1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፌስቡክ ጎልማሳ መሆን

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2006

በፌስቡክ ላይ የተደረገ አንድ አዲስ ጥናት እንደሚያመላክተው አሁን አሁን ከወጣቱ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ቁጥር የጎልማሳው እየበለጠ መጥቷል።

https://p.dw.com/p/1AY8w
Facebook Fahndung Hamburg
ምስል picture-alliance/dpa

በፌስቡክ ላይ ጥናት ያካሄዱት ተንታኞች እንደሚሉት። «ፌስቡክ ጎልማሳ ሆኗል» ይህም የተጠቃሚውን እድሜ አመሳክረው መሆኑ ነው። በጥናቱ መሰረት ፌስቡክ እና ሌሎች የማህበራዊ መገናኛዎች ላይ የሚመዘገበው ወጣት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀነስ ላይ ይገኛል። በተለይ ከ35 ዓመት በታች ያሉ ተጠቃሚዎች ሌላ የማህበራዊ መገናኛዎችን መምረጥ ጀምረዋል፤ ይህን ያሉት ስለ መስሪያ ቤቱ የገቢ ይዞታን በተመለከተ የተንታኞች ጉባኤ ላይ የተገኙት የፌስቡክ የገንዘብ አስተዳዳሪ ዴቪድ ኤበርስማን ናቸው።
ፌስቡክ በቅርቡ የአክስዮን ገበያን ከተቀላቀለ ጀምሮም የአክሲዮኑ ዋጋ እንብዛም ከፍ አላለም። ሁሌም እንዳዋዠቀ ነው። ይሁንና ፌስቡክ ይህን ያህል አስጊ የሚባል ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው ይላሉ ሙኒክ ከተማ የሚገኘው የ JFF የጥናት እና ምርምር ተቋም የመገናኛ ብዙኋን መምህር ኒልስ ብሩግን። ታድያ ለምን ከ35 እድሜ በታች ያሉት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲህ ቀነሰ? በዚህ ጥያቄ ላይ ተመራማሪዎቹ መልስ አላቸው። ወጣቶች ወላጆቻቸው እና አስተማሪዎቻቸው ፌስቡክ ውስጥ ጓደኞቻቸው ሆነው በማንኛውም ሰዓት የሚፃፃፉትን እና ጓደኛ የሚያደርጉትን ሰው መከታተል መቻላቸው ወጣቱን ከፌስቡክ ያሸሸ አንዱ ምክንያት ነው ተብሏል። ካስትን ቬንዝላፍ -ከኮሚኒኬሽን እና ማህበራዊ መገናኛ ተቋም በዚህ ይስማማሉ። «በእውነተኛው ዓለምም ቢሆን ወጣቶቹ ወላጆቻቸው የሚሄዱበት መሸታ ቤት ሄደው አይጠጡም» የሚል ነበር መልሳቸው። በርግጥ
ባለፉት ዓመታት ወላጆች ልጆቻቸው ፌስቡክ ውስጥ ከማን ጋ እንደሚፃፃፉ ለመቆጣጠር ሲሉ ራሳቸው አባል ሆነው እንደሚመዘገቡ በተደጋጋሚ ተወስቷል። ይህ ብቻ አይደለም ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ወጣቶቹን ከፌስቡክ እያሸሸ ያለው፤ ማህበራዊ መገናኛው መመሪያ ለተጠቃሚው ውስብስብ እና ግራ የሚያጋቡ በመሆኑ ነው።
ምንም እንኳን በጥናቱ መሰረት ወጣቱ የማህበራዊ መገናኛ ገፆችን መጠቀሙን ቢቀንስም ፤አማራጭ አግኝቷል። ይህም እንደ «ኃትስ ዓፕ » እና ቫይፐር ባሉ የስልክ መልዕክት ማጫወቻዎች ፎቶ እና የድምፅ መልዕክቶች መለዋወጥ ችሏል። ቀደም ሲል ፌስ ቡክ ብቸኛ አማራጭ የነበረበትን ምክንያት የመገናኛ ብዙኋን መምህር ኒልስ ብሩግን ያብራራሉ።

« እስካሁን ፌስ ቡክ ጠንካራ ነበር። ምክንያቱም ተጠቃሚው ወደ ሌላ የማህበራዊ መገናኛ ልሂድ ቢል የሚያውቃቸውን አድራሻዎች ሁሉ እንደ አዲስ መፈለግ ነበረበት። ሰው የማህበራዊ መገናኛዎች የሚጠቀመው ደግሞ ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋ ሁሌም ግንኙነት ኖሮት ለመቆየት ነው። ይህ ዋንኛው ምክንያት ነው። አሁን አሁን ግን ስልክ ላይ አንዴ የሚያውቋቸው ቁጥር ካለ፤ የ ኃትስ ዓብን ማጫወቻ ስልክ ላይ ሲጫን ሁሉንም አድራሻዎች መልሶ ማግኘት ይቻላል።»
ይህ ማለት ግን የፌስቡክ ድርጅት የግድ ስጋት ይግባው ማለት አይደለም ይላሉ ቬንዝላፍ -ከኮሚኒኬሽን እና ማህበራዊ መገናኛ ተቋም። ጎልማሶቹ እና ከ35 ዓመት በላይ የሆኑት ተጠቃሚዎች ወደፊትም ፌስ ቡክ መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ።

« እነኚህ የማህበራዊ መገናኛዎች እየጎለመሱ ይሄዳሉ። የተሻለ ተግባር እየኖራቸው ይሄዳል። ይሁንና ፌስቡክ አሁን ጎልማሶችን ይበልጥ ስለሳበ ። የማህበራዊ መገናኛው አበቃለት ማለት አይደለም። »
ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎችስ የፌስቡክን ጎልማሳ መሆን አስመልክቶ ምን አይነት አስተያየት አላቸው? ከፌስቡክ ሌላስ አማራጭ የሚሆን ምን ዓይነት የማህበራዊ መገናኛዎች ይጠቀማሉ? በፌስቡክ ገፃችን ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡን ውስጥ የጥቂቱ እንዲህ ይላል።

ብርሃኑ ፤ «ጉግል + ከምጠቀማቸው የማህበራዊ መገናኛዎች አንዱ ነው። ፌስ ቡክ ግን የበለጠ ታዋቂነት ስላለው ብዙ ሰዎች ያዘወትሩታል። » ሲል፤አብይታ በጥናቱ ውጤት ይስማማል። እሱም « በአሁን ጊዜ ከወጣቶች ይልቅ ጎልማሶች በብዛት ፌስቡክ ይጠቀማሉ» ይላል። ጉደኛኝ ለማግኘት ጥቅም ላይ ይውላል። እኔ ለምሳሌ ጓደኛዬን ያገኘኋት ፌስቡክ ላይ ነው። ብሏል።

ኤስላም ሰላም ደግሞ «የኛ ወላጆች እንኳን ሊቆጣጠሩን ስለ ፌስቡክ ስንነግራው ማመን እያቃታቸው ተቸግረናል።» ሲል አሉ ደግሞ «እኔ ራሴ ጎልማሳ ነኝ። ግን ልጄን ለመቆጣጠር ሳይሆን ለመረጃ እና ለማህበራዊ ግንኙነት ነው የምጠቀመው። በዛ ላይ ከጊዜው ጋር ለመሄድ እድሜ አይወስነውም» ብሏል።
አሚርም፤ «ፌስ ቡክ እድሜ ሊገድበው አይገባም። ጥሩ የመረጃ ምንጭ ነው። እንደፈለገ የምናወራበት ከሩቅ ዘመዶች በነፃ የምንገናኝነት ነው »ብሏል። ሌሎች አስተያየቶችም በፌስ ቡክ ደርሰውናል። ቀጥላችሁ ተወያዩበት።

በዶይቸ ቬለ የአማርኛው የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ሰሙኑን ተጠቃሚዎች ከተወያዩበት ርዕስ አንዱ ለምሳሌ በኔልሰን ማንዴላን ሞት የተሰማቸውን ሀዘን የገለፁበት ነው። ማንዴላን እንዲህ ያስታውሷቸዋል፤
ዋቤ፤ ከማንዴላ የተማርኩት...ጀግንነት ! ፍቅር ! አባትነት ! ለህዝብ መኖርን ! ነው ሲል የሀበሻ ልጅ ፤ ደግሞ «ያሸነፈ የሚፈልገውን ህግ እያወጣ ተሸናፊን መበቀል በተለመደበት ዓለም ስልጣኑን ሲይዝ የበደሉትን ይቅር ብሎ መቻቻልን ያስተማረ ታለቅ መሪ ብሏቸዋል።»
አለሙ፤ «በምድር ላይ በይቅርታና በዉይይት የማይፈታ ችግር እንደሌለ አንዲሁም ከስኬት ለመድረስ የሚከፈል መስዋዕትነት እንዳለ ተማርኩኝ::

መሰረት ደግሞ ፤ ታላቁ የነፃነት ታጋይ ቢዙ ያስተማሩንና የነፃነት ጮራ ነዎት ። ርስኦ ቢለዮንም ስምዎና ስራዎ ለዘላለም ይኖራል።ዉድ አባታችን እግዚአብሄር ነፍስዎች በገነት ያኑርልን። ብላለች።
አስማማው ፤« ለነፃነቱ ሳይሆን ለሀገሩ ነፃነት የኖረ ለምን እንደተፈጠረ አውቆ በኖረበት ጊዜ በትክክል የኖረ ሳይሞት የኖረ ሞቶም ይኖራል ማንዴላ ነብስ ይማር አይባልም ሳይሞት ተምሩዋልና። ነው ያለው ፤ ሌሎችም በርካት መልዕክቶች በፌስ ቡክ ገፃችን ላይ ይነበባሉ።

ልደት አበበ

Facebook Nelson Mandela (Screenshot)
ምስል Facebook
Deutschland Technologiekonferenz TechCrunch Disrupt in Berlin
ምስል imago/Rüdiger Wölk
Symbolbild Facebook verdient an Smartphone-Werbung
ምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ