1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይኛ ቋንቋ ዕጣ በርዋንዳ

እሑድ፣ የካቲት 14 2002

ለሀገራቸው ትልቅ ራዕይ ያላቸው ጠንካራ የተሀድሶ ለውጥ አራማጅ በመሆን ይታወቃሉ። የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖዉል ካጋሜ። ካለ ፖለቲካ መፍታታት የኤኮኖሚ ዕድገት ማስገኘት ያስችላል የሚሉትን ጥጥር የልማት ፖለቲካ ሞዴል አራማጅም ሆነው ይታያሉ።

https://p.dw.com/p/M71Z
የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖዉል ካጋሜምስል DW-TV

በዚሁ ፖሊሲያቸው መሰረትም የእንግሊዝኛ ቋንቋ በሀገሪቱ የሚሰራበትን የቀድሞውን ቅኝ ገዢ ቋንቋ፡ ፈረንሳይኛን እንዲተካ ይፈልጋሉ። የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶችም በወቅቱም በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲያስተምሩ እየተደረገ ነው፤ ምንም እንኳን ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎቹ መምህራን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ባይኖራቸውም። ይህ በሀገሪቱ ለሚገኙት ወደ ሀምሳ ሺህ ለሚጠጉት መምህራን ትልቅ ፈተና ሆኖዋል፤ አንዱ መምህር እንዳስረዱት።

ካለፉት ሀያ ሁለት ዓመታት ወዲህ በመምህርነት የተሰማሩት ፊዴሌ ኒያንጌዚ እንደገና ክፍል ውስት ገብቶ ትምህርት ለመከታተል ዕድኤአቸውትልቅ ነው። ሆኖም በሰሜን ርዋንዳ በምትገኘው በጉዋንጊሪ ከተማ በአንድ ክፍል መጨረሻ መደዳ ተቀምጦ ትምህርት ሲከታተል ይታያል።

« ብዙዎቻችን በመጀመሪያ ደረጃ እና በኋላም በሁለተኛ ደረጃ የተማርነው የፈረንሳይኛን ቋንቋ ነው። እንግሊዝኛ ቋንቋ መናገሩ ለኛ ከባድ ነው፤ ምንም እንኳን ሰዋስዉን እና የዓረፍተ ነገር አሰካክን ብንማርም፡ እንግሊዝኛውን የመናገሩ ልማድ ይጎድለናል። በዚህ ትምህርት ግን አሁን እንግሊዝኛውን መናገር ጀምረናል። »

ቋንቋውን ለመቀየር የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረጉ ቀላል አይሆንም። ሁሉንም የትምህርት ክፍሎች፡ ሂሳብ፡ ባየሎጂ፡ ኬሚስትሪ ወይም ታሪክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መሰጠት አለባቸው። ይሁንና፡ ርዋንዳ በሀገርዋ ያሉትን መምህራን በጠቅላላ ትምህርት ቤት በሚዘጋበት የዕረፍት ጊዜ ውስጥ ብቻ የሚያሰለጥንላት በቂ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ኃይል ተጓድላታል። ይህን ችግርዋን ለማቃለል በማሰብ ከጎረቤት ዩጋንዳ መምህራን ቀጥራለች። ከነዚህም አንዱ አይዛክ ጋቪየር ነው።

« አይደለም፡ አይደለም፡ ችግሩን ባጭር ጊዜ ማስወገድ አይቻልም። ቋንቋው የሚቀየርበት ድርጊት ቀስ በቀስ መደረግ ያለበት ነው። እንደማስበው አስራ አምስት ዓመት ገደማ ያስፈልጋል፣ እንደሚታወቀው የፈረንሳይኛ ቋንቋ በርዋንዳ ህዝብ ዘንድ ስር የሰደደ ነው። የርዋንዳ መንግስት ይህንኑ ለውጥ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለማስተዋወቅ ያወጣው ስልት ጥሩ ርምጃ ይመስለኛል። የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች አሁን እንግሊዝኛ ቋንቋን ይማራሉ። በዚሁ ትልቅ ዓብዮታዊ ለውጥ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን በመቻሌ ተደስቼአለሁ። »

Ruanda Kigali An Armenviertel geht der wirtschaftliche Aufschwung spurlos vorüber
የርዋንዳ መዲና ኪጋሊምስል Ch.Kaess

የቋንቋ ለውጥ ለማድረግ ለተወሰነበት ድርጊት የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፖለቲካ እንዲሁም የኤኮኖሚ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ልክ እንደ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ብዙዎቹ የርዋንዳ ከፍተኛ መደብ አባላት በስደት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ሀገሮች ውስጥ፡ ለምሳሌ በዩጋንዳ፡ በታንዛንያ ወይም በብሪታንያ ነው ያደጉት። ብዙዎቹም በሁቱ ጎሳ አባላት ይመራ የነበረው የሀገሪቱ መንግስት በሀምሳኛዎቹ ዓመታት የመጀመሪያውን ጭፍጨፋ ባካሄደበት ጊዜ ርዋንዳን ለቀው የተሰደዱት የቱትሲ ጎሳ አባላት ናቸው። እነዚህ አሁን ወደ ሀገራቸው የተመለሱት የርዋንዳ ዜጎች ታድያ ፈረንሳይኛ አለመናገራቸው በሀገር ውስጥ ችግር መፍጠሩ አልቀረም። የውጭ ፖለቲካውን ችግር ሲመለከቱት ከሁለት አሰርተ ዓመታት ገደማ በፊት የተፈጸመው የጎሳ ጭፍጨፋ በዚሁ ውስኣኔ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳረፈ ይገመታል። ፈረንሳይ በርዋንዳ ላይ ያላትን ተጽዕኖ ለማብቃት ትፈልጋለች፡ ምክንያቱም፡ ፈረንሳይ ለዚያን ጊዜው የሁቱ መንግስት በቱትሲዎች ላይ የፈጸመውን የጎሳ ጭፍጨፋ ማካሄጃ የተጠቀመበትን የጦር መሳሪያ አቀብላለች ብላ ነው የምታምነው፤ ፈረንሳይ ይህን ወቀሳ ሀሰት ስትል እንዳስተባበለች ነው። በሁለቱ ሀገሮች መካከል የቀጠለው የርስበርስ መወቃቀስ ግንኙነታቸውን ከማሻከር አልፎ ሁለቱ ሀገሮች ለብዙ ዓመታት ዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን እስካለፈው ህዳር ወር ድረስ እንዲያቋርጡ ምክንያት ሆኖ ነበር። የርዋንዳ ፕሬዚደንት በሚቀጥለው ሳምንት ዓርብ በመዲናይቱ ኪጋሊ ከፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኒኮላ ሳርኮዚ ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ ሆነዋል። ይሁንና፡ ዩኤስ አሜሪካ እና ብሪታንያ አሁን ወነኞቹ የርዋንዳ ተጓዳኞች ከመሆናቸው ሌላ፡ የኮመንዌልዝ አባል እስከመሆን ደርሳለች። እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ ሀገሮች በሚጠቃለሉበት የምስራቅ አፍሪቃ ህብረትም ውስጥ ተዋህዳለች። የቋንቋ ለውጥ የኤኮኖሚውን ውህደት ያቃልልላታል ብላ ተስፋ ማድረጓን ቻርልስ ጋሂማ፡ የትምህርቱን መመሪያ የሚያዘጋጀው መስሪያ ቤት ኃላፊ አስረድተዋል።

አርያም ተክሌ/DW