1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ የ 6 ወራት የአውሮፓው ኅብረት የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን መገባደድ፣

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2001

ያቀፈውን የአውሮፓውን ኅብረት የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ፣ ፈረንሳይ፣ ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ በመረከብ፣ የሚጠበቅባትን ተግባር ስታከናውን ከቆየች በኋላ፣ ከ 15 ቀናት በኋላ ትደመድማለች።

https://p.dw.com/p/GHUU
የወቅቱ የአውሮፓው ኅብረት ፕሬዚዳንት፣ የፈረንሳይ ርእሰ-ብሔር፣ ኒኮላ ሳርኮዚ፣ምስል AP

በየ 6 ወራት የሚፈራረቀውን፣ አሁን 27 አገሮችን በተዘዋዋሪው ልዩ መብት መጠቀም ብቻ ሳይሆን በይበጥ ኀላፊነትን በመሸከም፣ ፈረንሳይ፣ እዚህም ላይ መሪዋ፣ ፕሬዚዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ምንድን ነው ያከናወኑት? ቀጥሎ፣ የሳርኮዚን ያለፉት 6 ወራት የዲፕሎማሲ ክንዋኔዎች መለስ ብለን እንቃኛለን።---ተክሌ የኋላ ---

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ፣ ባለፉት 6 ወራት፣ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ፣ ከአወዛጋቢ ክስተቶች አንጻር፣ በገሐዳዊ የፖለቲካ ፈለግ ተከታይነት ጥንካሬአቸውን ያሳዩ መሪ መሆናቸውን፣ የፖለቲካ ድርጊት ተንታኞች እየመሠከሩላቸው ነው። የፈረንሳዩ መሪ በመጪው ወር ተዘዋዋሪውን ሥልጣን ለተረኛ ቼክ ሪፓብሊክ ከማስረከባቸው በፊት፣ ባለፈው ዓርብ፣ እንደምንም ታግለው፣ ከየፋብሪካውና ተሽከርካሪው የሚትጎለጎል የተቃጠለ አየር፣ እ ጎ አ እስከ 2020 በ 1/5ኛ እንዲቀነስ 27 ቱ አባል አገሮች እንዲስማሙ አብቅተዋል። ሳርኮዚ፣ ባለፉት 6 ወራት የአውሮፓው ኅብረት የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ወቅት ከገጠሙአቸው ዐበይት ፈተናዎች መካከል የጂዎርጂያና የሩሲያ ግጭት እንዲሁም ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ቀውስ ዋንኞቹ ሲሆኑ፣ በተለይ የሩሲያንና የጂዎርጂያን መቆራቆስ ለማርገብና ለውዝግቡም መፍትኄ ለመሻት ወደ ሞስኮና ቲፍሊስ ተጉዘው የደረሱበትን ስምምነት ሲያስታውቁ እንዲህ ብለው ነበር።

«በአንድ ወር ውስጥ የሩሲያ ወታደሮች በመላ፣ ከኦሴቲያና አብኻዚያ በስተቀር ከጂዎርጂያ ግዛት ሙሉ-በሙሉ ይወጣሉ።»

ሩሲያ ጦሯን እንደምትመልስ ያስታወቀችው፣ ወታደሮቿ በመገሥገስ፣ ወደ ጂዎርጂያ መዲና ከተቃረቡ በኋላ ነበር። የአውሮፓው ኅብረት፣ ከዚያ በፊት በተናጠል፣ ዐቢይ ዓለም አቀፍ ውዝግብ እልባት እንዲያገኝ ያደረገበት ጊዜ አልነበረም። የሰላም ውል መደረጉም ለሳርኮዚ ዲፕሎማሲያዊ ዝናን ነበረ ያተረፈላቸው። ያም ሆኖ ባለተጠበቀ ሁኔታ ድንገት ያገረሸው ውጊያ አውሮፓውያንን አስደንግጦ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም።

«እቅጩን ለመናገር ፣ ይህም በግልጽ መታወቅ ያለበት ነው፣ ሩሲያ በጂዎርጂያ ላይ የወሰደችው እርምጃ ያለተመጣጠነ ሲሆን፣ የጂዎርጂያ አካላት የሆኑትን የአብኻዚያንና የደቡብ ኦሴቲያን ነጻነት መቀበሏም በአውሮፓ ጥልቅ ሥጋት አስከተሏል። ተጽእኖ ማሳረፍ የሚቻልባቸው አካባቢዎች ወይም አገሮች አሉ ብሎ ፖለቲካ ማንቀሳቀስ ተቀባይነት የሌለው ነው። የያልታ የታሪክ ምዕራፍ ተደምድሟል።»

ሳርኮዚ ይህን ባሉበት ወቅት፣ በቅርቡ የአውሮፓ ታሪክ የሰርቢያ የግዛት ግማድ ኮሶቮ፣ እንዲገነጠልም ሆነ ነጻነት እንዲያውጅ፣ ዕድል ማግኘቱ ፣ ሩሲያ በአብኻዚያና ደቡብ ኦሴቲያ ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ በር ስለመክፈቱ፣ የተነፈሱት ቃል የለም።

ሌላው፣ የዩናይትድ ስቴትስ Lehman Brothers Bank መንኮታኮቱ፣ በአውሮፓ ብርቱ ድንጋጤ ካስከተለ በኋላም ሳርኮዚ ይህን ቀውስ እንደ ማለፊያ አጋጣሚ በመጠቀም 15 የዩውሮ ተጠቃሚ አውሮፓውያን መንግሥታትን ፓሪስ ላይ ሰብስበው፣ የዩውሮ ተጠቃሚ ያልሆነችው ሀገር ብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራውን፣ የከሠሩ ባንኮች እንዲያገግሙ ያቀረቡትን አቅድ፣ ሳርኮዚ ለአውሮፓውያንም፣ ያ ዓይነቱ አሠራር ፣ ዋስትና እንደሆነ አድርገው ያቀረቡትን የመፍትኄ ሐሳብ ፣ ጀርመንም በጥያቄ ምልክት፣ ብዙዎቹ ደግሞ፣ ሙሉ በሙሉ ተቀብለውታል።

ሳርኮዚ፣ ቀጥተኛ አቋም ያልያዙበትና እንደ ድክመትም የታየ ጉዳይ ቢኖር፣ ከቻይና ጋር ያላቸው ግንኙነት ሲሆን፣ ይህም፤ ዳላይ ላማን በመቀበላቸው፣ የአውሮፓ ኅብረትና የቻይና መሪዎች ጉባዔ እንዲሠረዝ ሰበብ ሆነዋል። በአውሮፓው ኅብረት የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ሳቢያ፣ ሳርኮዚ በአመዛኙ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ዝናን ቢያተርፉም፣ በሁለት ሳምንት ገደማ ውስጥ ይህንኑ ሥልጣን ስለሚያስረክቡ፣ በብሔራዊ ፖለቲካ ላይ መጠመድ ሳይሆን አይቀርም የወደፊት ዕጣቸውም ሆነ ትኩረታቸው። በመጪው ጥር ደግሞ፣ ግርማ ሞግስ ያላቸው፣ የዩናይትድ ስቴትስ፣ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት፣ ባራክ ዖባማ፣ ወደ ዓለም የፖለቲካ መድረክ፣ ብቅ ይላሉ።