1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍትህ አካላት በሙስና መዘፈቅ

ዓርብ፣ ግንቦት 17 1999

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሙስና በፍትህ አካላት ተስፋፍቷል ይላል

https://p.dw.com/p/E87w

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በሚል ስያሜ የሚጠራው ዓለም ዐቀፉ ፀረ-ሙስና ድርጅት በዓለም ዙሪያ በፍትህ ስርዓት ውስጥ ሙስናና ጉበኝነት መስፋፋቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ ። ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው የሁለት ሺህ ሰባት ዘገባ እንዳመለከተው በፍርድ ቤቶች በተንሰራፋው ሙስና ሰበብ ዜጎች ፍትህ እየተነፈጉ ነው ። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው በአብዛኛዎቹ አገራት የችግሩ ዓብይ መንስኤ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ሲሆን መንግስታት ለፍትህ ስርዓቱ አስተዳደር የሚሰጡት ድጋፍ አናሳ መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው ።
ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በሚያራምዱ ማህበረሰቦች ሰዎች ሁሉ ከህግ ፊት እኩል መሆናቸው የስርዓታቸው ምሶሶ ነው ። ይሁንና በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የዓለም ክፍል የፍትህ አካላት በስግብግብነት ወይም በፖለቲካ ተፅዕኖ ምክንያት ለሙስና በመጋለጣቸው ህዝቦች የፍትህ ያለህ እያሉ ነው ። በመሰረቱ የአንድ ሀገር ህግጋት የጀርባ አጥንት የሆኑት የፍትህ አካላት ነፃና ከሙስና የፀዱ የህዝቡ አገልጋዮች መሆን ነበረባቸው ። ሆኖም ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ግን አፍሪቃን ጨምሮ በሌሎች አህጉራት የፍትህ ስርዓቶች በሙስና የተዘፈቁ ናቸው ። በነዚህ አገራት ያለውን ሙስናም በድርጅቱ ነባር የምርምር አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ቪክቶሪያ ጄኔት በሁለት ይከፍሉታል ።
“ አንዱ በዳኞች አመራረጥ ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነው ። መንግስት በአብዛኛው ዳኞችን በሚሰይሙት ላይ ጫና ያደርጋል ። በተጨማሪም በፍርድ ቤቶች ብይን ላይም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አለ ። ዳኞች የፖለቲካ ስልጣን ለያዙት ወገኖች የሚጠቅም ብይን እንዲያሳልፉ ግፊት ይደረግባቸዋል ። ሁለተኛው የሙስና ዓይነት ደግሞ ጉቦ ነው ። ዜጎች ፍትህ ለማግኘት ከዳኞችና ከፍርድ ቤቶች አስተዳደር ሰራተኞች ጉቦ ይጠየቃሉ ። “
ጉቦው የሚሰጠው ዶክተር ቪክቶሪያ እንዳሉት ፍርዱ እንዲፋጠን ወይም እንዲዘገይ ሊሆን ይችላል ። በብዙ የዓለም ክፍል ውሳኔ ያላገኙ በርካታ ፋይሎች ፍርድ ቤቶች ውስጥ ተራቸው ይጠብቃሉ ። በአለም ዙሪያ በፍትህ አገልግሎት ውስጥ ስርዓት ከሙስና ጋር የተገናኘው ችግር የሰፋ ቢሆንም የአፍሪቃው ደግሞ ስር የሰደደ መሆኑን ነው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የፕሮግራም አስተባባሪ ዴቪዽ ኮሸል የሚናገሩት። ። ይህንንም ድርጅታቸው ባለፈው ዓመት በአፍሪቃ ያደረገውን ቅኝት በማጣቀስ ያስረዳሉ ።
“በዓለም ዙሪያ በፍትህ ስርዓቱና በሙስና ላይ በሁለት ሺህ ስድስት ካደረግነው ቅኝት ማየት እንደሚቻለው በወቅቱ መጠይቅ ከተደረገላቸው ፍርድ ቤቶች ይመላለሱ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ሀያ ሁለት በመቶው ጉቦ መክፈል ነበረባቸው ። ብዙዎችም የአፍሪቃ ፍርድ ቤቶች በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ። እና ችግሩ መኖሩ ግልፅ ነው ። “
ሆኖም እንደ ኮሸል በአንዳንድ የአፍሪቃ አገራት ሙስናን ለመዋጋት የተሀድሶ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆእኑ ተስፋ ሰጭ ነው ። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ለሙስና መስፋፋት በምክንያትነት ከሚጠቅሰው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በተጨማሪ የፍትህ አካላት የሰው ኃይልና የገንዘብ ዕጥረትም ሌላው መንስኤ ነው ። እነዚህና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታትም ድርጅቱ የመፍትሄ ሀሳቦችን አቅርቧል ።
“በመጀመሪያ የዳኞችን ምርጫ በሚመለከት ዳኞችን የሚመርጥ ገለልተኛ አካል መሰየም አለበት ። ዳኞች ግልፅ በሆነ አሰራር በችሎታቸው በዕውቀታቸውና በአልግሎታቸው ይመረጣሉ ። በሁለተኛ ደረጃ የፍርዱ ሂደት ግልፅ ይሁን ነው የምንለው ። ጋዜጠኞች ምሁራን የሲቪል ማህበራት እና ለሌች ዜጎች የፍርድ ሂደት የተካተተባቸውን መዝገቦች ሊያገኙ ይገባል ። በተጨማሪም ዳኞች በየጊዜው የሀብታቸውን መጠን ማሳወቅ አለባቸው ። ለዳኞችና ለፍርድ ቤት ሰራተኞች አመቺ የስራ ሁኔታዎች መሟላት አለበት ። በቂ ክፍያ ካላገኙና በተገቢው መንገድ ካልሰለጠኑ ፍትህ በአደገኛ ሁኔታ ይዛባል ።
ከመንግስት ውጭ የሆነ ሌላ ኃይል ዳኞችን በቀጥታ የሚቆጣጠርበት የአሰራር ስልት መዘርጋትም ተጠያቂነትን ለማጠናከር መወሰድ ከሚገባቸው ዕርምጃዎች ውስጥ አንዱ መሆን እንደሚገባው ነው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ነባር የምርምር አስተባባሪ ዶክተር ቪክቶሪያ ጄኔት የገለፁት ።