉ ሁሉ ሊያዉቅልን ይገባል።»

Guido Westerwelle UN Vollversammlung
የጀርመን ዉጉሚ ቬስተርቬሌ-በተመድ ጉባኤምስል AP

ጌንሸርን የተኩት ክላዉስ ኪንክል ደግሞ ከቀዳሚያቸዉም እልፍ ብለዉ፥ የዲፕሎማሲያዊዉን የግድም ድሞሽ ቋንቋ ትተዉ ጀርመን በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የማግኘት ፍላጎትዋን በግልፅ ተናገሩ።

«የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አስካሁን ድረስ በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ፍፃሜ የነበረዉን ሁኔታ እንጂ እያደገ የመጣዉን የጃፓንና የተዋሐደችዉ ጀርመንን አስተዋፅኦ የሚያንፀባርቅ አይደለም። ጀርመን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባል እንድትሆን የደገፉትን አባል ሐገራትና መንግሥታት በሙሉ አመሰግናለሁ።»

ጀርመን ቋሚ አባል የመሆን ጥያቄና ፍላጎትዋ፥- የቅርብ ወዳጆችዋ ከሚባሉት ሐገራት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመሳሰሉት ያገኘችዉ ምላሽ ቀዝቃዛ-ይሁንታ አይነት፥ ኢጣሊያና ፈረንሳይን ከመሳሰሉት ደግሞ ጭራሽ ተቃዉሞ ብጤ ነበር።እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1998 ሥልጣን የያዘዉ የሶሻል ዲሞክራቶቹና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ተጣማሪ መንግሥት ለሐሳቡ የአዉሮጳ ሕብረትንና የሌሎች ሐገራትን ድጋፍ ለማግኘት መጠነ-ሰፊ ዘመቻ ነበር የከፈተዉ።

የያኔዉ መራሔ መንግሥት ጌርሐርድ ሽሩደርም ሐገራቸዉ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ማግኘት የለባትም የሚሉ ሐገራትን በግልፅ ነበር የተቹት።
«እንዲሕ አይነት አስተያየት የሚሰጥ፥ የሚናገረዉ ስሕተት ነዉ።እኛ ለተባበሩት መንግሥታት
ድርጅት ከፍተኛዉ መዋጮ ከሚሰጡት ሰወስተኞቹ ነን።ሠላም ለማስከበር በርካታ ወታደሮች በማዝመት ሁለተኞች ነን።ከዚሕ በላይ ምን አይነት ተጠያቂነት ነዉ-የሚፈለገዉ።»

ጠየቁ። በርግጥም ሽሮደር የሚመሩት መንግሥት ከሌሎች ሐገራት ጋር በመተባበር ባደረገዉ ዘመቻ የአዉሮጳና የአፍሪቃን ጨምሮ የበርካታ ሐገራትን ድጋፍ ማግኘት ችሎ ነበር።ይሁንና የነሽሮደር ዘመቻ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ከሚመሩት ከዩናይትድ ስቴትስ መስተዳድር ግልፅ እንቅፋት ነዉ የገጠመዉ።የዚሕ ምክንያቱ ሽሮደር እና የያኔዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዮሽካ ፊሸር የኢራቅን ወረራ በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ መቃወማቸዉ ነበር።

ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዲሞክራቶቹና የነፃ ዲሞክራቶቹ ጥምር መንግሥትም የፀጥታዉ ምክር ቤት ሥራና አሠራር እንዲሻሻል፥ ጀርመንም ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ ቀዳሚዎቹ የጀመሩትን ዘመቻ እንደቀጠለበት ነዉ።ዛሬ ከኒዮርክ የሚጠበቀዉ ግን ሁለት አመት የሚቆየዉን የምክር ቤቱን ተለዋጭ መቀመጫ-ጀርመን ማግኘት አለማግኘትዋ ነዉ።

ዛንድራ ፔተርስማን

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ