1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መቀመጫ ጀርመን፥ ካናዳ እና ፖርቱጋል

ሰኞ፣ መስከረም 17 2003

አንዳድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ጀርመን ከሁለቱ መቀመጫዎች አንዱን ለማግኘት የዘጠና በመቶ ድጋፍ አላት።ካናዳ-ስልሳ ከመቶ፥ ፑርቱጋል አርባ-ከመቶ።የመቶ ዘጠና ሁለቱ አባል ሐገራት አምባሳደሮች ድምፅ ሲሰጡ ይለያል።ጥቅምት-ሁለት።

https://p.dw.com/p/PNsb
ጠቅላላ ጉባኤምስል AP


25 09 10

የአዉሮጳ ሕብረት ጉባኤ-ዉሳኔ ቢሆን ኖሮ-በርሊን የሚነገር-የሚታቀደዉ ሊዝቦን ከሚባል-ከሚታለመዉ ከቋንቋ ባለፍ አንድ በሆነ ነበር።የቡድን ሥምንት መርሕ-አቋም ቢሆን ኖሮ የበርሊን ኦታዋ ልዩነት ያገላለጥ-ብቻ በሆነ ነበር።የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ዘመቻ ቢሆን ኖሮ ደግሞ የጀርመን፥ የካናዳ እና የፖርቱጋል ጦር ባንድ ዕዝ በታዘዘ ነበር።እንደ እስከ ዘንድሮዉ ቢሆን ኖሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ-አቋምም አንድነታቸዉን እንጂ ሰወስትነታቸዉን አይመሰክርም።ዘንሮ ግን በርሊን፥ ኦታዋ-ሊዝበን ሰወስት ሆነዉ ለፀጥታዉ ምክር ቤት ሁለት መቀመጫዎች ይሻኮታሉ።የሽሚያ ሽኩቻዉ ምክንያት-እንዴትነት የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

የካናዳዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሎሬንስ ካኖን ለሐገራቸዉ ድጋፍ ለማሰባሰብ ኒዮርክ የሚገኙትን የዲፕሎማሲ ደጃፎች ማንኳኳት ከጀመሩ ባለፈዉ ቅዳሜ ሳምንት ደፈኑ።ካኖን አዉስትሬሌያ እና ኒዉ ዝላንድን የመሳሰሉት የሐገራቸዉ ጥብቅ ወዳጆች አቻዎቻቸዉ በዘመቻዉ እንዲተባበሯቸዉ ያደረጉት ጥረት መሳካቱ ባለፈዉ ማክሰኞ ከኒዮርክ ሲዘገብ ብራዚል ከደቡብ አሜሪካ አንጎላና ሞዛምቢክ ከአፍሪቃ ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸዉ ወገነዉ ወዳጅ-አጋሮቻቸዉን ለማስተባበር መዘጋጀታቸዉ ከኒዮርክ በሊዝበን በኩል ተሰማ።

Westerwelle / UN / Vollversammlung / New York
ቬስተርቬለ-በጀርመን ተማመኑምስል AP

ነገ ሳምንቱ።የዚያኑ ዕለት የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ የሚያነጋግሩቸዉን መሪ ዲፕሎማቶች ዝርዝር፥ የሚናገሩትን ፍሬ ነገር ያጨቁበትን ሻንጣ አንጠልጥለዉ ከበርሊን ተነሱ።ተስፋም ሰንቀዋል።

«ሰፊ እድል አለን።ግን እስከ መጨረሻዉ ጠንክረን መስራት አለበን።በእርግጥ በጣም ጥሩ ዉጤታማና ጠንካራ ተፎካካሪዎች እንዳሉንም መዘንጋት የለበትም።»

ቬስተርቬለ በኒዮርኩ የዲፖማሲ ዘመቻ፥ ጥድፊያ መሐል መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ከኒዮርክ ወደ በርሊን ለመሸኘት ሲዘጋጁ፥ ከቬስተርቬለ ቀድመዉ የዲፕሎማሲዉን መን ሲገምዱ-ሲጠልፉ የሰነበቱት ካናዳዊዉ አቻቸዉ ሎዉሬንስ ካኖን ጠቅላይ ሚንርትር ስቴፋን ሐርፐር ለመቀበል ሽቅብ ቁል ቁል ይሉ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሥራ-አሠራርን በጣሙን በየአመቱ መስከረም የሚሰየመዉን የድርጅቱን የመሪዎች ጉባኤን የ«እንቶ-ፋንቶ» ወሬ መሰለቂያ አድርገዉ የሚያዩት የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር ስቴፋን ሐርፐርነዉ ባለፉት ሰወስት አመታት በተደረገዉ ጉባኤ ላይ ተገኝተዉ አያዉቁም ነበር።ዘንድሮ ግን እንደ እስከ ዘንድሮዉ ሊያጣጥሉ-ሊንቁት አይችሉም።መገኘት አለባቸዉ።

Wahlen in Kanada Stephen Harper
ሐርፐር-ካናዳ ይገባታልምስል AP

እና ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል ኒዮርክ ላይ የሚሉ-የሚያደርጉትን አከናዉነዉ በርሊን እንደገቡ የካናዳዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሐርፐር ለኒዮርክ ጠቅላላ ጉባኤዉ፥ ካናዳ «አዉሮጳና ሌሎች» ለሚባለዉ ቡድን ከተመደቡት ሑለት መቀመጫዎች አንዱን ለማግኘት ብቃቱ፥ አገልግሎቱ፥ ደግነቱም ያስመርጣታል-ይሉ ያዙ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1945 ( ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) ሲመሰረት ከሁለተኛዉ አለም ጦርነት የተላቀቀችዉን አለም ሠላምና ፍትሕ እንዲያስጠብቅ ታስቦ-ታልሞ፥ በጦርነቱ ዉጤት ላይም ተመስርቶ ነበር።ከያኔ እስካሁን አለም በእጅጉ ተለዉጣለች።አለምን የሚስተባብረዉ አለም አቀፍ ድርጅትም ከተለወጠችዉ አለም እዉነታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ይለወጥ ባዮች አልጠፉም።ግን አልተለወጠም።በትክክለኛዉ አባባል ድርጅቱንም አለምንም ከፊት ሆነዉ የሚዘዉሩት ወገኖች ለአለም ሠላም ፍትሕ የቆመዉ ድርጅት ፍትሐዊ እንዲሆን አልፈቀደም።ወይም ያቅማማሉ።

በዚሕም ምክንያት የድርጅቱ ወሳኝ አካል መሆን የነበረበት ጠቅላላ ጉባኤዉን-ራሱን ብዙዎች እንደሚያዉቁት የዘንድሮዉ የጉባኤዉ ፕሬዝዳት ስዊዘርላንዳዊዉ ዲፕሎማት ዮሴፍ ዳይስ እንደመሠከሩት ከመጨቃጨቂያ ክበብነት ያለፈ አቅም የለዉም ብለዉ ነዉ።
«መገናኛ ዘዴዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤን ብዙ ጊዜ የሚያቀርቡት አቅመ-ቢስ አድርገዉ ነዉ።በተጨባጭ ትርጉም የሌለዉ የመከራከሪያ ክበብ አድገዉ ነዉ።»

ጠንካራዉን ሥልጣን ጠቅልሎ የያዘዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ነዉ።ከምክር ቤቱ አስራ-አምስት አባል ሐገራት መካከል ደግሞ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸዉ አምስቱ ቋሚ አባላት ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ፥ ሩሲያ፥ ብሪታንያ ፈረንሳይ እና ቻይና።የድርጅቱ አብይ ተልዕኮ የአለምን ሠላም ማስከበር፥ ፍትሕንና ሠብአዊ መብትን ማስረፅ ነዉ።

ለነዚሕ ተልዕኮዎቹ ስኬት የሚያስፈልገዉን ገንዘብ በማዋጣት ከዩናይትድ ስቴትስ በስተቀር ጃፓንን የሚስተካከል ሐገር የለም።ከዩናይትድ ስቴትስና ከጃፓን በስተቀር ጀርመንን የሚያክል ሐገር የለም።አለም አቀፉ ድርጅት ተልዕኮዉን እንዲያስፈፅም እንደ ድርጅት እንዲንቀሳቀስም ከፍተኛዉን ገንዘብ በማዋጣት ሁለተኛዉን እና ሰወስተኛዉን ደረጃ የያዙት ጃፓንና ጀርመን የአለምን ሥርዓት በመወሰኑ ሒደት ሙሉ ተሳታፊዎች አይደሉም።

ብሪታንያ፥ ፈረንሳይና ሩሲያና ቻይና ግን ወሳኞች ናቸዉ።ከቻይናና ከሩሲያ ይልቅ ከናዳ ለድርጅቱ ከፍተኛዉን ገንዘብ ታዋጣለች።ሁለቱ እንጂ ካናዳ ወሳኝ አይደለችም።አምስቱ ሐገራት የአለምን ሁለንተናዊ ሥርዓት ሒደት-እንዴትነት የሚበይነዉን ሥልጣን የያዙት ከስልሳ አመት በፊት የነበረዉን ጦርነት ከማሸነፋቸዉ ባለፍ ሌላ ብዙ ምክንያት-አመክንዮም ኖሯቸዉ አይደለም።

EU-Gipfel - Luis Amado
አማዶ-የተማከለ ዲፕሎማሲ አለንምስል AP

ከአንድ መቶ ዘጠና ሁለቱ አባል ሐገራት የተቀሩት አንድ መቶ ሰማንያ ሰባቱ አንድም በአቅመ ቢሱ ጠቅላላዉ ጉባኤዉ ይነታረካሉ፥ ሁለትም የቀሩትን የፀጥታዉ ምክር ቤትን አስር መቀመጫዎች በየሁለት አመቱ አንዴ ለመያዝ በየአካባቢያቸዉ ይሻኮታሉ።ዘንድሮ ካናዳን፥ ጀርመንና ፖርቱጋልን የሚያሻኩቱት ከአስሩ መቀመጫዎች ለ-አዉሮጳና ለተቀረዉ አለም የተመደቡት ሁለት መቀመጫዎች ናቸዉ።

የካናዳዉ ጠቅላይ ሚንስትር ስቴፋን ሐርፐር ባለፈዉ ሐሙስ ለጠቅላላዉ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ሐገራቸዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች መሆንዋን፥ ለድርጅቱ ገንዘብ በማዋጣት ከሰባቱ ቀደምት ሐገራት አንዷ መሆንዋን፥ ሠላምን ለማስከበር ወታደሮችዋ አፍቃኒስታንን በመሳሰሉ አካባቢዎች ሕይወት-አካላቸዉን እየከፈሉ መሆናቸዉን በመጥቀስ ከሁለቱ መቀመጫዎች አንዱ እንደሚገባት ጠየቁ።

የሐርፐርን ንግግር ከኒዮርክ ሲተላለፍ ሊዝበን አዉሮፕላን ማረፊያ ሆነዉ የተከታተሉት የፖርቱጋሉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሉዊስ አማዶ ፖርቱጋል ከሁለቱ መቀመጫዎች አንዱን እንደምታገኝ እርግጠኛ ነኝ አሉ-ለጋዜጠኞች።ምክንያት-«ሊዘበን የምትከተለዉ ዲፕሎማሲ ሁሉንም ያማከለ፥ እና ሚዛናዊ በመሆኑ።» አከሉ እና ጠቅላይ ሚንስትር ሆሴ ስክራትስን ተከትለዉ ካዉሮፕላን ገቡ።ጉዞ ወደ ኒዮርክ።

የጠቅላላ ጉበኤዉ አዳራሽ አንድ-ሺሕ ስምንት መቀመጫዎች አሉት።የአለም ሐገራት፥ መሪዎች፥ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ብዙ ጊዜ ግን አምባሳደር ዲፕሎማቶች ይታጨቁበታል።የእያንዳዱ ሐገር ተወካይ ለአስራ-አምስት ደቂቃ የመናገር እድል አለዉ።ንግግሩ-የየተናጋሪዉን መንግሥት ወይም ሐገር ይፋዊ አቋም ለጉባኤተኞችና ለአለም በይፋ ከማሳወቅ ባለፍ ብዙም የሚተከረዉ ነገር የለም።ዋናዉ ሥራ ከጉባኤዉ ጀርባ በየሻይ-ቡና-ምሳ ቤቱ፥ በየቢሮ-ሆቴል፥ ኮሪደሩ የሚደረገዉ ዉይይት-ንግግር ማባበል-ማግባባት ነዉ።ዲፕሎማሲ።

የፖርቱጋሉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሉዊስ አማዶ ለመጋረጃ ጀርባዉ ማግባባት ጠቅላይ ሚንስትራቸዉን አስቀድመዉ ኒዮርክ ሲገቡ የጀርመኑ አቻቸዉ ጊዶ ቬስተርቬለ ለሐገራቸዉ ድጋፍ ለማሰባሰብ የሰላሳ-አንድ ሐገራት ተወካዮችን አነጋግረዉ ነበር።ጀርመን ከጃፓንና ከአዉስትሬሊያ ጋር በመሆን አለምን ከኒኩሌር ጦር መሳሪያ ለማፅዳት የሚከራከር አለም አቀፍ ቡድን እንዲመሠረት ጥረት እያደረገች መሆንዋን አስታዉቀዉም ነበር።

«ጀርመን ከጃፓንና ከአዉስትሬሊያ ጋር በመሆን አዉዳሚ የጦር መሳሪያንና የኑክሌር ጦር መሳሪያ ምርትን ለማስወገድ ግፊት የሚደርገዉ የአለም ሐገራት ቡድን መስራች ናት።»

እንዲሕ አይነቱ አቋም የጀርመንን መንግሥት መርሕ ከማስተዋወቅ ሌላ የቡድኑን አባላት ከሁሉም በላይ አለም ከኒክሌር ጦር መሳሪያ መፅዳት አለባት የሚል መርሕ የሚከተለዉን የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማን መስተዳድር ልብ ለማማለል ጠቃሚ ነዉ።

ከዚሕ ቀደም በአማካይ በየአስር አመቱ አንዴ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ተዘዋዋሪ መቀመጫን የያዘችዉ ካናዳ ከድርጅቱ መስራች፥ ብዙ ገንዘብ ከፋይነቷ ባለፍ ለአዳጊዎቹ ሐገራት የምትሰጠዉ ርዳታ፥ በአለም ያላት ጫና እና እዉቅና በቀላሉ ያስመርጣት ነበር።አሁን ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞዉ የካናዳ አምባሳደር ያቪስ ፎርትየር እንደሚሉት የጠቅላይ ሚንስትር ሐርፐር መንግሥት የሚከተለዉ መርሕ የካናዳን ጥሩ-ስምና ዝና እያደበዘዘዉ ነዉ።

የሐርፓር መንግሥት ተቺዎቹ እንደሚሉት በአለም አቀፉን ድርጅት አበክሮ እየተሳተፈ የድርጅቱ ሥራና አሠራር እንዲሻሻል ከመጣር ይልቅ ድርጅቱን ለአራት አመት ያሕል ርቆታል።ከዚሕም በተጨማሪ ካናዳ ለአዳጊዎቹ ሐገራት የምትሰጠዉን ርዳታ የሐርፐር መንግሥት ከአፍሪቃ እየቀነሰ ወደ ደቡብ አሜሪካ መላኩ የአፍሪቃዉያንን ድምፅ ሊያሳጣዉ ይችላል።

የካናዳ ዲፕሎማቶች የድምፅ ሰጪዎችን ቀልብ ለመሳብ ሐገራቸዉ ታደርጋለች የሚሉትን አስተዋፅኦ ከመዘርዘር እኩል-በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ሰወስት ቋሚ መቀመጫ (ብሪታንያ፥ ፈረንሳይና ሩሲያ) ያላቸዉ፥ አዉሮጶች አሁን ባንዴ ሁለት መቀመጪያ ሊያገኙ አይገባም እያሉ ነዉ።

ጀርመን ከዚሕ ቀደም አራት ጊዜ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባል ሆና አገልግላለች።አሁን በሚደረገዉ ፉክክር ከተመረጠች የአለም አቀፉን ድርጅት አሰራርና አወቃቀር ለማሻሻል ከአምስት አመት በፊት የተጀመረዉ እቅድ ገቢር እንዲሆን እንደምትጥር መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አልሸሸጉም።
«እና ከዚሕም በተጨማሪ ለብዙ አመታት የዘገየዉን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን (መዋቅር) ማሻሻል (አንዱ ) ነዉ።»

የሐብት-ጉልበት ግዛት ትልቅነትን ለድሮ ታሪክ ትታ-ትንሽነትን የሙጥኝ ያለችዉ አዉሮጳዊት ሐገር ፖርቱጋል የትንሽነትዋን ያክል የቀድሞ ቅኝ ተገዢዋ-ያሁን ለትልቅነት ተንጠራሪዋን የብራዚልንና የብራዚል ደጋፊዎችን ድጋፍ እንደምታገኝ እርግጠኛ ናት።ከአፍሪቃም አንጎላ፥ ሞዛምቢክ፥ ጊኒ ቢሳዎን የመሳሰሉት እና የነሱ ደጋፊዎች ይመርጧታል።ብዙዎቹ የአዉሮጳ ሐገራትም ከጀርመን ባያስቀድሟት ከካናዳ እንደማያስቀሯት ግልፅ ነዉ።

ከዚሕም በተጨማሪ የፀጥታዉ ምክር ቤት የምዕራቡን መርሕ በግንባር ቀደምትነት የሚያሾሩት ሐብታም ሐገራት እንዳይበዙበት የሚሹ፥ በጋራ ብልፅግና ማሕበር አቋምና መርሕ የተማረሩ ቢያንስ ከካናዳ ይልቅ ፖርቱጋልን መምረጣቸዉ አይቀርም።ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምትሰጠዉ ገንዘብ፥ ባለሙያ ብዙ የሚጠቀስ አይደለም።ያዘመተቻችዉ ሠላም አስከባሪ ወታደሮች ቁጥርና የተሳተፈችባቸዉ ተልዕኮዎች ብዛት ግን ከተወዳዳሪዎችዋ ቢበልጥ እንጂ አያንስም።

ክፉኛ የመታት የምጣኔ ሐብት ድቀት ግን ተስፋ-ምኞትዋን እንዳጨናጉለዉ ማስጋቱ አልቀረም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ትናንት ለጠቅላላዉ ጉባኤ እንደነገሩት ግን ፖርቱጋል ከተመረጠች ሐላፊነትዋን ለመወጣት አቅሙ፥ ፍላጎቱ፥ብቃቱም አላት።

ጀርመን ፉክክሩን በአሸናፊነት መወጣቷ እንደ ሐገር ለጀርመኖች፥ እንደ መስተዳድ ለተጣማሪዉ መንግሥት ታላቅ ድል ከመሆኑ እኩል፥እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለመጀመሪያ ጊዜ በጠቅላላዉ ጉባኤ ለተካፈሉት ለጊዶ ቬስተርቬሌ የግልም-ድርብ ድል ነዉ የሚሆን።ለድርብ ድሉ ሥምረት በጀርመንን ተማመኑ አሉ-ቅዳሜ።

«ክቡር ፕሬዝዳት የጀርመን የዉጪ መርሕ የሰላም መርሕ ነዉ።በዚሕ መፀዉ ጀርመን ቋሚ ያልሆነዉን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መቀመጫን ለማግኘት ትወዳደራለች።ምክንያቱም በተለይ ለነፃነትና ለልማት አበክረን መስራት እንፈልጋለንና----በጀርመን መተማመን ትችላላችሁ።በጀርመን ተማመኑ።»
አንዳድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ጀርመን ከሁለቱ መቀመጫዎች አንዱን ለማግኘት የዘጠና በመቶ ድጋፍ አላት።ካናዳ-ስልሳ ከመቶ፥ ፑርቱጋል አርባ-ከመቶ።የመቶ ዘጠና ሁለቱ አባል ሐገራት አምባሳደሮች ድምፅ ሲሰጡ ይለያል።ጥቅምት-ሁለት።

ዶይቸ ቬለ፣ የዜና ወኪሎች

ነጋሽ መሀመድ

አርያም ተክሌ