1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ መስከረም 29 2010

በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ግጭቶች ተቀስቅሰዉ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን በሺዎች የሚቆጠሩትም ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን ስንዘግብ ቆይተናል። በወቅቱም  ለወራቶች የዘለቀዉን ግጭት ለማብረድ ከፌዴራል መንግሥት በኩል ቸልተኝነት ታይቷል በሚል ትችቶች ተደምጠዋል።

https://p.dw.com/p/2lWPP
Karte Äthiopien englisch

Fed. Frowned on Ethio-Somali Commn. Office - MP3-Stereo

በመስከረም ወር መግቢያ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግጭቱ ወዳለበት ስፍራ የፌዴራል ፖሊስና የመከላክያ ሠራዊት ኃይልን እንደሚልኩና ግጭቶቹን ለማብረድም እንደሚሞክሩም ተናገሩ።

በዚያዉ ሰሞንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ግጭቱ በተከሰተባቸዉ የኢትዮጵያ ሶማሌን እና የኦሮሚያን ክልል የሚወክሉ ሽማግሌዎችን ጠርተዉ አነጋግረዉ ነበር። በጊዜዉም በሁለቱም ክልሎች ያሉት የመገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩት ፕሮፖጋንዳ እየጎዳን ነዉ በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩ በሬዲዮ፣ በቴሌቬዝንና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይህን  የሚያደርጉ ግለሰቦች በሕግ እንደሚጠየቁ እንዲህ ነበር ያሳሰቡት።

እንዲያም ሆኖ አሁንም በክልሎቹ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ለተከሰተዉ የግጭት መነሻም ሆነ አሁንም የቀጠለዉን አለመረጋጋት በተመለከተ ሁለቱም የክልሉ መስተዳደሮች አንዳቸዉ በሌላቸዉ ላይ ጣት መጠቋቆም ቀጥለዋል። ባለፈዉ ሳምንት የሶማሌ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ በድረገፃቸዉ ላይ የኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ሶማሌን መሬት በኃይል ለመዉሰድ ፈልጓል፣ የሶማሊላንድና የሶማሊያ ወደብን በመጠቀምም ጦር መሳርያ ለማስገባት እንደሚፈልግ፣ የፌዴራል ስርዓቱን ማተራመስ ፈልጓል የሚልና ተያያዥ ዝርዝር ክስ አስነብበዋል።

የፌደራል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ትላንት ባወጣዉ መግለጫ ይህ የተሰራጨዉ መረጃ «መንግሥት ያስቀመጠዉን አቅጣጫ የሚቃረንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚያራምድ ማንኛዉም አመራር የማይጠበቅ» ነዉ በማለት ተችቷል።

የሁለቱም ክልል የኮሙንኬሼን አመራሮች ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲወነጃጀሉ ታዝብያለሁ የሚለዉ የድረገጽ ጸሐፊ በፍቃዱ ኃይሉ የክልሎቹ መንግሥታት የሚነጋጋሩ አይመስሉም፣ መንግሥት መከፋፈሉም ማሳያ ነዉ ሲል ለዶይቼ ቬሌ አስተያየቱን ሰጥቷል።

በዶይቼ ቬሌ የዋትስአፕ ገፆ ላይ በተመሳሳይ መንግሥት ያወጣዉን መግለጫ በሚመለከት ስማቸዉን ሳይጠቅሱ አስተያየታቸዉን የላኩልን አሉ። አንድ ግለሰብ መግለጫዉ «በጣም የዘገየ መግለጫ ነው» ሲሉ፣ ሌላኛዉ ደግሞ «ይህ የመንግሥት መግለጫ አልኩ ከማለት በሰተቀረ አንዳች ለውጥ እንደማያመጣም» ብለዋል። «የፈዴራል ኮሚኒኬሽን ያወጣዉ መስጠንቀቂያ ትረጉም የለዉም፣ ለምን ብትሉ ለግጭቱ መንስኤ የፈዴራል እጅ አለበት» የሚል ትችትም የሰንዘሩ ይገኙበታል።

ከክልሎቹ መንግሥታት በኩልም ሆነ ከፌዴራል የኮሙንኬሼን ጽሕፈት ቤት አመራሮች የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ